ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ እባቦች እና አራዊቶች በሚበዙበት ጫካ ውስጥ ከልጆቿ ጋር ስትኖር የተገኘችው ሩሲያዊት
የሕንድ ፖሊስ በደቡብ ካርናታካ ግዛት በዋሻ ውስጥ ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር ስትኖር ያገኛትን ሩሲያዊት ሴት ታሪክ ለመረዳት እየሞከረ ነው።
ፖሊሶች በቱሪስቶች በሚዘወተረው እና ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ የተለመደውን ቅኝት እያደረጉ በነበሩ ጊዜ ነው ኒና ኩቲናን ከልጇቿ ጋር ያገኟት።
ባለሥልጣናቱ የ40 ዓመቷ ሴት ከስድስት እና ከአምስት ዓመት ልጆቿ ጋር ሕንድ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል ሕጋዊ ሰነዶች የላቸውም።
በግዛቲቱ ዋና ከተማ ቤንጋሉሩ አቅራቢያ በሚገኝ የውጭ ዜጎች ማቆያ ማዕከል ውስጥ እንዲቀመጡ የተደረገ ሲሆን፣ በቅርቡም ከአገር እንዲወጡ ይደረጋል።
ኩቲና ከሕንድ የዜና ወኪል ኤኤንአይ ጋር ባደረገችው ሁለት የቪዲዮ ቃለመጠይቆች የአኗኗር ዘይቤዋን በማብራራት ተከራክራለች።
እሷ እና ልጆቿ በዋሻው ውስጥ በመኖራቸው ደስተኛ እንደሆኑ እና "ተፈጥሮ መልካም ጤናን ያጎናጽፋል" ስትል ተናግራለች።
ፖሊስ በጫካው ውስጥ ካገኛቸው አንድ ሳምንት ያለፈ ቢሆንም ስለ ሴትየዋ እና ልጆቿ እንዴት በእባብ እና በዱር አራዊት ወደተሞላው ጫካ እንደመጡ፣ ምን ያህል ጊዜ በዚህ ዋሻ ውስጥ እንደኖሩ እና በትክክል ማን መሆናቸውን ለመረዳት አልቻለም።
ፖሊስ ድንገት ያገኘው የዋሻ መኖሪያ
የኡታራ ካናዳ አውራጃ የፖሊስ የበላይ ተቆጣጣሪ ኤም ናራያና ለቢቢሲ እንደተናገሩት "አካባቢው በቱሪስቶች በተለይም በውጭ ዜጎች ዘንድ ተወዳጅ ነው። ነገር ግን ብዙ እባቦች ያሉ ሲሆን፣ በተለይ በዝናብ ወቅት ደግሞ ለመሬት መንሸራተት የተጋለጠ ነው። የቱሪስቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል ካለፈው ዓመት ጀምሮ ጫካው ላይ ቅኝት ማድረግ ጀመርን።"
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ እና በቅኝቱ ላይ የነበረ ሌላ የፖሊስ ባልደረባ ደግሞ በጫካው ውስጥ ቁልቁለቱን ሲወርዱ ከቤት ውጭ እንዲደርቁ የተሰቀሉ ደማቅ ልብሶችን በማየታቸው ወደ ዋሻው እንደሄዱ ገልጿል።
ወደ ዋሻው ሲቃረቡ፣ በደማቅ የጨርቅ መጋረጃ ተሸፍኖ ከነበረው መግቢያ አቅራቢያ "አንዲት ትንሽ ሴት ልጅ እየሮጠች መጣች።" በሁኔታው የተደናገጡት ፖሊሶች ወደ ውስጥ ሲከተሏት ኒና ኩቲናን እና ሌላኛዋን ልጇ አገኙ።
ንብረታቸው የፕላስቲክ ምንጣፎች፣ አልባሳት፣ የፈጣን ምግብ እሽጎች እና አንዳንድ ሌሎች የግሮሰሪ እቃዎች ብቻ ነበሩ።
ዋሻው ደግሞ ውሃ አስርጎ እያስገባ ነበር።
ቢቢሲ ፖሊስ የቀረፀውን የዋሻውን ቪዲዮ የተመለከተ ሲሆን፣ ሕፃናቱ በቀለማት ያሸበረቁ የሕንድ ልብስ ለብሰው ፈገግ ብለው ይታያሉ።
ሚስተር ናራያና "ሴቲቱ እና ልጆቿ በቦታው በጣም ተመችቷቸው፤ ተደላድለው ነበር። እዚያ መኖር አደገኛ እንደሆነ ለማሳመን ጥቂት ጊዜ ወስዶብናል" ብለዋል።
በጫካው ውስጥ እባቦች እና የዱር እንስሳት በመኖራቸው ለደኅንነታቸው አደገኛ መሆኑን ፖሊሶች ሲነግሯት "እንስሳትእና እባቦች ጓደኞቻችን ናቸው፤ ሰዎች ናቸው አደገኞች" ስትል እናትየው መመለሷን ተናግረዋል።
ኩቲና እና ሴት ልጆቿ ከጫካው ካወጡ በኋላ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ ጤናማ መሆናቸውን ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።
ኒና ኩቲና ማን ናት?
በሕንድ የውጭ ዜጎች ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያለ አንድ ባለሥልጣን ሩሲያዊት እንደሆነች እና ተገቢው ሂደት እንደተጠናቀቀ ወደ አገሯ እንደምትመለስ ለቢቢሲ ገልጿል።
በቺናይ የሚገኘውን የሩሲያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ማነጋገራቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ቢቢሲም በዴልሂ ለሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ደብዳቤ ቢጽፍም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ኩቲና ከሕንድ ኤኤንአይ እና ፒቲአይ የዜና ወኪሎች ጋር ባደረገችው የቪዲዮ ቃለ ምልልስ በሩሲያ የተወለደች ቢሆንም ለ15 ዓመታት ያህል እዚያ እንዳልኖረች እና ወደ ኮስታሪካ፣ ማሌዥያ፣ ባሊ፣ ታይላንድ፣ ኔፓል እና ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ብዙ አገራት መጓዟን ተናግራለች።
በሁለቱም ቃለ ምልልሶች፣ ኩቲና ከ20 እስከ 5 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አራት ልጆች እንደነበሯት እና ባለፈው ዓመት በመንገድ አደጋ ስለሞተው ትልቅ ልጇ አንስታለች።
ባለሥልጣናቱ ሁለተኛ ልጇ 11 ዓመቱ ሲሆን፣ ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህንን መረጃም ለቆንስላ ጽ/ቤቱ ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል።
የውጭ ዜጎች ምዝገባ ቢሮው የልጆቹን አባት፣ ድሮር ጎልድስቴይን፣ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን እና እስራኤል ውስጥ ነጋዴ እንደነበር ማወቅ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በአሁን ጊዜ ሕንድ ውስጥ እንዳለ እና እንዳገኙት ኩቲና እና ሴት ልጆቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ወጪ እንዲሸፍን ለማሳመን እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጎልድስቴይን ለሕንድ የኤንዲቲቪ ቻናል ኩቲና እርሱ ሳያውቅ እንደሄደች እና ለፖሊስ መጥፋቷን የሚገልጽ ማመልከቻ ማስገባቱን አስታውቋል።
ልጆቹን በጋራ የማሳደግ መብት እንዲሰጠው እንደሚፈልግ እና የሕንድ መንግሥት ወደ ሩሲያ እንዳይልካቸው ለመከላከል የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግሯል።
ወደ ዋሻው መቼ መጡ?
ኩቲና እና ሴት ልጆቿ ወደ ካርናታካ ጫካ እንዴት እና መቼ እንደመጡ የሚገልጽ ምንም መረጃ የለም።
ፖሊስ በዋሻው ውስጥ ለሳምንት ያህል እንደቆዩ መናገሯን ገልጿል።
በተጨማሪም ከሳምንት በፊት ታዋቂ የሆነ ፈጣን ኑድልን ጨምሮ አንዳንድ አትክልቶችን እና ሌሎች የምግብ ሸቀጦችን በአቅራቢያው ካለ ሱቅ እንደገዛች ተናግሯል።
ከጎዋ ወደ ካርናታካ እንደመጣች መናገሯን በዋሻ ውስጥ መኖር እንደጀመረች መናገሯንም ገልጿል።
አንዷ ሴት ልጇ በጎዋ ዋሻ ውስጥ እንደተወለደችም ተናግራለች።
በሰጠችው ቃለ ምልልስ ከሴት ልጆቿ ጋር ስላለችበት የማቆያ ጣቢያ በማማረር "እስር ቤት ነው" ብላለች።
"በጣም ጥሩ ቦታ ላይ ነበር የምንኖረው። አሁን ግን ብቻችንን መሆን አንችልም። ወደ ውጭ መውጣት አንችልም። እዚህ በጣም ቆሻሻ ነው፤ በቂ ምግብም የለም" ስትል አክላለች።
ኩቲና መቼ እና እንዴት ወደ ሕንድ እንደመጣች ግልጽ አይደለም።
ፖሊስ ፓስፖርቷ እንደጠፋ መናገሯን፣ ነገር ግን ከንብረቶቿ መካከል የቆየ ፓስፖርት ማግኘታቸውን ይህም ከጥቅምት 18/2016 እስከ ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በቢዝነስ ቪዛ ወደ ሕንድ እንደመጣች ያሳያል።
ነገር ግን ቪዛው ከሚፈቅደው በላይ የቆየች ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ተይዛ በጎዋ የሚገኘው የውጭ ዜጎች ቢሮ ከሕንድ መውጣት እንድትችል "የመውጫ ቪዛ" መትቶላታል።
በፓስፖርትዋ ላይ ካለ የኢሚግሬሽን ማህተም መረዳት እንደሚቻለው ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ኔፓል ገብታ ከሦስት ወራት በኋላ ወጥታለች ከዚያ በኋላ ወዴት እንደሄደች ግልጽ አይደለም።
ነገር ግን ኩቲና ለኤኤንአይ እንደተናገረችው በአጠቃላይ "ቢያንስ ወደ 20 አገራት ተጉዛለች።"
ምንም እንኳን አንዳንድ ዘገባዎች ከየካቲት 2020 ጀምሮ ተመልሳ እንደመጣች ቢናገሩም፣ በቀጣይ ወደ ሕንድ መቼ እንደተመለሰች ግልጽ አይደለም ።
"በእውነት ሕንድን እንወዳታለን" ስትል ለፒቲአይ ተናግራለች።
ኩቲና ቪዛዋ ከጥቂት ወራት በፊት ማለቁን አምናለች።
"የሚሠራ ቪዛ የለንም፣ ቪዛችን አልቋል" ካለች በኋላ፣ ጥፋቱ የተከሰተው በሞተው ልጇ ሐዘን ምክንያት በመጎዳቷ እና ሌላ ነገር ምንም ማሰብ ስላልቻለች መሆኑን አስረድታለች።
በዋሻ ውስጥ የምትኖረው ለምን ነበር?
በዋሻ መኖሪያዋ ውስጥ የፓንዱራጋ ቪታላ፣ የሂንዱ አምላክ ቅርጽ የተገኘ ሲሆን፣ ለመንፈሳዊ ተመስጦ ወደዚያ እንደሄደች ተነግራለች።
ለኤኤንአይ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ግን ይህንን መረጃ ውድቅ አድርጋለች። "የመንፈሳዊ ጉዞ አይደለም። እኛ ተፈጥሮን ስለምንወድ፣ ጤና ስለሚሰጠን ነው...በጣም ትልቅ ጤና ነው፤ በቤት ውስጥ እንደምትኖረው አይደለም።"
አክላም "በተፈጥሮ ውስጥ፣ በጫካ ውስጥ የመቆየት ትልቅ ልምድ" እንዳላት እና ሴት ልጆቿ ደስተኛ እና ጤናማ እንደሆኑ ተናገራለች። የመረጠችው ዋሻ "በጣም ትልቅ እና የሚያምር" እንዲሁም "ለመንደር በጣም ቅርብ" በመሆኑ ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን መግዛት ትችል እንደነበርም አስረድታለች።
"እየሞትን አልነበረም። ልጆቼን፣ ሴት ልጆቼን በጫካ ውስጥ እንዲሞቱ አላመጣኋቸውም። በጣም ደስተኞች ነበሩ። በፏፏቴው ውስጥ ይዋኙ ነበር። ለመተኛት በጣም ጥሩ ቦታ ነበራቸው። በሥነ ጥበብ ሥራ ላይ ብዙ ትምህርት ነበራቸው። ሸክላ እንሠራለን፤ ሳልን፤ ጥሩ በላን፤ በጣም ጥሩ እና ጣፋጭ ምግብ እያበሰልኩ ነበር" ስትል ለኤኤንአይ ተናግራለች።
በተጨማሪም ኩቲና በጫካ ውስጥ መኖር ልጆቿን ለአደጋ ያጋልጣል የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርጋለች።
"እዚያ በኖርኩባቸው ጊዜያት ጥቂት እባቦችን አይተናል" ካለች በኋላ፤ ይህም ሰዎች በቤታቸው፣ በማዕድ ቤታቸው ወይም በንጽህና ቤታቸው ውስጥ እባብ ማግኘታቸውን እንደሚናገሩት ነው ብላለች።