ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሙስሊሞች ለኢድ በዓል በግ እንዳያርዱ የሞሮኮው ንጉስ ጥሪ አቀረቡ
ሙስሊሞች ለኢድ አል አድሃ ክብረ በዓል በጎችን ከማረድ እንዲቆጠቡ የሞሮኮው ንጉስ መሐመድ 6ኛ ጥሪ አቀረቡ።
ንጉሱ ለሞሮካውያን ይህንን ያሉት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ነው።
እጥረቱ የተከሰተው በአገሪቱ ለሰባት ዓመታት በቆየው ድርቅ ነው ተብሏል።
በሰኔ ወር የሚከበረው ኢድ አል አድሃ ነቢዩ ኢብራሂም (አብርሃም) በአምላክ ትዕዛዝ ልጃቸውን ለመሰዋት ያሳዩትን ቁርጠኝነት የሚዘክር ነው።
ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአብዛኛውን ጊዜ በጎች ወይም ሌሎች እንስሳትን ያርዳሉ።
ምግብ ከቤተሰብ ጋር በመቋደስ ወይም ለድሆች በመስጠት በዓሏን ያሳልፉታል።
ነገር ግን በሞሮኮ የግጦሽ መስክ ደረቅ በመሆኑ ምክንያት የቀንድ ከብቶች 38 በመቶ መቀነሱን ይፋዊ መረጃ ያሳያል።
የስጋ ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል።
አገሪቷም 100 ሺህ የሚሆኑ በጎችን ከአውስትራሊያ ልታስገባ ነው።
በዚህ ወቅት በተለመደ ሁኔታ እንስሳትን በማረድ ዕለቷን ማስታወስ" በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል" ሲሉ ንጉስ መሐመድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ባነበቡት ንግግራቸው አስደምጠዋል።
አባታቸው ንጉስ ሐሰን ሁለተኛ ሞሮኮ ለረጅም ጊዜ በድርቅ መጠቃቷን ተከትሎ ተመሳሳይ ጥሪ በአውሮፓውያኑ 1966 አቅርበው ነበር።
የሞሮኮ የግብርና ሚኒስትር አህመድ ቡአሪ "እንደ መኪና እና ኢንዱስትሪ ላሉ ዘርፎች ቅድሚያ ውሃ በመስጠታችን የግብርና ዘርፉ ተጎድቷል፤ የመስኖ ስፍራዎች በጥብቅ መመሪያዎች ምክንያት ውሃ እንደ ልብ እያገኙ አልነበረም" ብለዋል።
በሞሮኮ በስጋ ላይ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት ሲባል በከብት፣ በበግ፣ ግመሎች እና እና ቀይ ስጋ ላይ የተጣለ የውጭ ንግድ ግብር እንዲሁም ቫት እንዲነሱ ተደርጓል።