ሳይንስ ያዳላል? ጥቂት በሴቶች ጤና ላይ ስለሚስተዋለው ኢ-ፍትሃዊነት

ሳይንስን ስናስብ ተጨባጭ፣ በምርምር፣ በሙከራዎች እና በመረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ድምዳሜዎች ላይ መድረስ ይታሰባል።

ነገር ግን ሳይንሳዊ ሙከራዎች የሚደረጉት በሰዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አንፃራዊ ናቸው።

ይህም ሁኔታ በሳይንስ ውስጥ መድልዎ እንዲሰፍን በማድረግ በሰዎች ጤና ላይ ተፅእኖን እያሳረፈ መሆኑን በዓለም አቀፍ የጤና የበጎ አድራጎት ድርጅት የእኩልነት፣ ልዩነት እና አካታችነት መሪ የሆነት ዶ/ር ሊሊያን ሃንት ያስረዳሉ።

በሳይንስ ውስጥ ያለው መድልዎ በዓለም ሕዝብ ፆታ፣ ዘር ወይም በሚኖሩበት ቦታ ምን ያህል ተፅእኖ ያሳርፋል የሚለውን እንመለከታለን።

“የመኪና አደጋ ደኅንነት ለወንዶች ብቻ?”

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወንዶች ከሴቶች በበለጠ የመኪና አደጋ የመጋለጥ ዕድል አላቸው።

ነገር ግን አንዲት ሴት የመኪና አደጋ ከደረሰባት መውጫ የማጣት ዕድሏ ከፍተኛ ነው ይላል በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የተደረገ ጥናት።

የፕሊማውዝ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ያሉ ዶክተሮች በዩኬ በአውሮፓውያኑ 20012- 2019 ወደ ድንገተኛ ማዕከላት የገቡ ከ70 ሺህ በላይ ከመኪና አደጋ የተረፉ ሰዎችን መረጃ አጥንተዋል።

ምንም እንኳን አደጋዎች የሚያጋጥሙት በአብዛኛው በወንዶች ላይ ቢሆንም ሴቶች ባጋጠማቸው አደጋ 16 በመቶ መውጫ ያጡ ሲሆን የወንዶች ደግሞ 9 በመቶ ነው።

ለዚህም ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ በመኪና ደኅንነት ላይ የሚደረጉ መሞከሪያ አሻንጉሊቶች ከወንዶች የሰውነት አንፃር የተገነቡ እና የሴቶችን አካል ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ መሆኑን ከጥናቱ ተባባሪዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ላውረን ዊክስ ያስረዳሉ።

“የሴቶች ዳሌ በየትኛውም ቁመት እና ክብደት ከሚገኙ ወንዶች በጣም ሰፊ እንደሆነ እናውቃለን። የመኪና አደጋን ለመከላከል በሚል መሞከሪያ የሚያደርጓቸው አሻንጉሊቶች ለአካለ መጠን ከደረሰች ሴት ይልቅ የ12 ዓመት ታዳጊን ነው የሚያሳየው” ይላሉ።

ጥቁሮች ችላ የተባሉባቸው ዘርፎች

በመላው ዓለም ስለ ቆዳ በሽታ ምንነት የህክምና ተማሪዎችን ለማስተማር የሚያገለግሉ የመማሪያ መጻህፍት ጥቁር ወይም ጠየም ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸውን ሰዎች ችላ ብለዋቸው ቆይተዋል።

ማሎን ሙክዌንዴ የተባለ የዩኬ ጥቁር የህክምና ተማሪ በዚህ ሁኔታ በመሰላቸት ከሁለት ዓመታት በፊት ጥቁር እና ጠየም ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎችን የቆዳ ህመም ምልክት የሚያሳዩ 'ማይንድ ዘ ጋፕ' የተባለ መመሪያም እንዲያሳትም ምክንያት ሆኗል።

በወቅቱም ማሎን “በአሁኑ ጊዜ በህክምና ትምህርት ውስጥ ለነጭ ቆዳ የሚያደላ ሁኔታ አለ። ይህም ሁኔታ እኔን እና እኔን የመሰሉ ሰዎችን ያገላል። የወደፊቱ የህክምና ባለሙያዎች እንደመሆናችንም ይህ ሁኔታ የታካሚዎችን ሁኔታ እንዳይጎዳ እነዚህን ልዩነቶች ልብ ልንላቸው ይገባል” በማለት በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

በተመሳሳይ መልኩ የአዕምሮ ምርምር ለማድረግ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውለው ቴክኖሎጂ ሹሩባ፣ አፍሮ ፀጉር፣ ቁጥርጥር ወይም ከርደድ ያለ ፀጉር ባላቸው ሰዎች በጥሩ ሁኔታ አይሰራም። ይህም ሁኔታ የአፍሪካ ዝርያ ያላቸውን ሕዝቦች በሙሉ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያገል ነው።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የግሮቨር ላብራቶሪ ሳይንቲስቶች ይህንን ችግር ለመቅረፍ አዲስ ዘዴ ፈጥረዋል።

ግን እነዚህ መፍትሄዎች የመጡት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው።

የመጀመሪያዋ ሴት የሰውነት አካላት መማሪያ 3ዲ ሞዴል

የአናቶሚ ተማሪዎች የሴቶችን ውስጣዊ አካል ለመማር በነጭ ወንድ አካላዊ መንገድ የተሰራን የኮምፒውተር ባለሦስት አውታር [3ዲ] ሞዴልን መመልከትና ማጥናት አለባቸው።

ኤልሴቪየር የተባለ የጤና ምርምር ኩባንያ ይህንን ለመለወጥ በሚያደርገውም ጥረት የመጀመሪያዋን ሴት 3ዲ የአናቶሚ ሞዴል ከወራት በፊት አውጥቷል።

“ከዚህ በፊት የአናቶሚ ትምህርት በወንዶች አካል ላይ ላይ የተመሰረተ ነበር። ከዚያም ሴቶች ከወንዶች በተለየ ያላቸው አካላት እንደ እንግዳ አይነት እንዲጨመሩ ተደርገው ነበር ትምህርቱ ሲሰጥ የነበረው” በማለት አዲስ ሞዴል ተግባር ላይ የዋለበት የራይተን እና ሰሴክስ ሜዲካል ትምህርት ቤት የአናቶሚ ፕሮፌሰር የሆኑት ክሌር ስሚዝ ተናግረዋል።

“የሴቷ የአካል ቅርፅ በተፈጥሮው ትንሽ ቀጠን ይላል። አሁን በተሰራችው ሞዴል በጣም የተወሳሰበውን የሴት ዳሌ፣ ማህጸንና ውስጣዊ አካላትን ዝርዝር ሁኔታ ማየት በጣም አስደናቂ ነው። የሠራናት ሞዴል በወንድ ዳሌ ውስጥ ማህፀን ማስገባት ብቻ አይደለም” ይላሉ።

የህክምና ተማሪዋ ያስሚን ይህች አዲሷ ሞዴል በህክምናው ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ታመጣለች ትላለች፣ ምክንያቱም ሴቶች የህክምና መማሪያ መጻህፍ እንደሚስሏቸው ትናንሽ ወንዶች አይደሉም ።

 የሴቶች ጤና ያልተጠናና ምርምሩም ገንዘብ የለውም

በሳይንስ ውስጥ ያለው አድሏዊነት ሴቶችን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ለይቶ የሚጎዳበት ምክንያት “የሴቶች ጤና በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ ስለማይደረግለት እና ያልተጠናም በመሆኑ ነው” ሲሉ ዶክተር ሃንት ያስረዳሉ።

“የሴቶች ጤና ላይ እክል የሆኑ በርካታ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጥናቶች መደረግ አለባቸው። ለረጅም ጊዜ ችላ በተባሉ ለምሳሌም ያህል በወሊድ ዙሪያ፣ በወር አበባ ላይ ምርምር ሊደረግ ሊደረግ ይገባል” ይላሉ።

ለሴቶች ጤና ገንዘብ አለመኖርና ጥናት አለመደረግ ዋነኛው ምክንያት ሥልጣንና ገንዘብ ነው ብለው ያምናሉ።

“ለዚህ በዋነኝነት ምርምርን የሚቆጣጠረው ማን ነው? ምርምር ለማድረግስ ገንዘብ ያለውስ ማን ነው? እነዚህን መመለስ ከቻልን ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሁኔታዎች እነዚህ አካላት ቅድሚያ መሰጠት አለባቸው ብለው የሚያስቡትን ነው” በማለት ያስረዳሉ።

የሚኖሩበት ቦታስ ምን ያህል ተፅእኖ ያደርሳል?

በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በጥቂት አገራት የተጠናው ሳይንስ በዓለም ላይ የመንግሥት ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን ለማውጣት መነሻ ሆኗል በማለት ዶ/ር ሃንት እንደ ምሳሌ ይጠቅሱታል።

በእነዚህ አገራት በተሰሩ ጥናቶች መሠረት ፖሊሲዎች ተቀርጸው በሁሉም ቦታ ተፈጻሚ ሆነዋል።

ዊርድ (WEIRD) የሚለው ምህጻረ ቃል ምዕራባውያን፣ የተማሩ፣ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ፣ ሀብታም እና ዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰቦችን ለማመልከት የሚያገለግል ነው።

እነዚህ ማኅበረሰቦች ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 12 በመቶ ያነሱ ናቸው፤ ነገር ግን በሳይንሳዊ ጥናቶች ውስጥ 80 በመቶውን ይወክላሉ።

“እነዚህ ሃብታም የተሰኙት አገራት በምርምሮች ላይ ኢንቨስት ለማድረግና የምርምር አጀንዳዎችን የሚቀርጹ ናቸው። በዚህ አስፈላጊ የሆነው ጥናት ምንድን ነው? ምን መጠናት አለበት? የሚለውን በዋናነት ደረጃቸውን ይወስናሉ” ይላሉ ዶክተር ሃንት።

“ከእነዚህ አገራት የመጡት ፖሊሲዎች የሆነ ሰው አይነት ነህ በሚል እሳቤ ላይ ተመርኩዘው ነው የተቀረጹት። የተለየ የጤና ሁኔታ ካላችሁ ምናልባት አካላዊ ርቀት ወይም ማስክ ማድረግ ብቻ ወረርሽኙን መከላለል ይቻል ነበር። ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ተጓዳኝ እክሎች ያለባቸው ይህ ሁኔታ ለእነሱ አልነበረም።”

“በቤታችሁ ተወስናችሁ ተቀመጡ የሚለው ውሳኔ ለአንዳንዶች ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ጤናማ ቤተሰብ የሌላቸው ወይም ቤት ውስጥ ችግር ያለባቸው፣ በተጨናነቀ እና በጠባብ ቤቶች ለሚኖሩ ሁኔታው የበለጠ የከፋ አድርጎታል።”

“ስለዚህ እነዚህ ሁሉ የፖሊሲ ምክሮች፣ ውሳኔዎች እንዲሁም የሃሳቦቹ መነሻ የተገኙት ሁሉንም ሕዝቦች ባካተተ ምርምር አይደለም። ከእነዚህ አገራት የመጡ ፖሊሲዎች ጥቂቶችን የሚጠቅሙ በርካቶችንም የሚጎዱ ናቸው” ይላሉ።

በተጨማሪም በጣም ዝቅተኛ በሆነ የሙቀት መጠን መቀመጥ ያለባቸው ለአንዳንድ የላቁ የኤምአርኤን ክትባቶች የማጓጓዣ እና የማከማቻ መስፈርቶች ሳይንስን ሁለንተናዊ ለማድረግ የመሞከሩ ሁኔታ ተጨማሪ ፈተናዎች ፈጥረዋል።

“ክትባቱ በትክክለኛው የሙቀት መጠን ለረጅም ጊዜ መቆየቱን እና ማኅበረሰቡ ጋር እንዴት ሊደርስ ይችላል የሚለውን በተመለከተ ችግሮችን ማየት ጀመርን። የክትባት ምርምሮቹ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ እና በአካባቢው ቢደረግ እነዚህን ችግሮች አስቀድመው መፈታት ይችሉ ነበር” ይላሉ ዶክተር ሃንት።

ሳይንስን ዲሞክራሲያዊ የማድረግ አስፈላጊነት

በሳይንስ ላይ በፆታ፣ በዘር ወይም በመደብ ላይ የሰፈነው መድሏዊ ችግርን ለመቅረፍ “ሳይንስን ዲሞክራሲያዊ የማድረግ ሥራን እንድንሠራ ይጠይቃል ይላሉ” ዶ/ር ሃንት።

ለዚህም አንደኛው መንገድ ከተለያዩ አገራት የመጡ ተመራማሪዎችን ማበረታታት እና ሳይንቲስት እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

“ሁልጊዜም ቢሆን ትኩረት የምንሰጠው ለራሳችን ልምዶች ነው። አስፈላጊ ነው ብለን የምናስበውን ነገር ቅድሚያ እንሰጣለን። ይህም አተያያችንን ይቀርፀዋል” በማለት ዶክተር ሃንት ያስረዳሉ።

“እነዚህን ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች በግዴታ ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ በምርምር ውስጥ ብዝሃነት ሊኖር ይገባል፤ ምክንያቱም አዳዲስ ሀሳቦችም የሚገኙት በዚህ መንገድ ነው።”

ሌላው “ሳይንስን ዲሞክራሲያዊ እምዲሆን” መደረግ አለበት የሚሉት ምርምሮች ላይ የገንዝብ ድጋፍ ለማድረግ የብዝሃነት መስፈርቶችን ማሟላት እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ነው።

በተለያዩ አገራት ያሉ ብሔራዊ የሳይንስ ተቋማት ይህንን ተግባራዊ ያደርጉታል ነገር ግን “ውጤቱ ወጥ ሊሆን አልቻለም” ብለዋል ዶክተር ሃንት።

በሳይንስ ውስጥ ያለውን አድሏዊነት ለመታገል ኢንዱስትሪው አንድ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያምናሉ ባለሙያዋ።