የቦትስዋና ፕሬዝዳንት 20 ሺህ ዝሆኖችን ወደ ጀርመን እልካለሁ ሲሉ አስጠነቀቁ

በቦትስዋ እና በጀርመን መካከል የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት 20 ሺህ ዝሆኖችን ወደ ጀርመን እልካለሁ ሲሉ አስጠነቀቁ።

በቦትስዋና እና በአውሪፓዊቷ አገር መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ከጥቂት ወራት በፊት የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ወደ አገሩ በሚገባ በአደን የተገኘ የእንስሳት አካል ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር መደረግ አለበት ካለ በኋለ ነው።

የዝሆኖች ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረባት ቦትስዋና ለመዝናኛነት ለአደን ከሚመጡ ጎብኚዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከማግኘቷ በተጨማሪ የዝሆን ቁጥርን ለመገደብ ጥሩ አማራጭ ሆኖኛል ትላለች።

አንድ መንግሥታዊ ያልሆ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአፍሪካ ከሚደረጉ የመዝናኛ አደን ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ጀርመናውያን ናቸው።

የጀርመን የአካባቢ ሚኒስቴር አስተያየት ያበሳጫቸው የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት ሞከገዌትሲ ማሲሲ፣ ቢልድ ለተባለ የጀርመን ጋዜጣ ሲናገሩ “እኛን እየተናገራችሁ እንዳላችሁት እናንተም ከዝሆን ጋር መኖር አለባችሁ” ካሉ በኋላ 20 ሺህ ዝሆኖችን እልካለሁ ሲሉ አስፈራርተዋል።

የጀርመን መንግሥት አስተያየት የቦትስዋና ዜጎችን ከማደህየት ወጪ ሌላ ትርጉም የለውም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ቦትስዋና የዝሆን ቁጥርን ለመጨረመር ባለፉት ዓመታት ያካናወነችው የጥበቃ ሥራ ውጤማ አድርጓት አገሪቱ ከጠበቀችው በላይ የ130 ሺህ ዝሆኖች መኖሪያ ሆናለች።

ዝሆኖች የተለያዩ ንብረቶችን ከማውደማቸው በላይ ማሳ ላይ ያለ ሰብልን በመብላት ጉዳት ያደርሳሉ። ከሰው ልጆች ጋር በሚፈጠር ግጭትም ዜጎች ሕይወታቸውን እያጡ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል።

የዝሆኖች ብዛት በበረከተባት ቦትስዋና የእንስሳቱን ቁጥር ለመቀነስ ዝሆኖችን ወደ ጎረቤት አገራት ስትልክ ቆይታለች።

ከዚህ ቀደም 8 ሺህ ዝሆኖችን ለአንጎላ አበርክታ ነበር። ለሞዛምቢክም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖችን ለመስጠት ጥያቄ አቅርባለች።

ከዚህ በተጨማሪም ለቤት እንስሳት ምግብነት የሚውል የዝሆን ሥጋ ለማቅረብም አማራጭ አቅርባም ነበር።

ፕሬዝዳንት ማሲሲ “ለጀርመን ዝሆን በስጦታ መልክ መስጠት እንፈልጋል” ካሉ በኋላ ንግግራቸው ቀልድ አለመሆኑን እና ጀርመን አልፈልግም ብትል እንኳ እንደማይቀበሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቦትስዋና አሁን ላይ በየዓመቱ ለመዝናኛነት ተብለው የሚታደኑ ዝሆኖችን ኮታ የምታወጣ መሆኑን እና ይህም ለአካባቢው ማኅብረሰብ የገቢ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

የቦትስዋና ፕሬዝዳንት አስተያየትን ተከትሎ የጀርመን የአካባቢ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለአካባቢ ጥበቃ ሲባል ጀርመን በሚገቡ የአደን ውጤት በሆኑ የእንስሳት አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች ብለዋል።

አውስትራሊያ፣ ፈንሳይ እና ቤልጂየም የአደን ውጤት የሆኑ የእንስሳት አካላትን ወደ አገር ማስገባት ከሚከለክሉ አገራት መካከል ይገኙበታል።