የሚሊኒየም አዳራሽ 18 ዓመታት - የዐቢይ እና ኢሳያስ መገናኘት፣ የቢዮንሴ ኮንሰርት፣ የኮቪድ ሕክምና ማዕከልነት

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የዛሬ 18 ዓመት ኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ለመቀበል ሽር ጉድ ስትል ነበር ሚሊኒየም አዳራሽ የተገነባው።

በጊዜያዊነት የተገነባው ሚሊኒየም አዳራሽ፤ ሁለት አሥርታት ለሚጠጋ ጊዜ በርካታ ሰዎች የሚታደሙባቸው ኹነቶች ዋነኛ ማዘጋጃ ሥፍራ ሆኖ ቆይቷል።

ሚሊኒየም አዳራሽ ከሙዚቃ ኮንሰርት እስከ ዐውደ ርዕይ፣ ከሃይማኖታዊ ክንውን እስከ ፖለቲከኞች ንግግር አስተናግዷል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከልነቱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን መያዝ በኋላ ወደ አገር ቤት የተመለሱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በአዳራሹ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከእነዚህም መካከል ጀዋር መሐመድ ይጠቀሳል።

አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለረዥም ጊዜ ተማሪዎቹን በድምቀት ያስመርቅ የነበረው በዚህ አዳራሽ ነበር።

ሚሊኒየም አዳራሽ፤ ልዩ በሆነ አጋጣሚ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን በሱዳን ሙዚቃ ሲደንሱም አሳይቶናል።

በ2017 ዓ. ም. በሚሊኒየም አዳራሽ መጠነኛ የእሳት አደጋ ተነስቶም ነበር።

በ20ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈው ሚሊኒየም አዳራሽ እስከ 25,000 ሰዎች እንደሚያስተናግድ ይነገርለታል።

የሚሊኒየም አዳራሽን የሚያስተዳድረው በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር የሚገኘው አዲስ ፓርክ ነው።

ሚሊኒየም አዳራሽ ፈርሶ እንደ አዲስ እንደሚገነባ ሚድሮክ ይፋ አድርጓል። መልሶ ግንባታው ለ32ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (ኮፕ27) የሚደረገው ዝግጅት አካል እንደሆነም ተገልጿል።

ለኮፕ32 የሚያገለግሉ ሆቴሎችን የማስፋፋት ዓላማ እንዳለው የገለጸው ሚድሮክ፤ በሚሊኒየም አዳራሽ የማርዮት ሞክሲ ሆቴልን እንደሚገነባ አስታውቋል።

ያለፉትን 18 ዓመታት መለስ ብለን በሚሊኒየም አዳራሽ የተከናወኑ ጉልህ ክንውኖችን ስንቃኝ ሦስት ማሳያዎችን መውሰድ እንችላለን።

ዐቢይ እና ኢሳያስ በሚሊኒየም

ከስምንት ዓመት ገደማ በፊት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአዲስ አበባ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ነበር።

መሰናዶው "የኢትዮ-ኤርትራ ሰላም ማብሰሪያ" መድረክ ተብሎ ተሰይሞ እንደነበር ይታወሳል።

ጦርነትም ሰላምም ሳይታይበት የቆየው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ተለውጧል።

አሁን ላይ አገራቱ ቢቃቃሩም በወቅቱ ሁለቱ መሪዎች የሞቀ ወዳጅነት ነበራቸው።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ ሲገኙ ከታዳሚዎች ከፍተኛ ድጋፍ ተችሯቸው ነበር።

ቢዮንሴ በሚሊኒየም

ቢዮንሴ ለኢትዮጵያ ሚሊኒየምን አዲስ አበባ ከተገኙ ገናና ድምጻዊያን አንዷ ናት። በሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው ኮንሰርት ወደ 5,000 ገደማ ሰዎች መታደማቸው ተገልጾ ነበር።

ከቢዮንሴ በፊት ዝነኛው ራፐር ሉዳክሪስ ሙዚቃውን አቅርቧል። ሰፊ ትኩረት ያገኘችው ግን ቢዮንሴ ነበረች።

ቢዮንሴ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አጠገብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መገኘቷ በርካቶችን ያነጋገረ ክስተት ነበር።

ቢዮንሴ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደማቅ አሻራ ካላቸው ድምጻዊያን መካከል በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።

በወቅቱ ዝነኛ የነበረው የአሜሪካው 'ብላክ አይድ ፒስ' የሙዚቃ ቡድን አርቲስቶች ኮንሰርታቸውን ያቀረቡት በዚሁ አዳራሽ ነበር።

ባለፉት ዓመታት በሚሊኒየም አዳራሽ አስቴር አወቀ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ መሐሙድ አሕመድ እና ሌሎችም አንጋፋ ድምጻውያን አቀንቅነዋል። ከአፍሪካውያን ድምጻውያን መካከል ዴቪዶ እና ፒ-ስኩዌር ይጠቀሳሉ።

የኮሮናቫይረስ ማዕከል የሆነው ሚሊኒየም አዳራሽ

ከስድስት ዓመት በፊት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሲከሰት ሚሊኒየም አዳራሽ ሕሙማንን አስተናግዷል።

የሚሊኒየም የኮቪድ-19 ማዕከል ዋና ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ውለታው ጫኔ በወቅቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ አዳራሹ ለጤና ሚኒስቴር በነጻ ከተሰጠ በኋላ ሥራ ጀምሯል።

አዳራሹ 200 ሜትር በ170 ሜትር ገደማ ስፋት ቢኖረውም ለሕክምና አገልግሎት የተዘጋጀ አለመሆኑ ፈታኝ እንደነበር ዶክተሩ ገልጸዋል።

በሒደት የሕሙማን ለይቶ ማቆያ ክፍሎች በማዘጋጀት ሕክምና ተሰጥቷል። አዳራሹን እንደ ተለዋጭ ሆስፒታል ሲጠቀሙ መነሻ አድርገው የወሰዱት ኒው ዮርክ እና ጣሊያንን እንደነበር ተናግረዋል።

በቫይረሱ ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከቫይረሱ ማገገም የቻሉ ሰዎች ከሚሊኒየም አዳራሽ ሲወጡ የሕክምና ባለሙያዎች ያደርጉላቸው የነበረው ሽኝት የሚዘነጋ አይደለም።

የሚሊኒየም ትውስታ በምሥል