ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሩሲያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ አወጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በዩክሬን ውስጥ ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች ሰበብ በከፍተኛ የሩሲያ የጦር አዛዦች ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ።
ፍርድ ቤቱ በስም የጠቀሳቸው የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሩሲያ ጦር ሌፍተናንት ጄኔራል ሰርጌይ ኮቢላሽ እና የባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑት አድሚራል ቪክቶር ሶኮሎቭ ናቸው።
ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በሩሲያ ባለሥልጣናት ላይ የእስር መዘዣ ሲወጣ ይህ ሁለተኛው ነው።
የመጀመሪያው የፍርድ ቤቱ መያዣ ትዕዛዝ የወጣው በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአገሪቱ የህጻናት መብቶች ባለሥልጣን ላይ ነው።
ነገር ግን ሩሲያ ለፍርድ ቤቱ ዕውቅና ስላልሰጠች እነዚህ ባለሥልጣናት ወደ ችሎቱ የመቅረብ ዕድላቸው እውን የሚሆን አይደለም።
በጦር አዛዦቹ ላይ አሁን የወጣው የእስር ማዘዣ “የሚመሩት ሠራዊት በዩክሬን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ለፈጸመው ጥቃት” ተጠያቂ ናቸው የሚል ምክንያታዊ የሆነ መነሻ በመኖሩ ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ።
በከፍተኛ መኮንኖቹ ትዕዛዝ ተፈጽመዋል የተባሉት ወንጀሎች ካለፈው ዓመት ጥቅምት አስከዚህ ዓመት ጥቅምት የተፈጸሙ መሆናቸውንም ፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
ጨምሮም በጥቃቶቹ በሰላማዊ ሰዎች እና በንብረት ላይ የደረሱት ጉዳቶች ከፍተኛ ናቸው ሲልም የጦር አዛዦቹን ከሷል።
ሁለቱ ግለሰቦች “እያንዳንዳቸው በሰላማዊ ሰዎች መገልገያዎች ላይ ላነጣጠሩ የጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው” በማለት “ኢሰብአዊ ድርጊቶች እና በሰብአዊነት ላይ ወንጀል እንዲፈጸም” ምክንያት ናቸው ብሏል።
የ58 ዓመቱ ሌፍተናንት ጄኔራል ሰርጌይ ኮቢላሽ የቀረበባቸው ወንጀል በተፈጸመበት ጊዜ የሩሲያ አየር ኃይል የረጅም ርቀት የአውሮፕላኖች ቡድን አዛዥ ነበሩ።
የ61 ዓመቱ አድሚራል ቪክቶር ሶኮሎቭ ደግሞ ክሱ ላይ በተጠቀሰው ጊዜ የሩሲያ ባሕር ኃይል የጥቁር ባሕር ቡድንን ያዙ እንደነበር ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ገልጿል።
ሩሲያ ከዚህ በፊት ሠራዊቷ በዩክሬን ውስጥ የሚገኙ የሰላማዊ ሰዎች መገልገያዎችን ዒላማ እንደማያደርግ አስተባብላ ነበር።
ለሁለት ዓመት ከሩሲያ ጋር በጦርነት ውስጥ የምትገኘው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ፍርድ ቤቱ ያወጣውን የእስር ትዕዛዝ በውንታዊ ብለውታል።
ፕሬዝዳንቱ “በዩክሬን ሰላማዊ ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙ ሁሉም የሩሲያዊ የጦር አዛዦች ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ሊያውቁ ይገባል” በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
“እንዲህ ዓይነቶቹን ወንጀሎች የፈጸሙ ሁሉም ሰዎች ተጠያቂነት እንደሚኖር ማወቅ አለባቸው” ብለዋል።
ከሃያ ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት በተደረሰ ስምምነት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አገራት ጣልቃ መግባት እና ለፍርድ ማቅረብ በማይችሉባቸው የወንጀል ሁኔታዎች ጣልቃ እንዲገባ የተመሠረተ ነው።
በዚህም የዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎችን ፍርድ ቤቱ እንዲመረምር እና ተጠያቂዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ይህንን ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን የመሠረተውን ስምምነት 123 አገራት ተቀባይነት ሰጥተው ያጸደቁት ሲሆን፣ ሩሲያን ጨምሮ ቻይና፣ ሕንድ እና አሜሪካ ግን ፍርድ ቤቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አልሆኑም።
የዛሬ ዓመት ገደማ ፍርድ ቤቱ በፕሬዝዳንት ፑቲን እና የሩሲያ የህጻናት መብቶች ኮሚሽነር በሆኑት ማሪያ ልቮቫ-ቤሎቫ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ነበር።
ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ባለሥልጣናት ላይ ያቀረበው ክስ ከሕግ ውጪ ህጻናትን ከዩክሬን ወደ ሩሲያ እንዲጋዙ አድርገዋል የሚል ነው።
ሩሲያ ግን በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ ላይ በፍርድ ቤቱ የቀረበውን ክስ እና የወጣውን የእስር ማዘዣ እንደማትቀበለው በመግለጽ ውድቅ አድርጋለዋለች።












