በዘፈቀደ ከፋርማሲ የምንገዛቸው ቀላል መድኃኒቶች እየጨረሱን ይሆን?

መድኃኒት የተገራ ‘መርዝ’ ማለት ነው። ረቂቅ እንክብል ልታሽረን፣ ደቂቅ እንክብል ልታሰናብተን ትችላለች።

በመርዝና በመድኃኒት መሀል ያለው ቀጭን ልዩነት ‘ምጣኔ’ ይባላል።

አንዳንድ መድኃኒቶች በማዘዥ ብቻ የሚሸጡልንም ለዚሁ ነው፤ መርዝ እንዳይሆኑብን።

መቼና እንዴት እንደምንወስዳቸው በአደራ ጭምር የሚነገረን ለዚሁ ነው፤ መልሰው እኛኑ እንዳይደፉን።

እኛ ግን ግድ የለንም። ምናልባት እንክብሎችን በገንዘባችን እንደልብ ስንገዛቸው ጊዜ አስቤዛ እየመሰሉን ይኾናል?

የምናወራው ስለእነ አሞክሳሲሊን፣ ስለነሜትሮኒዳንዞል፣ ስለሲፕሮፍሎክሲን ነው።

ስማቸውን ስለሸመደድናቸው ‘ተራ’ አንቲባዮቲኮች።

እውነት ለመናገር ተራስ አይደሉም።

‘አንቲባዮቲኮች’ ከእያንዳንዱ መዳናችን ጀርባ ያሉ ዋስትናዎች ናቸው። የደኅንነታችን ዘቦች ናቸው።

አሁን ግን ዞረው እየተኮሱብን ነው።

የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች መጨነቃቸውም ለዚሁ ነው።

በመድኃኒት መሞት የነበረባቸው ተህዋሲያን አንሞት አሉ። ደደሩ።

ፀረ-ተህዋሲያንን የሚቋቋሙ ጀርሞች በኢትዮጵያ እንደ አሸን ፈሉ።

ይህ ነው የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ያስጨነቃቸው።

ዶ/ር እስከዳር ፍርዱ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪም ናቸው። “ይህ ነገር ሁሉንም ሐኪም እያስጨነቀ ያለ ጉዳይ ነው” ይላሉ።

ጭንቁን ምን አመጣው?

መድኃኒትን የናቁ ተህዋሲያን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መድኃኒቶች ፈዋሽነታቸው እየለገመ ነው። በተለይ አንቲባዮቲኮች።

ለምን ለገሙ?

አንዱ ምክንያት እንደ መርፌ እየተዋዋስን ስለምንወስዳቸው ነው፤ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ፣ በዘፈቀደ።

“ቆይ ያላለቀ መድኃኒት አለኝ፣ እንዳትገዙ...” እያልን።

ብዙ ኢትዮጵያዊ ወላጆች ለ7 ቀን የተሰጣቸውን ‘አንቲባዮቲክ’፣ ለሦስት ቀን ብቻ ይወስዱታል።

‘ምነው?’ ሲባሉ፣ “ውይ! ወዲያው ተሻለኝ እኮ!!” ይላሉ።

ይህ እጅግ በጣም አደገኛ ነገር እንደሆነ ሐኪሞች እንጂ ተርታው ሕዝብ አያውቅም።

የሕዝብ ዕውቀት ከተሳሳተ አደገኛ ነው።

ጉዳቱ መድኃኒቱን ላቋረጠው ሰው ብቻ ሳይሆን ለመላው ማኅበረሰባችን እንደሚተርፍ ብዙ ሰው አይረዳም።

ያለማዘዣ የምንገዛቸው ‘አልታዘዝ’ ያሉ መድኃኒቶች

በፊት ተህዋሲያን በመድኃኒት ይሸበሩ ነበር። አሁን ተናናቁ።

ነገሩን ‘የፀረ-ተህዋሲ መድኃኒቶች ብግርና’ እንለዋለን። ይህ የሚሆነው አንድ ተህዋስ ድራሹን እንዲያጠፋው ለተቀመመ መድኃኒት ‘እምብየው! አልበገርም!’ ሲል ነው።

በእንግሊዝኛ “Antimicrobial resistance” ይባላል።

ተህዋሲ መድኃኒትን ከናቀ ጉድ ፈላ። ከዚያ በኋላ ያን ሰው ማከም ፈተና ነው።

በመላው ዓለም ሚሊዮኖች በዚህ ቸልተኝነት ሞተዋል። በኢትዮጵያ ግን የቆጠረው የለም።

በ2050 በዓለም ቁጥር-1 ገዳይ ይሆናል ተብሎ የተተነበየለት ይህ የፀረ-ተህዋሲ መድኃኒቶች ብግርና ነው።

የጤና ባለሙያዎችን ጤና እየነሳ ያለውም ለዚሁ ነው።

የእኛ ሐኪሞች የፀረ-ተህዋሲ ብግርናን በሚሠሩባቸው ሆስፒታሎች ሁሉ እያዩት ነው።

ዶ/ር እስከዳር ከእነዚህ ሐኪሞች አንዱ ናቸው።

የተላመዱ ተህዋሲያን በጤና ተቋማት ውስጥ በብዛት መገኘታቸው የሚጠበቅ እንደሆነ አውስተው፣ አሁን ግን ነገሩ ወደ ኅብረተሰቡ እየዘለቀ እንደሆነ ምልክቶች እንዳሉ ያወሳሉ።

“ታካሚዎች በሆስፒታል ብዙ ፀረ-ተሕዋሲ መድኃኒት ይሰጣቸዋል። ስለዚህ መድኃኒትን በተላመዱ ሱፐርበግ (superbug) ባክቴሪያዎች ሊያዙ ይችላሉ።አሁን ነገሩን አሳሳቢ እያደረገ ያለው ግን ይህ ‘የተማረ’ ባክቴሪያ ወደ ኅብረተሰቡ ዘልቆ መግባቱ ነው’’ ይላሉ።

ዶ/ር እስከዳር ‘የተማረ’ እያሉ የሚጠሩት ተህዋሲ መድኃኒት የተላመደውን ነው። ብግሩን።

እርሳቸውም በሥራ አጋጣሚ የሚያክሟቸው ብዙ ታማሚዎች ፀረ-ተህዋሲ መድኃኒቶች ቢታዘዙላቸውም የሚጠበቀውን ውጤት ሳያመጡ ሲቀሩ አይተዋል።

በአጭሩ በዚህ ዘመን አንቲባዮቲኮች ለገሙ፤ ተህዋሲያኑ ደደሩ፣ ጀርሞች በገሩ።

ይህ በዚሁ ከቀጠለ ግን ምን እንሆናለን?

የጤና ሰዎች በጊዜ ሕዝቡን ማንቃት ያስፈልጋል እያሉ መጮኽ የጀመሩት ግን ለምንድነው?

ሐኪሞቻችን ‘መድኃኒትን በዘፈቀደ መውሰድ ይብቃ!’ እያሉ በአያሌው የሚተቹት ምን ታይቷቸው ነው?።

“በቀላል ምሳሌ ጉንፋን ቫይረስ ነው፤ የሚድነው በእንክብካቤ ነው፤ ለጉንፋን አንቲባዮቲክ ሲሰጥ ተህዋሲያን መድኃኒትን እየተላመዱ እንዲመጡ ዕድል ይከፍታል’’ ይላሉ ዶ/ር እስከዳር።

ሌላው ደግሞ መድኃኒት ጀምሮ የመተው አባዜ።

“..አሁን እዚህ ጥቁር አንበሳ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ብትገቡ ‘ግራምኔጌቲቭ’ የሚባሉ ባክቴሪያዎች በጣም ተላምደው እያስቸገሩን ነው።”

ስለ የትኛው መድኃኒት ነው የምናወራው?

የፀረ-ተህዋሲ መድኃኒት (Anti-Biotics) የምንላቸው ለባክቴሪያ፣ ለጀርሞችና ለፈንገሶች የሚሰጡ መልከ-ወ-ስመ ብዙ መድኃኒቶችን ነው።

ሐኪሞች አዘውትረው ስለሚያዙልን ነው መሰል እንደ ዘመድ በቅርብ እናውቃቸዋለን። አንዱ ችግርም ይኸው ነው።

ምን ያህል ሐኪሞች ናቸው መድኃኒቶቹን በማዘዝ ረገድ ጥብቅ ጥንቃቄን የሚከተሉት? በዘፈቀደ የማዘዝ አዝማሚያስ የለም ወይ?

አለ!

በግዴለሽነት እያንዳንዱን ታካሚ አንቲባዮቲክ እያሸከሙ የሚልኩ 'ኬረዳሽ' ሐኪሞች የሉም አይባልም። አሉ!

ለጊዜው ግን በሐኪሞች በኩል ያለውን ችግር ለሌላ ጊዜ እናቆየውና ስለ እኛ እናውጋ።

ብዙዎቹን መድኃኒቶች ለጉንፋን፣ ለጉሮሮ ኢንፌክሽን፣ ለተቅማጥ በሚል እንዲሁ እንደዋዛ ከፋርማሲ እንገዛቸዋለን። ትክክል አይደለንም።

እኛ ገዢዎች ብቻ ሳንሆን ሻጮቹም ልክ አልሠሩም።

ያለ ሕጋዊ መድኃኒት ማዘዣ መሸጥ የሌለባቸው ናቸው።

ሆነም ቀረ ፋርማሲዎች ‘እኛ ምናገባን!’ ብለው ይሸጡልናል። ሁሉም ባይባልም ብዙዎቹ።

ውለታ እየዋሉልን ከመሰለን ተሳስተናል። የፈጸሙት ያፈጠጠ ወንጀል ነው።

እነዚህ መድኃኒቶች ያለ ማዘዣ አይሸጡ የተባለው በምክንያት ነው።

ያለመታደል ኾኖ ብዙ መደብሮች ከኛ ጤና ይልቅ የኛ ገንዘብ ያስጨንቃቸዋል።

ይህን የምንለው በሐሜት ሳይሆን በማስረጃ ነው።

የጤና ተመራማሪዎች የሆኑት ኢዮሳይት፣ ገብረመድህን በዕደማርያም እና ትንሳኤ ተክሌ ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ጥናት አሳትመው ነበር።

ጥናቱ በአዲስ አበባ ምን ያህሎቹ ፋርማሲዎች በማዘዣ ብቻ መሸጥ ያለበትን መድኃኒት ያለማዘዣ ይሸጣሉ የሚለውን ለመገምገም ነበር።

ለጥናቱ የተመረጡ ሰዎች ሆን ብለው በየፋርማሲው እየሄዱ መድኃኒቶቹን እንዲጠይቁ ተደረገ። እንደ ድራማ ብጤ።

“ልጄ ተቅማጥ ይዞት ነው፣ መድኃኒት ፈልጌ ነው?” እያሉ ሰዎች ፋርማሲ እንዲጠይቁ ተደረገ። የጥናቱ ውጤት አስደንጋጭ ነበር።

በጥናቱ ከተቃኙት 262 ፋርማሲዎች፣ 166ቱ የተጠየቁትን መድኃኒት ለጥናቱ ‘ተዋናዮች’ ሸጡላቸው፤ ያለ ምንም ማዘዣ።

ፋርማሲዎች ለምን አይቀጡም?

ይህን መቆጣጠር ያለበት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ነው።

ለመሆኑ ይህ መሥሪያ ቤት ምን እየሠራ ነው? አቶ ሚሊዮን ትርፌን ጠየቅን።

አቶ ሚሊዮን በዚህ መሥሪያ ቤት አግባባዊ የመድኃኒት አጠቃቀም ከፍተኛ አስተባባሪ ናቸው።

መሥሪያ ቤታቸው ችግሩ እንዳለ በማያሻማ ሁኔታ መረዳቱን አልሸሸጉም።

በቁጥጥር ረገድ ያለውን ክፍተት ሲያስረዱ፣ መሥሪያ ቤታቸው በሰባት ክልሎች ቅርንጫፍ ቢኖሩትም በቀጥታ እርምጃ ለመውሰድ ግን መቸገሩን ጠቀሱ።

ለምን ተቸገረ?

“እኛ ፌዴራል ነው የተቀመጥነው፤ አንድ ክልል ሄደን ይሄን ጥፋት አይተናል ብለን እርምጃ መውሰድ ግን አንችልም፤ ክልሉ ይህ የኔ ሥራ ድርሻ ነው ይለናል።”

ችግሩ የተጠቃሚዎች ብቻ አለመሆኑን ያወሱት አቶ ሚሊዮን ፋርማሲ ባለሙያዎችም ቢሆን ያለ ማዘዣ መሸጥ እንደሌለበት እያወቁ ‘ያው ደንበኛው እኔ ባልሸጥለት ቀጥሎ ካለው ፋርማሲ ይሸጥለታል’ በሚል ለመሸጥ ይበረታታሉ።

አቶ ሚሊዮን ችግሩ የሚመነጨው ከስግብግብ ፋርማሲዎች ብቻ እንዳልሆነ ግን ያሰምሩበታል። የታካሚው ቸልተኝነት፣ የግንዛቤ መሳሳትም መኖሩን አስገንዝበውናል።

“ሰዎች ሐኪም ቤት ሄደው፣ ወጪ አውጥተው፣ ተሰልፈው መታከም ያታክታቸዋል። አማራጭ ሆኖ የሚታያቸው ለተመሳሳይ ችግር ከዚህ ቀደም የወሰዱትን መድኃኒት ደግሞ ገዝቶ መዋጥ ነው።”

በሌላ አነጋገር ሰው ፋርማሲ ሄዶ ራሱን በራሱ ያክማል። የ5 ቀን የ7ቀን እያለ አንቲባዮቲክ ያዛል።

 “ራስን በአንቲባዮቲክ መድኃኒት ማከም በጣም አደገኛ ውሳኔ ነው” ይላሉ አቶ ሚሊዮን።

እንደ በርገር በሞተረኛ የሚሸጡ መድኃኒቶች

የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ በርካታ ግብይት መልኩን ቀይሯል።

ሰዎች ከቤት መውጣት አይፈልጉም።

ካሉበት ሆነው የሚያዙት ታዲያ በርገር እና ጫት ብቻ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች መድኃኒትም ያዛሉ፤ ለዚያውም ከቤታቸው፤ ለዚያውም በሞተረኛ፤ ለዚያውም ያለማዘዣ።

“ለምሳሌ ሬምዲሲቪር (Remdesivir) የሚባል መድኃኒት ነበር። ሰዎች በኪሳቸው ከውጭ አገር ይዘውት ይገባሉ። የሆነ ሆስፒታል ለተኛ ታማሚ በሞተረኛ ይቀባበሉታል። ይህ ነገር እንደ ልማድ ተወስዶ በሌሎች መድኃኒቶች (አንቲባዮቲክም ጭምር) እየተዘወተረ እንደሆነ እንረዳለን” ይላሉ አቶ ሚሊዮን።

ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ዓለምቀረ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክሊኒካል ፋርማሲ ክፍል ባልደረባ ናቸው።

በግለሰብ ደረጃ የሚታየው ፀረ- ተህዋሲ መድኃኒት የአወሳሰድ ቸልተኝነት መዘዙ ‘ለግለሰቡ ብቻ ከመሰለን ተሳስተናል’ ይላሉ።

“ለ7 ቀን የተሰጠንን አንቲባዮቲክ ተሻለን ብለን ብናቆመው ተህዋሲውን ሳንገድለው ቀረን ማለት ነው። ሳይሞት የቀረው ብግር ባክቴሪያ በቀላሉ ወደ ሌሎች ሰዎችም የመተላለፍ አቅም ይኖረዋል። ይህ ለማኅበረሰብ ሁሉ አደጋ ነው።”

ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው አንድ ጎልቶ የሚታይ የዕውቀት ክፍተት አለ ይላሉ።

ለምሳሌ 500 ግራም አሞክሳሲሊን በቀን በየ8 ሰዓት ልዩነት ለ7 ቀን ሲታዘዝ ይህ የተወሰነው ዝም ብሎ እንደው በአጋጣሚ አይደለም።

“በምን ያህል መጠን፣ ለምን ያህል ጊዜ፣ በምን ያህል ድግግሞሽ ቢወሰድ ጀርሙን ይገድለዋል?” የሚለው የብዙ ዓመት ጥናትና ምርምር የወለደው ውሳኔ ነው።”

የመጨረሻ ጥያቄ እናንሳ። ኅብረተሰቡ ለምን መድኃኒቶችን በዘፈቀደ ይውጣል? ቸልተኝነቱ ከየት መጣ?

ለፕሮፌሰር ጌታቸው ይህ የዕውቀት ማነስ የወለደው ችግር ነው።

‘ምንጊዜም የሕዝብና የምሁራን ዕውቀት ለየቅል ነው። ሕዝብ እንደተሻለው ነው የሚያየው፤ የሕክምና ሳይንስ ግን የሚያየው የጀርሙን መሞት ነው።’

አንዳንዴ የተሻለን ይመስለን ይሆናል እንጂ ይበልጥ እየታመምን ነው።

አንዳንዴ ለፈውስ የተሠሩ መድኃኒቶችን በገዛ እጃችን ወደ መርዝነት እየቀየርናቸው ነው።