ባለፉት ዓመታት በእስራኤል ከተገደሉ የኢራን ተመራማሪዎች እና የጦር መኮንኖች ዋነኞቹ

እስራኤል ጠላቶቼ ከምትላቸው መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች - ኢራን። ኢራንም ብትሆን ‘አጥፊዬ’ ከምትላቸው አገራት መካከል ቀን ከሌት በዐይነ ቁራኛ የምትጠብቃት እስራኤልን ነው።

በእርግጥም ኢራን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ የእስራኤል ከመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከምድር ገጽ ላይ እንድትጠፋ ፍላጎት እንዳላት በመሪዎቿ አማካይነት በይፋ ከመናገር አትቆጠብም።

ለዚህ ደግሞ ሰላም በራቀው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ እና እስራኤልን በጠላትነት ከፈረጇት ዋነኛ ታጣቂዎች መካከል አብዛኞቹን ትደግፋለች፣ ታስታጥቃለች።

ከጋዛ ተነስቶ ድንገተኛ እና አደገኛ ጥቃት የፈጸመባት እንዲሁም ይህንን ተከትሎም እስራኤል ድምጥማጡን ሳላጠፋ አላርፍም በማለት ጦርነት ውስጥ ያስገባት ሐማስ የኢራን የቅርብ ወዳጅ ነው።

ጊዜ እና አጋጣሚን ጠብቀው አድፍጠው የሚጠብቋት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና የየመን ሁቲዎችም በኢራን የሚደገፉ ኃይሎች ናቸው። ስለዚህም በዙሪያዋ እንቅልፍ የሚነሷት ጠላቶቿን የምትደግፈውን ኢራንን እስራኤል እንዲሁ በቸልታ አይታት አታውቅም።

የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት የሚነገርላት ኢራን ከምትደግፋቸው ታጣቂዎች በላይ ለእስራኤል ስጋት ናት። ስለዚህም ባገኘችው አጋጣሚ እና ቦታ እዚው ኢራን ግዛት ውስጥ ሳይቀር ባለሥልጣናቷን እና የጦር መሪዎቿን ኢላማ ስታደርግ ቆይታለች።

በዚህም ምክንያት ባለፉት ዓመታት ኢራን የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድን በወታደራዊ መስክ ጥቂት የማይባሉ የጦር አዛዦችን እና ውድ የሆኑ የኑክሌር ተመራማሪዎቿን በመግደል ተጠያቂ ስታደርግ ቆይታለች።

በተለይ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረባት እስራኤል፣ የኑክሌር ግንባታ ሂደቷን ለማዳከም ከተቻለም ለማደነቀፍ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በርካታ ኢራናውያን የኑክሌር ተመራማሪዎችን ገድላለች።

የእስራኤል መንግሥት ኢራን ለህልውናው ስጋት መሆኗን ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ አንስቶ ባገኘው አጋጣሚ በተደጋጋሚ ከመግለጽ ባሻገር ስለወሰደው እርምጃ በይፋ ሲያምን ተሰምቶ አየውቅም።

አስካከሁን በኢራን ሳይንቲስቶች እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ እስራኤል ኃላፊነቱን ባትወስድም ዓለም ሁሉ ዋነኛ ተጠርጣሪ የሚያደርጋት እርሷን ነው።

ባለፉት ዓመታት ከተገደሉ የኢራን የኑክሌር ሳይንቲስቶች እና የጦር መኮንኖች መከካል ጥቂቶቹን እነሆ፡

መሱድ አሊሞሐማዲ

ሁለቱም በይፋ ባያምኑም እስራኤል እና ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት አገራት እንደሆኑ በስፋት ይነገራል። በዚህም ምክንያት ሁለቱም በዐይነ ቁራኛ የሚተያዩ አገራት ናቸው።

አሜሪካ እና ምዕራባውያን የኢራንን የኑክሌር ግንባታ ለማስቆም የመንግሥቱ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ጫናዎችን ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። እስራኤል በበኩሏ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ በስላለ ተቋማተቷ አማካይነት የኢራንን የኑክሌር ግንባታ ለማደናቀፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም።

ከዚህ የእስራኤል ጥረት ውስጥ የኑክሌር ግንባታ በሚካሄድባቸው ስፍራዎች እና ማዕከላት ላይ የበይነ መረብ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎችንም እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።

በተጨማሪም አገሪቱ ካሏት እጅግ ውስጥ ከሆኑ የኑክሌር ሳይንቲስቶች መካከል እጇ ላይ የወደቁት ላይ ጥቃትን በመፈጸም እስከ መግደል ደርሳለች።

እስራኤል ኢራናውያን ተመራማሪዎችን ዒላማ ማድረግ ስትጀምር ቀድመው ከተገደሉ የኒውክለር ሳይንስ አዋቂዎች መካከል አንዱ መሱድ አሊሞሐማዲ ነው።

ይህ እውቅ የኳንተም ፊዚክስ ምሁር ከቴህራን ወጣ ብሎ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ ነበር 2010 (እአአ) መጀመሪያ ላይ የተገደለው።

በስመ ጥሩ ቴህራን ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የነበረው አሊሞሐማዲ ለሥራ ከቤቱ እየወጣ ሳለ ነበር ከርቀት ቁጥጥር የሚደረግበት መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ሕይወቱ ያለፈው።

በወቅቱ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፊዚክስ ምሁሩ ግድያ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባቸውም።

ማጂድ ሻህሪአሪ

ከአሊሞሐማዲ ግድያ በኋላ እስራኤል በዐይነ ቁራኛ ትከታተለው የነበው የኑክሌር ሳይንስ ባለሙያው ማጂድ ሻህሪአሪ ነበር።

ሻሂድ ባሄሽቲ በተባለ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረው ሻህሪአሪ፤ ልክ እንደ አሊሞሐማዲ ሁሉ ወደ ሥራ ለማቅናት ከመኖሪያ ቤቱ እንደወጣ ነበር መኪናው ላይ ተጠምዶ በጠበቀው ቦምብ የተገደለው።

ማጂድ ሻህሪአሪ ከዩኒቨርሲቲ መምህርነቱ በተጨማሪ ስሙ ከኢራን የኒውክላር ማብለያ ጣቢያ ጋር አብሮ ይነሳ ነበር።

ኢራን በማን እንደተፈጸመ ባልታወቀው የቦምብ ጥቃት ለተገደለባት የኑክሌር ሊቅ ሻህሪአሪ ሞት እስራኤልን ብቸኛዋ ተጠያቂ አድረጋት ነበር።

ይህ ዩኒቨርሲቲ የኒውክላር ሳይንስ መምህር በኢራን የኒውክለር ፕሮግራም ውስጥ ኃላፊነት እንዳለው ሕይወቱ ባለፈበት ወቅት ተገልጿል።

ሜ ጄኔራል ሐሰን ቴህራኒ ሞግሃዳም

ምዕራባውያኑ “ሚሳኤሉ ሰውዬ” የሚል ቅጽል ስም የሰጧቸው ሜ/ጄ ሐሰን ቴህራኒ ሞግሃዳም፣ ቴህራን አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታ ባስከተለ ጥቃት ነበር እአአ 2011 ማብቂያ ላይ የተገደሉት።

ሞግሃዳም ሜጀር ጀነራል ብቻ ሳይሆን በሙያቸው መሃንዲስ ነበሩ። እኚህ ጄኔራል በቻይና እና በሰሜን ኮሪያ በባሊስቲክ ሚሳኤል ሳይንስ ትምህርት ቀስመው ወደ አገራቸው የተመለሱ ነበሩ።

ኢራን ለጥቃቱ ሞሳድን ተጠያቂ ባድረገችበት ጥቃት ከሜጀር ጄኔራል ሞግሃዳም ጋር አብረው የነበሩ 17 የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂዎችም ተገድለው ነበር።

የከፍተኛ ጦር መኮንኑ ግድያ ኢራንን በእጅጉ ነበር ያስቆጣት። በቀብራቸው ላይም የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ተገኝተው ነበር።

በጄኔራሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የወቅቱ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን ሳላሚ ሟቹን “የአብዮቱ የሚሳኤል ኃይል መሃንዲስ ነበረ” ሲሉ ገልጸዋቸው ነበር።

ሞህሰን ፋክሪዛሄድ

በአውሮፓውያኑ 2020 በጉምቱው የኑክሌር ሳይንስ ተመራማው ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ላይ የተፈጸመው ግድያ ብዙ ያነጋገረ ነበር።

የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ ይህን ተመራማሪ ለመግደል ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ሳይሳካሉት ቆይተው፣ ከአራት ዓመታት በፊት ከኢራን መዲና ቴህራን ወጣ ብሎ ከሚገኝ ስፍራ ፋክሪዛሄድን የመግደል ውጥኑ ሰምሮለታል።

ፋክሪዛሄድ በተገደሉት ወቅት በኢራን መከላከያ ኃይል ውስጥ የምርምር እና ፈጠራ ክፍል መሪ ነበሩ። ይህም ግለሰቡን እስራኤል በእጅጉ ከምትፈራው የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ጋር በጥብቅ ያስተሳስራቸዋል።

እንደሚነገረውም ሞሳድ እኒህን ግለሰብ ለመግደል የረቀቀ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ከርቀት ቁጥጥር የሚደረግበት የጦር መሳሪያን ጥቅም ላይ አውሏል።

ኢራን ለእኚህ ተመራማሪ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባትም ነበር። እስራኤል እንደተለመደው መሰል ጥቃቶችን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

በሳይንቲስቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ኃላፊ ግድያው የተፈፀመው ማንም ሰው በሌለበት እና ኤሌትሮኒክ በሆነ መንገድ ነው ብለው ነበር።

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራምን በበላይነት በመምራት የሚታወቁትን ተመራማሪ የገደሉትን እንደሚበቀሉ ዝተው ነበር።

ብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ ሬዛ ዛሄዲ

ኢራን በጠላቶቿ ዒላማ የሚደረጉባት የኑክሌር ባለሙያዎቿ ብቻ አይደሉም። ከፍተኛ የጦር መኮንኖቿም በተለያዩ አጋጣሚዎች እና ቦታዎች እንዲሁ እንደወጡ ቀርተውበታል።

እነዚህ የጦር ጄኔራሎቿ ኢላማ የሚደረጉት በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም ጭምር ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው ሁለቱን አገራት በጠላትነት ፈርጀው ጥቃት የሚሰነዝሩባቸውን ታጣቂ ቡድኖችን በማስታጠቅ እና በመደገፍ ስለሚከሷቸው ነው።

እስራኤል እና ምዕራባውያን አገራት በኢራቅ፣ ሊባኖስ፣ በየመን፣ በሶሪያ እና በሌሎችም የአካባቢው አገራት ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ቡድኖች ለዓለም ሰላም ጠንቅ ናቸው ይሏቸዋል። በዚህ ምክንያትም ከታጣቂ ቡድኖቹ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የኢራን ጄኔራሎች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።

ከእነዚህ መካከል ባለፈው ሰኞ ሶሪያ ውስጥ በሚገኝ የኢራን ቆስላ ላይ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዥ የነበሩት ብርጋዲዬር ጄኔራል መሐመድ ሬዛ ዛሄዲ ተገድለዋል።

ምንም እንኳ እስራኤል ጥቃቱን በተመለከተ እስካሁን ያለችው ነገር ባይኖርም በሶሪያ መዲና ደማስቆ በሚገኘው የኢራን የቆንስላ ሕንጻ ላይ እስራኤል ፈጽማዋለች በተባለ ጥቃት ሰባት የኢራን የአብዮታዊ ዘብ አባላት ተገድለዋል።

ከሟቾቹ መካከል የአብዮታዊ ዘብ አንድ ክንፍ የሆነው የቁድስ ኃይል ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ብርጋዲዬር ጄኔራል መሐመድ ሬዛ ዛሄዲ እና ምክትላቸው ብርጋዲየር ጄኔራል ኦሐመድ ሐዲ ሐጂ ራሒም እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።

ሶሪያ እነዚህ ከፍተኛ የጦር አመራር የተገደሉት የኢራን ቆንስላ በእስራኤል ጦር አውሮፕላን ከተመታ በኋላ ነው ብላለች።

የ63 ዓመቱ ዛሄድ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ መሪ ከሆኑት ከፍተኛ ጄኔራሎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ በሊባኖስ እና ሶሪያ ከአውሮፓውያኑ 2008 እስከ 2016 ድረስ አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።