በሕንድ ሴት ተማሪዎች የወር አበባ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ እርቃናቸውን መደረጋቸውን ተከትሎ ሁለት ሰዎች ታሰሩ

በሕንድ መፀዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ደም መገኘቱን ተከትሎ ሴት ተማሪዎች የወር አበባ ላይ መሆናቸውን ለመለየት እርቃናቸውን እንዲሆኑ መደረጉን ተከትሎ ርዕሰ መምሕሯ እና ረዳቷ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የፖሊስ እርምጃ የመጣው አሳፋሪው ድርጊት ተፈፅሞባቸዋል ከተባሉ "ከ10 እስከ 15" የሚሆኑ ተማሪዎች መካከል የአንዷ ተማሪ እናት ቅሬታ ማቅረቧን ተከትሎ ነው።

ድርጊቱ የተፈፀመው ማክሰኞ ዕለት ከሙምባይ ከተማ ብዙም ባልራቀ አካባቢ ነው።

ረቡዕ ዕለት ወላጆች በትምሕርት ቤቱ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን፤ በአስተዳዳሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል።

በተንቀሳቃሽ ምስል የትምሕርት ቤቱ ርዕሰ መምሕርት ከተቆጡ ወላጆች ጋር ሲጨቃጨቁ ታይተዋል።

ርዕሰ መምሕርቷ ድርጊቱ ስለመፈፀሙ እንዲሁም ተማሪዎቹ እርቃናቸውን ሆነው እንዲፈተሹ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ክደዋል።

ሚሊንድ ሺንዲ የተባሉ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ ድርጊቱን እየመረመሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የፖሊስ ክስ በምዕራብ ማህራሸትራ ግዛት ታሃን የሴቶች ትምሕርት ቤት አራት መምሕራንን እና ሁለት ባለአደራዎችን በስም ዘርዝሯል።

ቢቢሲ ለትምሕርት ቤቱ ኃላፊዎች መልስ እንዲሰጡት ጠይቋል።

ፖሊስ ለክሱ ጥቃት እና የሴቶችን ጨዋነት ለመጣስ መሞከር የሚሉ የሕግ ክፍሎችን ተጠቅሟል።

ከዚህ ባሻገርም ህፃናትን ከወሲባዊ ጥቃቶች ለመከላከል የወጣው ሕግ ክፍልም በክሱ አባሪ ሆኗል።

ወላጆች ከ5ተኛ እስከ 10ኛ ክፍል ያሉ ሁሉም ተማሪዎች (ከ10 እስከ 15 ዓመት እድሜ ያላቸው) ማክሰኞ ዕለት በትምሕርት ቤቱ ርዕሰ መምሕር ወደ አዳራሽ መጠራታቸውን ተናግረዋል።

በመቀጠል ተማሪዎቹ የመዳፍ አሻራን የሚያሳይን ጨምሮ በመፀዳጃ ቤቱ የተነሱ ምስሎችን በፕሮጄክተር እንዲያዩ ከተደረገ በኋላ፤ የወር አበባ ላይ የሆኑ ተማሪዎች እጃቸውን እንዲያወጡ ተጠይቀዋል።

ከዚያም አንድ መምሕርት እጃቸውን ካወጡ ተማሪዎች የመዳፍ አሻራ መሰብሰባቸውን ወላጆች ተናግረዋል።

ቢያንስ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ እና የወር አበባ ላይ አይደለንም ያሉ ተማሪዎች ወደ መፀዳጃ ቤት ተወስደው ለፍተሻ እርቃናቸውን እንዲሆኑ ተደርገዋል።

ቅሬታውን ለፖሊስ ያስገባቸው እናት፤ የወር አበባ ላይ ያልነበረችው ልጇ የንፅህና መጠበቂያ ለምን አላደረግሽም ተብላ ቁጣ እና ስድብ እንደደረሰባት ተናግራለች።

ልጄ በተፈጠረው ነገር "በጣም ሀፍረት ተሰምቷታል" ብላለች።

አንዳንድ ወላጆች ለቢቢሲ በድርጊቱ ልጆቻቸው መረበሻቸውን ተናግረዋል።

"ክስተቱ በልጆቻችን ደኅንነት ላይ ትልቅ ጥያቄ ነው ያስነሳው። ልጆቻችን በጣም ፈርተዋል። መንግሥት እዚህ ትምሕርት ቤት ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ አለበት" ሲሉ አንድ ወላጅ ተናግረዋል።

በሕንድ ዛሬም ድረስ የወር አበባ የሚያዩ ልጃገረዶች እና ሴቶች እንደ እርኩስ የሚቆጠሩ ሲሆን ከማኅበራዊ እና ኃይማኖታዊ ትዕይንቶችም ይገለላሉ።

በሴት ተማሪዎች ላይ የሚፈፀሙ እንደዚህ አይነት አሳፋሪ ድርጊቶች ከዚህ ቀደምም በሕንድ ታይተዋል።

እ.አ.አ በ2017 ኡታር ፐርዲሽ በተባለ ትምሕርት ቤት መፀዳጃ ቤት በር ላይ ደም ከተገኘ በኋላ 70 ሴት ተማሪዎች እርቃናቸውን እንዲሆኑ ተደርገዋል።

በ2020 በጉጅራት ኮሌጅ ተማሪዎች ቤተ መቅደስ፣ ማዕድ ቤት መግባት እና ሌሎች ተማሪዎችን ከመንካት የሚገድባቸውን የወር አበባቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን በማቆማቸው 68 ተማሪዎች እርቃናቸውን ሆነው ተፈትሸዋል።

የወር አበባ ላይ የሆኑ ተማሪዎች ምግብ ሲመገቡ ከሌሎች ተማሪዎች ርቀው እና ክፍል ውስጥ ደግሞ የመጨረሻው ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ይጠበቃል።

ይህ ኋላ ቀር አስተሳሰብ በተማሩ ሴቶች ተቃውሞ የገጠመው ቢሆን ስኬቱ እምብዛም እና አሁንም በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ሴቶች አድልኦ ይገጥማቸዋል።