ሞታቸውን ለማፋጠን የሚጾሙ ሃይማኖተኞች እንዳሉ ያውቃሉ?

የ88 ዓመቷ ሳያር ዴቪ ሞዲ የማኅጸን በር ካንሰር እንዳለባቸው ከታወቀ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ሕክምናቸውን ላለመከታተል ወሰኑ።

ከሕክምና ይልቅ እስከ መጨረሻው የእስትንፋሳቸው ህቅታ ድረስ መጾምን መርጠዋል።

"የሕክምና ሪፖርቷ ሲመጣ፣ ካንሰሩ በመላ አካላቷ እየተሠራጨ መሆኑን ያሳያል። ባለፈው ሐምሌ አንድ ዕለት ከጸለየች በኋላ ሾርባ ጠጣች። በማግስቱ ጠራችን እና ሳንታራ [ራስን ከእህል እና ከውሃ ማቀብ] ለማድረግ መወሰኗን ነገረችን" ሲል የልጅ ልጇ ፕራናይ ሞዲ ያስታውሳል።

ሳንታራ ወይንም ሳሌክሃና፣ በአንዳንድ የጄን ሃይማኖት ተከታዮች የሚፈጸም ከምግብ እና ከውሃ ራስን በማቀብ ሞትን የመጋፈጥ ሥርዓት ነው።

የሕንድ ሚዲያ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በዓመት ከ200 እስከ 500 የሚደርሱ የጄን እምነት ተከታዮች በዚህ መንገድ መሞትን ይመርጣሉ።

ይህ ግን የእምነቱ መሠረታዊ መስፈርት አይደለም።

አንዳንዶች ድርጊቱን ራስንን ማጥፋት ነው በማለት የተቃወሙ ሲሆን፣ በሳንታራ ላይ እገዳ የሚጠይቅ አቤቱታ ለሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተፈራርመው በማስገባት ውሳኔውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ጄኒዝም

ቢያንስ 2,500 ዓመት ዕድሜ እንዳለው በሚገመተው በዚህ ሃይማኖት፣ ጃይኒዝም፣ ሁከት ቦታ የለውም።

ለጄይኖች አምላክ የለም፤ ነገር ግን በንፁህ፣ ቋሚ፣ ግለሰብ እና ሁሉን አዋቂ ነፍስ ያምናሉ።

የጄን እምነት ተከታዮች ሁሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ አትክልት ተመጋቢዎች ናቸው።

ከዚህም ባሻገር ለሥነ ምግባራዊ እሴቶች ጥብቅ ትኩረትን ይሰጣሉ እንዲሁም ዓለማዊ ድሎት እና ምቾቶችን ንቀው ይተዋሉ።

በሕንድ ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ጄይን እምነት ተከታዮች አሉ።

ብዙዎቹ በደንብ የተማሩ ናቸው፤ አንድ ጥናት ከጄይን እምነት ተከታይ ጎልማሶች መካከል አንድ ሦስተኛው የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ አላቸው ይላል።

እና ብዙዎቹ በአንፃራዊነት ሞልቶ የተረፋቸው ሀብታምም ናቸው።

የጄይን የሃይማኖት አባቶች በሰፊው የሕንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የተከበሩ ናቸው።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጸሎት ለማድረስ በቤተ እምነቱ ተገኝተው ያውቃሉ።

በኤክስ ገጻቸው ላይም የአንድ የሃይማኖቱ መምህር ህልፈትን ተከትሎ ባሰፈሩት ጽሑፍ የግለሰቡ ሞት "ለአገሪቱ የማይተካ ኪሳራ" መሆኑን ገልጸዋል።

እኚህ የሃይማኖቱ መምህር በ77 ዓመታቸው ከሦስት ቀናት ጾም በኋላ ነበር ያረፉት። በቀብራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል።

ጄይኖች ሕይወታቸውን በጾም የማጠናቀቅ ሂደት ይሁነኝ ተብሎ ከሚደረግ ራስን ማጥፋት (mercy killing ) ወይም በሕክምና ከሚደረግ ራስን ማጥፋትን ጋር መወዳደር እንደሌለበት ይከራከራሉ።

በኮሎራዶ ዴንቨር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት እና የጄይኒዝም ኤክስፐርት የሆኑት ስቲቨን ቮዝ "ሳሌካሃና ወይም ሳንታራ በባለሙያ ከሚታገዙ ራስን ማጥፋቶች የሚለዩት ገዳይ የሆነን ማንኛውንም ነገር መውሰድ አያካትትም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ቮዝ ገለጻ ይህ ልምምድ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ "ሰውነትን መልቀቅ" ወይም "ሰውነት በራሱ ጊዜ እንዲከስም መፍቀድ" ተብሎ ተገልጿል።

ሕይወትን ማክበር

በካርማ፣ በነፍስ፣ ዳግም መወለድ እና መዳን ላይ ማመን የሳንታራ ቁልፍ መሠረታውያን ናቸው።

እንደ ሳያር ዴቪ ያሉ አንዳንድ የጄይን ሃይማኖት ተከታዮች ሞት በደጃፍ እንዳለ ባወቁ ጊዜ ወይንም ሊድን በማይችል ህመም መያዛቸውን ከተረዱ በኋላ ይህንን ሞት ይመርጣሉ።

በጾም ወቅት የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ላይ ሳያር ዴቪ ነጭ ሻርፕ (ሳሪ) ለብሰው አፋቸውን በእራፊ ጨርቅ ሸፍነው ይታያሉ።

ፕራናይ ሞዲ "እሷ የተረጋጋች፣ ንቅት ያለ አእምሮ የነበራት እና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ ታወራ ነበር" ሲል ያስታውሳል።

ሞዲ በአያቱ የመጨረሻ ጾም ወቅት በመካከለኛው ሕንድ በካብሪድሃም በሚገኘው ቤታቸው ብዙ ሰዎች በተገኙበት ድግስ ተዘጋጅቶ ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድ ተመልክቷል።

"በስፍራው ሞት ድባቡ የጣለ አይመስልም፤ የቤተሰብ አባላት፣ ዘመዶች፣ ጓደኞች፣ ጎረቤቶች እና ብዙ እንግዶች መጥተው ምርቃቷን ተቀበሉ።"

በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንኳን፣ ዴቪ 48 ደቂቃ የሚፈጀውን የጄይን ጸሎት ለማድረግ ጉልበታቸውን አልደከመም ነበር።

"መድኃኒቶቿን ካቆመች በኋላ በጣም ታማ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ፤ ነገር ግን ስለ ምንም ነገር አላጉረመረመችም። ብሩህ እና ሰላማዊ ትመስል ነበር" ይላል ሞዲ።

የዴቪ ልጆች፣ የልጅ ልጆቿ እና የልጅ ልጅ ልጆች ሕይወቷ እያከተመ ሲሄድ ተመለከተዋል።

ሞዲ "በዚህ መንገድ መሞቷን መመስከር ለእኔ በጣም ከባድ ነበር፤ ነገር ግን በተሻለ ቦታ ላይ እንደምትገኝ አውቃለሁ። ውሳኔዋን እናከብራለን።"

የመጨረሻው ትግል

ሳንታራ ሁልጊዜ እንደ እንቅልፍ ያለ ሰላማዊ ማሸለብ ላይኖረው ይችላል።

ፕሮፌሰር ሚኪ ቼዝ የዶክትሬት ዲግሪዋን የሠራችው በዚህ የፈቃድ ሞት ላይ ነው።

እና በደርዘን የሚቆጠሩ የመጨረሻ ጾሞችን ተመልክታለች።

በዊስኮንሲን-ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ የጄይን እምነት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር የሆነችው ቼዝ "አንድ ሰው በካንሰር መያዙን እና እንደማይድን ካወቀ በኋላ ሳንታራ ወስዶ [ጾሞ] ነፍሱ አልወጣ ብላ ተሰቃይቶ ነበር፤ ቤተሰቡ በውሳኔው ቢኮራም ቢደግፉትም፣ ሲሰቃይም ለማየት ተቸግረው ነበር" ብለዋል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ቼዝ ካንሰር ያለባት እና እንደማትድን ያረጋገጠች ሴት ጾም ከጀመረች በኋላ በጣም ተረጋግታ ሞት እንደ እንቅልፍ እያባበለ ሲወስዳት አይታለች።

"ምራቷ እሷን ማበረታታት እና ቁርጥ ውሳኔዋን መደገፍ እንደቤተሰብ ኃላፊነታቸው እንደሆነ እንደሚሰማቸው ነግረውኛል፤ እናም እርሷ በጾም ውስጥ ሳለች የአምልኮ መዝሙሮችን ይዘምሩላት ነበር።"

ፕሮፌሰር ቮስ "የተወሰነ ትግል የማይቀር ነው" ብለው ያምናሉ።

"ማንም ሰው በረሃብ ሲሞት ማየት ፈጽሞ አያስደስትም እና የመጨረሻዎቹ ጊዜያት በጣም አሳዛኝ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰውየው ወደ መጨረሻው አካባቢ ሰውነቱ ራሱን ለማዳን ሲታገል ምግብ ወይም ውሃ ሊጠይቅ ይችላል። ነገር ግን የእህል እና የውሃ ዘር ሊሰጠው አይችልም፤ ይህ በአብዛኛው የፍጻሜው አካል እንደሆነ ይታወቃል" ይላሉ።

በዚህ መንገድ የሞቱ የዲጋምበር መነኮሳት (ራቁታቸውን የሚንቀሳቀሱ) በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምሥሎቻቸው ሲዘዋወር ይታያል።

ከመራብ መጠማታቸው የተነሳ ሥጋቸው ጥሏቸው ሸሽቷል።

የጉንጫቸው አጥንት ወጥቶ፣ የጎድን አጥንታቸው በጣት ይቆጠራል።

ሳንታራ የተሰኘውን የፈቃድ ጾም አብዛኛውን ጊዜ የሚጾሙት ሴቶች ናቸው።

ፕሮፌሰር ቮስ ይህ የሆነበት ምክንያት ሲያስረዱ፣ ሴቶች የበለጠ በእምነታቸው ላይ ጠንካራ ሆነው በመታየታቸው እና እንዲሁም ከወንዶች የበለጠ ረዘም ላለ ዓመት ስለሚኖሩ ነው ይላሉ።

ፕሮፌሰር ቼዝ ማኅበረሰቡ ሳንታራን እንደ "አስደናቂ መንፈሳዊ ስኬት" ይመለከተዋል ብለዋል።

ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮች

በአውሮፓውያኑ 1929 የተወለዱት ሽሪ ፕራካሽ ቻንድ ማሃራጅ ጂ ከቀደምት የጄይን መነኮሳት መካከል አንዱ ናቸው። በ1945 ወደ ምንኩስና ሕይወት የገቡት እኚህ አባት፣ አባታቸው እና ታናሽ ወንድማቸውም መነኮሳት ነበሩ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ወደማይቀረው ሞት የሄዱት ራሳቸውን ከእህል እና ውሃ አቅበው (ሳንታራ) ጾመው ነው።

"አባቴን እና ወንድሜን በማየቴ አልተጨነቅኩም። ሙሉ በሙሉ ራሴን ነጠልኩ። ወላጅ አልባ ሆኜ አልተሰማኝም ወይም በሕይወቴ ውስጥ ባዶነት ይኖራል ስል አላሰብኩም።"

የ95 ዓመቱ አዛውንት የሚኖሩት በሰሜን ሕንድ በጎሃና ከተማ በሚገኝ ገዳም ውስጥ ነው። ስልክም ሆነ ላፕቶፕ አይጠቀሙም።

ከቢቢሲ ጋር የተነጋገሩት በደቀ መዝሙራቸው አሺሽ ጄይን በኩል ነበር።

"አማላይ ሞት የዚህ ሕይወት ፍፁም ፍፃሜ እና የቀጣዩ መልካም ጅምር ነው የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የእኔ ፍልስፍና፣ መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ መርሆች ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መነኩሴው ሳንታራ ብዙ ደረጃዎችን ያካትታል፤ ድንገተኛ ወይም ግብታዊ ሊሆን አይችልም ይላሉ።

አንድ ሰው ከቤተሰብ ፈቃድ ማግኘት እና እንደ መሃራጅ ጂ ካሉ መንፈሳዊ አስተማሪዎች መመሪያ መቀበል ያስፈልገዋል።

የሳንታራ የመጀመሪያ ደረጃ ሁሉንም ያለፉ ኃጢአቶችን እና በደልን መለስ ብሎ በመመልከት መቀበልን ያካትታል።

ከዚያ በኋላ አንድ ሰው ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልገዋል።

"አንድ ሰው በመጾም እና ሞትን በመጋፈጥ አካሉን እና ነፍሱን ማንጻት፣ መጥፎ ካርማዎችን መቀነስ፣ ለሚቀጥለው ውልደት ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት መዘጋጀት ይችላል" በማለት ማሃራጅ ጂ ያስረዳል።

"በመጨረሻም ነፍስን ከልደት እና ሞት ዑደት ነጻ በማውጣት ይጠናቀቃል።"

ሕጋዊ ተግዳሮቶች

በአውሮፓውያኑ 2015 በሰሜን ምዕራብ ሕንድ ራጃስታን ግዛት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዚህ ሃይማኖታዊ ድርጊት ላይ እግድ ጥሏል።

በኋላ ግን ውሳኔው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲዘገይ ተደርጓል።

የቀድሞ የመንግሥት ሠራተኛ ዲ.አር መህታ የሳንታራ ወግ ለመጠበቅ ከሚፈልጉ መካከል አንዱ ነው።

የሕንድ ማዕከላዊ ባንክ ምክትል ኃላፊ እና የአክሲዮን ገበያ ተቆጣጣሪ ሊቀ መንበር ሆነው የተሾሙት ሜህታ "የጄይን ተከታዮች ይህንን እንደ ምርጥ የሞት ዓይነት አድርገው ይመለከቱታል። ሆን ተብሎ የሚፈጸም፣ ሰላማዊ እና ሞትን በክብር መቀበል ነው፤ መንፈሳዊ መንጻት እና ዘላለማዊ ሰላም ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው" ይላሉ።

በ2016 በሃይደራባድ የ13 ዓመቷ ታዳጊ በተመሰሳይ ሁኔታ ከሞተች በኋላ ድርጊቱን የሚቃወሙ ሰዎች በርክተዋል።

ታዳጊዋ ለ68 ቀናት ከጾመች በኋላ ነበር የሞተችው፤ ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሞታቸውን እየጾሙ የጠበቁት አዛውንቶች ናቸው።

ማሃራጅ ጂ የሳንሌካና ሂደትን በ2016 ጀምሯል፤ ይህም ከሳንትራ በፊት ያለ ቅድመ ሁኔታ ነው።

መጀመሪያ ላይ ምግቡን በአስር ዓይነቶች ብቻ ገድቦ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ግን በሕይወት ያለው በሁለት የምግብ ዓይነቶች፣ ውሃ እና መድኃኒቶች ብቻ ነው። አሁንም ንቁ ሆኖ ይታያል።

ደቀ መዝሙሩ አሺሽ ጄን "ታምሞ ወይንም ደካማ ሆኖ አይገናኝም። ሁልጊዜ ደስተኛ ነው። ብዙም አያወራም።"

ማሃራጅ ጂ ቁጥብ አኗኗሩ መንፈሳዊ እድገት እንዲኖረው እንደረዳው ያምናል።

"ውስጣዊ ነፍሴ እና አእምሮዬ በጣም ደስተኞች ናቸው። ደስተኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነኝ።"