ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሰናል 5 ሲያስቆጥር፤ ዩናይትድ በዴ ሂያ ጥረት 3 ነጥብ ይዞ ወጥቷል
ትናንት በተከናወኑ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
አርሰናል በኢሚሬትስ ስታዲየም በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መጨረሻ ላይ የሚገኙትን ኖቲንግሃም ፎረስተን አስተናግደው አምስት ጎሎዎችን አከናንበዋቸዋል።
ገብርኤል ማርቲኔሊ፣ ሪስ ኔልሰን፣ ቶማስ ፓርቴ እና ማርቲን ኦዴጋርስ ለአርሰናል ጎል ያስቆጠሩ ተጨዋቾች ናቸው።
መድፈኞቹ በድንቅ የጨዋታ ብቃት ያገኙት ሦስት ነጥብ በ31 ነጥቦች በሊጉ መሪነት እንዲቀጥሉ አስቸሏቸዋል።
የመጀረሚያውን ጎል ለገርኤል ማርቲኔሊ አመቻቸቶ ያቀበለው ቡካዮ ሳካ በመጀመሪያው አጋማሽ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ ወጥቷል።
ቡካዮ ሳካ ያጋጠመው ጉዳት ዝርዝር ይፋ ባይደረግም ተጨዋቹን ከኳታር የዓለም ዋንጫ የሚያስቀረው አይሆንም ሲሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የአርሰናል ቁልፍ ተጫዋች የሆነው የ21 ዓመቱ ቡካዮ ሳካ፤ በጋርዝ ሳውጌት ቡድን አባል በመሆን ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወደ ኳታር ያቀናል ተብሎ ይገመታል።
የ14ኛው ሳምንት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች የተጠናቀቁት በማንችስተር ዩናይትድ እና ዌስት ሃም ግጥሚያ ነበር።
ማርከስ ራሽፎርድ ለማንስተር ዩናይትድ ያስቆጠራት 100ኛ ጎል ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲሰበስብ አስችላለች።
ከራሸፎድ ጎል እኩል የግብ ጠባቂው ዴቪድ ዴ ሂያ ድንቅ አቋም ክለቡ ሦስት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል።
ዴቪድ ዴ ሂያ በጨዋታው ማጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ የዌስት ሃም ተከላካዩ ከርትስ ዙማ የጭንቅላት ኳስ እንዲሁም የሚካሂል አንቶኒዮን እና የደክለን ራይስ ጠንካራ ምት
ግብ ጠባቂው ይህን አቋም ያሳየው በኳታር የዓለም ዋንጫ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን አለመመረጡ በስፋት ከተዘበ በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት በርካታ የሰፔን ጋዜጦች ዴ ሂያበእግሩ መጨዋት አይችልም በሚል በአሰልጣኝ ሉዊስ ኤነሪኬ ስብስብ ውስጥ አለመካተቱን ዘግበዋል።
የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከዴ ሂያ ይልቅ የብራይተኑን ሮበርት ሳንቼዝ፣ የብሬንት ፎርዱን ዴቪድ ራያ እና የቼልሲውን ኬፓ አሪዛባላጋን ይዘው ወደ ኳታር እንደሚያቀኑ የአገሪቱ ጋዜጦች በስፋት ዘግበዋል።
የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ግን የግብ ጠባቂ ዋነኛ ስራ ጎል እንዳይቆጠር ማድረግ እንጂ በእግር የመጫወት ችሎታ አይደለም ሲሉ ግብ ጠባቂያቸውን ተከላክለዋል።
“ሁሉም የራሱ አመለካከት አለው ለእኔ ግን ለግብ ጠባቂ የመጀመሪያው ነገር ጎሎች እንዳይቆጠሩ መከላከል ነው” ብለዋል።
በሳምንት 375ሺህ ፓወንድ የሚከፈለው ዴ ሂያ የዓለማችን ከፍተኛ ተከፋዩ ግብ ጠባቂ እንደሆነ ይታመናል።