በጋዛ የቀሩት የመጨረሻው የአጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪም በእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ተገለጸ

በሰሜን ጋዛ የቀሩት የመጨረሻው ፍልስጤማዊ የአጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪም በእስራኤል ታንክ ጥቃት መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ገለጹ።

ዶክተር ሰይድ ጁዴህ ሕይወታቸው የተቀጠፈው ሐሙስ፣ ታህሳስ 3/ 2017 ዓ.ም. ወደ ስራ እየሄዱ በነበረበት ወቅት በተፈጸመባቸው ጥቃት ነው።

ዶክተሩ በሰሜን ጋዛ ውስጥ በሚገኙት ካማል አድዋን እና አል አውዳ ሆስፒታሎች በአጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪምነት ያገለግሉ ነበር።

የእስራኤል ጦር ስለ ግድያው አላውቅም የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነገር ግን እየመረመርኩ ነው ብሏል።

የዕድሜ ባለጸጋ እና አያት የሆኑት ዶክተሩ ጡረታ ወጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ጦርነቱን ተከትሎ ሕዝባቸውን ለማገልገል ነበር ወደ ስራቸው የተመለሱት።

ባለፈው ወር በከማል አድዋን ሆስፒታል ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት "አድኑን" የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ፖስተር ይዘው ነበር። ይህ ሳይሰራ ቀርቶ ዶክተሩ ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል።

"አንድ ታካሚያቸውን ለማየት ወደ አል አውዳ ሆስፒታል እየሄዱ በነበረበት ወቅት አንደኛው ታንክ በቀጥታ ተኩሶባቸዋል" ሲሉ የከማል አድዋን ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ሁሳም አቡ ሳፊያ ስለ አገዳደላቸው ተናግረዋል።

አክለውም "እንደ አለመታደል ሆኖ ወዲያውኑ ሕይወቱ ጠፋ" ብለዋል።

አንዳንድ የአይን እማኞች በበኩላቸው እስራኤል በድሮን ጥቃት ገድላቸዋለች ብለዋል።

እስራኤል የውጭ ጋዜጠኞች በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እንዲገቡ አትፈቅድም።

ቢቢሲ በእየሩሳሌም የሚገኘውን የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የጋዛ እርዳታ ማስተባበሪያ ባልደረባ የሆኑትን ሉዊዝ ዋቴሬጅን አነጋግሯል።

"ለቤተሰባቸው በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ነው። በተጨማሪም በሰሜናዊ ጋዛ በጥቂት ዶክተሮች ጥገኛ ለሆኑ ፍልስጤማውያን ፈታኝ ሁኔታን ፈጥሯል" ብለዋል።

"በጋዛ ሰርጥ ያሉ ሆስፒታሎች ሆስፒታል ብሎ መጥራት ይከብዳል" ይላሉ ሉዊዝ።

"ጽዳት የለውም፤ ዶክተሮች የሏቸውም ማለት ይቻላል። ምንም ዓይነት የሕክምና መሳሪያ የላቸውም። ታካሚዎች እየረገፉ ነው" ሲሉ ነው ለቢቢሲ የተናገሩት።

ሉዊዝ ዋቴሬጅ በጋዛ ያለውን ሰብዓዊ ሁኔታ "የዓለም መጥፋት" ስሜት እንዳለው ገልጸዋል።

እስራኤል በከባባ ውስጥ ያስገባቻትን ጋዛ የተቀናጀና የማያባራ ጥቃት እየፈጸመችባት ይገኛል።

ይህ ጥቃት በስፍራው እንደገና በተሰባሰቡ የሃማስ አባላት ላይ ያነጣጠረ ነው ትላለች እስራኤል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ የእስራኤል ባለስልጣናት ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ባወረደ መልኩ የሚሰጧቸው ትርክቶች እንዲሁም እስራኤል ሆን ብላ ተቋማት ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች እና እልቂቶች በመነሳት የዘር ጭፍጨፋ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታውቆ ነበር።

ባለፈው ዓመት 90 በመቶ የሚሆነው፣1.9 ሚሊዮን ሕዝብ ቀያቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ጋዛ 79 በመቶ የሚሆነው መሬቷም እስራኤል የማፈናቀል ትዕዛዝ ቁጥጥር ስር ያደረገችው እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

ይህ ሁኔታ" በግዳጅ ማፈናቀል" እንደሆነ የጠቀሰው የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት "ስልታዊ እና የመንግሥት ፖሊሲ" አካል እንደሆነ መረጃዎቹ መጠቋማቸውን አክሏል።

እስራኤል የፈጸመቻቸው ድርጊቶች የዘር ማጽዳት ጋር ተመሳሳይነት አለው ብሏል።

እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ "ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው" ማለቷ ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ44 ሺህ 875 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።