ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐዘን ድባብ ያጠላባት የቤተልሔም ከተማ
እየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት የፍልስጤሟ ከተማ ቤተልሔም ዛሬ፣ ታህሳስ 16/ 2017 ዓ.ም የገና በዓል እየተከበረ ቢሆንም ሐዘን ወርሷታል።
የጎርጎሮሳውያንን የዘመን አቆጣጠር ለሚከተሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዛሬ የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ነው ነው።
ክብረ በዓሏ በተለያዩ አገራት በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ቢሆንም ከጋዛ ጦርነት ጋር ተያይዞ በቤተልሔም ደስታ ርቆ ሐዘን ነግሷል።
በአደባባይ ይደረግ የነበረው የገና በዓል አከባበር ለሁለተኛ ጊዜ እንዲሰረዝ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም በገና ወቅት በቤተልሔም የሚገኘው ማንገር አደባባይን ያጥለቀልቁ የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች እና የእምነት ተጓዦች ዘንድሮ የሉም።
ኢየሱስ ተወለደ ተብሎ በሚታመንበት ስፍራ የልደት ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የሚቆመው የገና ዛፍ በዘንድሮው የለም።
የገና ዘፈኖችም ሆነ መገበያያ ስፍራዎች የሉም። ቤተልሔም ወና ሆናለች፣ ሐዘን አጠልሽቷታል። ከተማዋ የቀድሞ ጥላዋን መስላለች።
ፍልስጤማውያን ክርስቲያኖች ከዚህ ቀደም የሚያደርጉትን የአደባባይ በዓል ትተው ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ብቻ ተከታትለው በቤታቸው ተወስነዋል።
"ይህ የደስታና የማክበር ጊዜ ሊሆን ይገባ ነበር። ነገር ግን በጋዛ ጦርነት ምክንያት እኛም ሐዘን ላይ ወድቀናል" ሲሉ በቤተልሔም የሉተራን ካህን የሆኑት ዶክተር ሙንዘር ይስሐቅ።
እየሱስ በበረት የተወለደበትን የሚያሳየውም ትዕይንት ህጻኑ እየሱስ በፍርስራሽ ክምሮች እና በሽቦ ታጥሮ በሚያሳይ ትዕይንት ተተክቷል።
ይህም የጋዛ ህጻናት እያለፉበት ያለውን ለማሳየት ነው።
የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ደምቆ የሚከበርባት የኔቲቪቲ (ልደት) ቤተ ክርስቲያን በዘንድሮውም ወና ሆናለች።
በቤተክርስቲያኗም ያለው የጸሎት ስነ ስርዓት የጋዛን ጥፋት የሚያስብ ነው።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው "የዘር ጭፍጨፋ ሳይቆም የገና በዓልን ለሁለተኛ ጊዜ ማክበር" ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ካህን አይዛክ ይናገራሉ።
"ውሳኔ ሰጭዎች ይህ እንዲቀጥል ፈቅደዋል። ለነሱ የፍልስጤማውያን ህይወት ትርጉም የለሽ ነው" ይላሉ።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ የእስራኤል ባለስልጣናት ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ባወረደ መልኩ የሚሰጧቸው ትርክቶች እንዲሁም እስራኤል ሆን ብላ ተቋማት ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች እና እልቂቶች በመነሳት የዘር ጭፍጨፋ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።
በተጨማሪም በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታውቆ ነበር።
እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ "ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው" ማለቷ ይታወሳል።
በቤተልሔም ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች ተስፋ መቁረጥ ተጫጭኗቸዋል። እየደረሰባቸው ያለውን "ግፍ" በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ችላ ማለታቸውን ያነሳሉ።
በእስራኤል ወረራ በተያዘችው ዌስትባንክ የምትገኘው የፍልስጤሟ ከተማ ቤተልሔም ነዋሪዎች በጦርነት እየወደመች ባለችው የጋዛ ከተማ ቤተሰቦች እና ወዳጆች አሏቸው።
"እናቴ በቴሌቪዥን የምንመለከተው ነገር በጋዛ እየሆነ ካለው አንጻር አንድ በመቶ እንኳን አያሳይም ብላ ነግራኛለች" ይላሉ የጋዛ ተወላጁ እና የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ዶክተር ዩሱፍ ክሁሪ።
ወላጆቹ እና እህቱ ባለፉት 14 ወራት ውስጥ በሁለት የጋዛ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው ካሉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ክርስቲያኖች መካከል ናቸው።
"እንደ መላው የጋዛ ሰርጥ ለረሃብ ተዳርገዋል። በማያቋርጥ የቦምብ ጥቃት እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ማንዣበብ እንቅልፍ አልባ ሌሊትን ያሳልፋሉ። የህክምና አገልግሎትም የላቸውም" ይላሉ፥።
"ወዳጆቻችን፣ ዘመዶቻችን አጥተናል"
እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
በጋዛ ካለው ጦርነት በተጨማሪ በዌስት ባንክ ውጥረት ነግሷል። እስራኤል በወረራ በተቆጣጠረቻት ዌስት ባንክ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ አዳዲስ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ጥላለች። በየቀኑ ለስራ ወደ እየሩሳሌም እና አይሁዳውያን ሰፈሮች ይመላለሱ ለነበሩ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ፈቃድ ሰርዛለች።
በቱሪዝም ላይ መሰረቱን ያደረገው የቤተልሔም ምጣኔ ሐብት እየተሽመደመደ ነው። ሌላ ጊዜ በስራ የሚወጠሩት አስጎብኚዎች እርግቦችን እየመገቡ ከልደታ ቤተ ክርስቲያን ጎን ቆመዋል።
"ቱሪስቶች ቢኖሩ፣ ሁሉም ሰዎች እንዲሁም ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ስራ አይፈቱም ነበር። ቱሪስቶች ከሌሉ በቤተልሔም ከተማ ውስጥ ምንም ህይወት የለም" ይላል አብዱላህ የተባለ አንድ አስጎብኚ።
"ገንዘብ የለኝም፣ ምንም ስራ የለም። ከአንድ ዓመት በላይ በቤታችን ነን" ሱል ስታር በተሰኘው ጎዳና ቅርስ በመሸጥ የሚተዳደረው አድናን ሱባህ።
ባሳለፍነው ዓመት በርካታ የአካባቢው ክርስቲያን እና ሙስሊም ቤተሰቦች ተሰድደዋል። ፍልስጤማውያን በራሳቸው መሬት ላይ በሚደርስባቸው ጥቃት፣ የእስራኤላውያን ሰፈራ መስፋፋት የወደፊቱን ዕጣ ፈንታቸውን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
ነገር ግን በቤተልሔም አንድ የማህበረሰብ ቡድን በዚህ ፈታኝ ወቅት ለውጥ ለማምጣት እየሞከረ ነው። ምግብ እና ሌሎች እገዛዎች ለሚያስፈልጋቸው ዕርዳታን እያቀረቡ ይገኛሉ።
ምንም አይነት መንግሥታዊ ዕርዳታ በሌለበት ሁኔታ በጎ ፈቃደኞቹ ከዲያስፖራው ጭምር መዋጮ ይሰበስባሉ።
"ገና የስጦታ፣ የፍቅር እና የደስታ መንፈስ የሚሰፍንበት ነው። በዚህ የዕርዳታ ዕሽግ በአካባቢያችን ላሉ ቤተሰቦች ደስታን እና ተስፋን እንደምንፈነጥቅ ተስፋ አድርገናል" ሲሉ ፍልስጤም ላየንስ ክለብ የተሰኘው ድርጅት ኃላፊ ዋኤል ሻኤር ይናገራሉ።