ቻይና እንደ ተገንጣይ የምታያቸው ዳላይ ላማ ማን ናቸው? በቡድሂዝም እንደገና መወለድ ምንድን ነው?

የቲቤት መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማ እሁድ 90ኛ ዓመታቸውን ያከብራሉ።

በቡድሂዝም እምነት ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸው ዳላይ ላማ ከሞቱ በኋላ ተተኪ እንደሚኖራቸው አረጋግጠዋል።

ዳላይ ላማ እንደገና ወደ ምድር ተመልሰው የሚመጡበትን ሁኔታ (ሪኢንካርኔሽን) በተመለከተ የመሠረቱት የጋደን ፎድራንግ ትረስት ብቻ ነው የማወቅ ሥልጣን ያለው ብለዋል።

14ኛው ዳላይ ላማ ተተኪያቸውን በተመለከተ መመሪያ ይሰጣሉ በሚል ለረጅም ጊዜ ሲጠበቁ ነበር።

መንፈሳዊ መሪው ይህንን የተናገሩት ከቻይና አገዛዝ ሸሽተው በግዞት ከሚኖሩባት ከሰሜናዊ ሕንድ ዳራምሻላ ግዛት ነው።

ቻይና የራሷን የዳላይ ላማ ዕጩ ለመጫን ልትሞክር ትችላለች የሚሉ ስጋቶች በነገሱበት ወቅት ነው የዳይላ ላማ መግለጫ የተሰማው።

የዳይላ ላማን ንግግር ተከትሎ ቻይና በሰጠችው ምላሽ እንደገና ወደ ምድር የመመለሳቸው ሂደት (ሪኢንካርኔሽን) በማዕከላዊ መንግሥት ይሁንታ በቻይና ውስጥ መሆን አለበት ብላለች።

ቻይና በአውሮፓውያኑ 1951 የቲቤትን ግዛት የጠቀለለች ሲሆን፣ ዳላይ ላማንም እንደ ተገንጣይ ነው የምትመለከታቸው።

ዳላይ ላማ ማን ናቸው?

ዳላይ ላማ የቲቤት ጠባቂ የሚባሉት ቅዱስ አቫሎኪትሽቫራ ወይም ቼንሬዚግ መገለጫ እንደሆኑ ይታመናል።

ልክ እንደ ሂንዱ እና ጄይንስ ዓይነት እምነቶች ቡድሂስቶችም የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ እንደገና እንደሚወለድ ያምናሉ።

በቲቤት ባህል መሠረት በከፍተኛ ሁኔታ በመንፈስ የበለጸጉ ሰዎች መቼ እና የት ድጋሚ እንደሚወለዱ መወሰን ይችላሉ።

የአሁኑ ዳላይ ላማ የተወለዱት በሰሜን ምሥራቅ ቲቤት በአውሮፓውያኑ 1935 ነው።

ወላጆቻቸው ድሃ አርሶ አደሮች ናቸው።

በሁለት ዓመታቸው 13ኛው ዳላይ ላማ እንደገና እንደተወለዱ (ሪኢንካርኔት እንዳደረጉ) ዕውቅና ተሰጣቸው።

"ቲቤታውያን የዳላይ ላማ ነፍስ ደጋግማ እንደምትወለድ (እንደምትመጣ) ያምናሉ" ሲሉ ዶክተር ቱፕተን ጂንፓ ያስረዳሉ።

ዶክተር ጂንፓ በቲቤት ቡድሂዝም ከፍተኛ ሥነ መለኮትን የተማሩ የቀድሞ መነኩሴ ናቸው። ዶክተሩ ከአውሮፓውያኑ 1985 ጀምሮ የዳላይ ላማ ተርጓሚ ሆነው በማገልገል ይገኛሉ።

እሳቸው እንደሚሉት በቲቤት እምነት መሠረት ሁሉም ዳላይ ላማዎች አንድ ሰው ወይም የአንድ ሰው ቀጣይነት ናቸው። ሆኖም የአሁኑ ዳላይ ላማ ይህንን በቀጥታ የሚወስዱት አይመስልም።

"ቅዱስነታቸው 14ቱም ዳላይ ላማዎች አንድ ሰው ናቸው ብለው እንደማያምኑ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ" የሚሉት ዶ/ር ጂንፓ "ሆኖም በዚያ የዘር ሐረግ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከዳይላ ላማዎች የዘር ሐረግ ጋር ልዩ ግንኙነት ይኖረዋል ይላሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።

ቡድሂዝም ጥንታዊ እና ከ2,500 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እምነት ቢሆንም፣ የዳላይ ላማ ተቋም ግን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው።

"የመጀመሪያው ዳላይ ላማ በሰው ልጅነት ዕውቅና የተሰጠው በአውሮፓውያኑ 1391 ለተወለዱት ጌዱን ድሩፕ ነው። ነገር ግን የቡድሂስት መምህርን ዕውቀት እንዲሁም ተማሪዎቹን ወርሶ እንደገና የሚወለድ፣ ሪኢንካርኔት የማድረግ ጽንሰ ሃሳብ ከዚያ በጣም የቀደመ ነው" ሲሉ በአበርዲን ዩኒቨርስቲ የሂማልያን ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማርቲን ኤ ሚልስ ይናገራሉ።

አክለውም "ቢያንስ 300 ዓመታትን ወደ ኋላ ይቀድማል" ይላሉ።

ዳላይ ላማ እንዴት ይመረጣሉ?

"የዳላይ ላማ ምርጫ ሂደት በጣም ጥብቅ፣ ውስብስብ እና የተብራራ ሂደት ያለው ነው" በማለት ዶክተር ጂንፓ ያስረዳሉ።

ግለሰቡን ለመለየት ዓመታት ሊወስድ ይችላል። የአሁኑን፣ 14ኛውን ዳላይ ላማ እንደገና የመወለድ (ሪኢንካርኔሽን) ሂደት አራት ዓመታትን ወስዷል።

ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ መነኮሳት ከቀድሞው ዳላይ ላማ ሞት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የተወለደ ወንድ ልጅ መፈለግ ይጀምራሉ። ፍለጋቸውም በበርካታ ፍንጮች ይመራል።

ከመነኮሳቱ አንዱ የህጻኑ ማንነት በህልም ሊገለጥላቸው ይችላል። በቀድሞው ዳላይ ላማ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት የጭስ አቅጣጫው የሚያመራበት እንዲሁ ደግሞ የመፈጠር (ሪኢንካርኔሽን) ሊከሰት የሚችልበትን ቦታ አመላካች ተደርጎ ይወሰዳል።

የህጻኑ ቦታ ከተረጋገጠ በኋላ በርካታ ዕቃዎች ይቀርቡለታል። ህጻኑ የቀድሞውን ዳላይ ላማ ንብረቶች በተሳካ መልኩ ማወቅ ከቻለ እንደገና የመወለዱ ሂደት (ሪኢንካርኔሽን) ጥሩ ምልክት አድርገው ይመለከቱታል።

ዋነኞቹ መነኮሳት በምርጫው ደስተኛ ከሆኑ ልጁ ይመረጣል እንዲሁም የሃይማኖት ትምህርት እና የነገረ መለኮት ጥናት ለዓመታት እንዲሰጠው ይደረጋል።

እስካሁን ባለው ከቲቤት ውጪ የተወለዱት ሁለት ዳላይ ላማዎች ናቸው፤ አንደኛው በሞንጎሊያ፣ ሁለተኛው ደግሞ በሰሜን ምሥራቅ ሕንድ ነው።

የቻይና ቁጥጥር

ቻይና የቲቤት ግዛቷን ቁጥጥር ለማጠናከር በአውሮፓውያኑ 1950 በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰማራች። ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የተነሳው የፀረ-ቻይና አመጽ መክሸፉን ተከትሎ ዳላይ ላማ ሸሽተው በሕንድ በስደት መንግሥት አቋቋሙ።

ምንም እንኳን በግዞት ያለው የቲቤት መንግሥትነት ኃላፊነታቸውን ቢለቁም አሁንም የቻይና አገዛዝን በመቃወም ያለው ንቅናቄ ዋነኛ ተምሳሌት ተደርገው ነው የሚታዩት።

ዳላይ ላማ ቀደም ብለው ከቲቤት ውጪ እንደገና የመወለድ ሂደታቸው (ሪኢንካርኔሽን) እንደሚፈጸም ተናግረዋል። ይህም ቻይና ከምትቆጣጠራት ግዛት ውጪ የመምጣት ምላሽ ነው።

ቻይና በበኩሏ ዳላይ ላማ የፖለቲካ ግዞተኛ ናቸው የሚለውን አጣጥላ "በሃይማኖት ሽፋን ፀረ- ቻይና የመገንጠል እንቅስቃሴ የሚያካሂዱ" ስትል ትወነጅላቸዋለች።

በአውሮፓውያኑ 2007 ቻይና የቀጣዩን ዳይላ ላማን ምርጫ ለመቆጣጠር የሚመስል ትዕዛዝ አስተዋውቃለች።

ቻይና በቲቤት ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው በሚል የመብት ተሟጋች ቡድኖች ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል።

"የቻይና ባለሥልጣናት በቲቤት ሃይማኖታዊ ሂደቶች ላይ የሚያደርጉትን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ ማቆም እና የሃይማኖት አባት ተተተኪዎችን የቁጥጥር እና የኃይል መጠቀሚያ ማድረጋቸው ሊያከትም ይገባል" ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቻይና ዳይሬክተር ሳራህ ብሩክስ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

በቲቤት ላይ የሚደርሰው ጫና

ማንኛውም የቲቤት ተወላጅ ከውጭ ጋዜጠኞች ጋር በማውራታቸው ወይም የዳላይ ላማን ምሥል በመያዛቸው ሊታሰሩ ይችላሉ።

ሕንድ ተቀማጭነቱን ባደረገ የቲቤት ተሟጋች አማካኝነት ቢቢሲ በቲቤት የሚኖሩ ሁለት መነኮሳትን እና አንድ የቡድሂስት እምነት ተከታይን ማነጋገር ችሏል።

ባለሥልጣናቱ የዳላይ ላማ የልደት በዓል እንዳይከበር እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደሆነ ይናገራሉ።

"በእኔ መንደር [ባለሥልጣናቱ] ሁለት ስብሰባዎች ያካሄዱ ሲሆን፣ በዚያም ዳላይ ላማ ተሰድበው ለታዳሚዎቹ አስከፊ መዘዞች እንደሚከተላቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል" ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ በቲቤት የአምዶ ክልል ተወላጅ ተናግሯል።

የዳይላ ላማን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ የተሰማሩ የቻይና ፖሊስ እና ወታደሮች ቁጥር መጨመሩንም ያምናል።

"በገዳሙ እና በአካበቢው በርካታ ወታደሮች እንደተሰማሩ ተሰምቶናል" ይላል።

ቻይና በምታካሂደው ሳንሱር ምክንያት አንዳንዶች በተለይም ወጣቶች ከዳላይ ላማ ጋር ያላቸው ቀረቤታ እየመነመነ እንደሄደ ይገልጻል።

"በርካታ ወጣቶች አግኝተዋቸው አያውቁም። የሚያስገርመው ግን ስማቸውን የሚሰሙት ከቻይና መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ሥርጭቶች ብቻ ነው" ሲል ያስረዳል።

የቻይና የመነኩሴ ዕድሜ መመሪያ

"በወላጆቼ ፍላጎት ነው ገና በልጅነቴ የመነኮስኩት" ይላሉ ስማቸው የተቀየው ትስሪንግ።

በቻይና የሲቹዋን ግዛት የተወለዱት የ46 ዓመቱ መነኩሴ የመነኮሱት ገና በሰባት ዓመታቸው ነው።

ቻይና በጣለቻቸው አዳዲስ እገዳዎች ህጻናት ለመመንኮስ 18 ዓመት እስኪሞላቸው መጠበቅ አለባቸው። በዚህም ምክንያት በገዳማት ያሉ የመነኮሳት ቁጥር ቀንሷል።

"የጀማሪ መነኮሳት ቁጥር እየቀነሰ ነው። በዚህ ዓመት ሦስት አዳዲስ መነኮሳት ናቸው ወደ ገዳሙ የመጡት። ከዚያም በፊት ባሉት ዓመታት ለትምህርት እና ለአምልኮ ወደ ገዳሙ የሚመጡ ህጻናት ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል" ይላሉ።

መነኩሴው የቻይና አገዛዝ ያመጣው የምጣኔ ሀብት መመንደግ ባህልን በማውደም የመጣ ዋጋ ነው ይላሉ።

ባለው የትምህርት ዕድገት ምክንያት የቲቤት ቋንቋ እየተሸረሸረ እንደመጣም ያምናሉ።

ሌላኛው የአምዶ ንጋባ ግዛት መነኩሴ በበኩላቸው "የቲቤት ቋንቋ እና ጽሁፍ የቀጠለው በቡድሂዝም እምነት ምክንያት ብቻ እንደሆነ" ያስረዳሉ።

ቀጣዩ ዳላይ ላማ

14ኛው ዳላይ ላማ 600 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረውን ተቋም መጠበቅ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ተተኪ በመምረጥ ረገድ የቻይናውያንን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል የቻይናን ዕጩ ውድቅ እንዲያደርጉ ዳላይ ላማ ለተከታዮቻቸው ተናግረዋል።

"ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣት ስለማይፈልጉ ዝም ሊሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በቻይና መንግሥት ለተሾመ ዳላይ ላማ ማንም ዕውቅና አይሰጥም" ይላሉ ዶክተር ጂንፓ።

"ቻይና የሰዎችን አካል ልትቆጣጠር ትችላለች፤ ነገር ግን የቲቤት ተወላጆችን ልብ እና አእምሮ ግን ማሸነፍ አትችልም" ሲሉ ያክላሉ።

ቻይና በበኩሏ የቲቤት "ባሪያዎችን እና ገባሮችን" ነጻ አውጥታ ግዛቲቱን ከኋላ ቀር ሃይማኖታዊ የጨቋኝ ሥርዓት በማላቀቅ ወደ ዘመናዊነት ጎዳና እንድትገባ አድርጌያለሁ ትላለች።