ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥንዶች ልጅ እንዳይወልዱ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?
በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን፣ ደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋ እና ወ/ሮ ባንቻየሁ ትዳር መስርተው አብረው መኖር ከጀመሩ 18 ዓመት ተቆጥረዋል።
በእነዚህ 18 ዓመታት ግን ልጅ ለማግኘት አልቻሉም ነበር።
18 ዓመታትን ከፈጀው የልጅ ማግኘት ናፍቆት በኋላ ከሦስት ወር በፊት የመጀመሪያ ልጃቸውን አግኝተዋል።
ጥንዶቹ የመጀመሪያ ልጃቸውን ወልደው ለመሳም የበቁት በቅርቡ በተደረገላቸው ሕክምና እንደሆነ ወይዘሮ ባንቻየሁ ገልጸዋል። የህክምና ባለሞያዎች ችግሩ የቱቦ መዘጋት እንደነበረም ነግረዋቸዋል።
በማህጸን ህክምና የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው ዶክተር እልፍነሽ ድሪብሳ "ማህጸን ላይ ዕጢ ካለ የሴቷ እንቁላል እና የወንዱ የዘር ፍሬ እንዳይገናኙ ቱቦውን ይዘጋዋል። ይሄ ችግር በዚህ ምክንያት የመጣ ሊሆን ይችላል" ይላሉ።
ይህ በተፈጥሮ የሚከሰትበት አጋጣሚ አናሳ ሆኖ፣ ዋነኛው ምክንያት ግን በወቅቱ ህክምና ያልተደረገላቸው በጾታዊ ግንኙነት የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች ቱቦውን እንደሚዘጉት ያስረዳሉ።
በዚህ ምክንያት የወንድ የዘር ፍሬ እንዲሁም የሴቷ እንቁላል ልክ ሆነው እያለ መገናኘት ባለመቻላቸው ብቻ እርግዝና መፈጠር አይችልም።
ትዳር ሳይመሰርቱ ለረዥም ጊዜ መቆየት፣ ትዳር ከመሰረቱ በኋላም ልጅ ሳይወልዱ መቆየት፣ ቤተሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ጫናዎች ስላሉት በዚህ ምክንያት የሚጨነቁ ወይም ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች [በተለይ ሴቶች] ማርገዝ ይቸገራሉ።
አቶ ተስፋ "ሕብረተሰቡ ትዳር እንደተመሰረተ ልጅ ይጠብቃል። የሚጠብቀውን ነገር ካልተሰጠ ሳትፈልግ ቀርተህ ሆን ብለህ ስለሚመስለው ለምንድን ነው ብለው ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ብቸኝነትን እና የመገለል ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል" ይላሉ።
ወ/ሮ ባንቻየሁ በበኩላቸው "አንዳንዱ ከበጎነት ተነስቶ ያዝናል፣ ከንፈር ይመጣል፣ ያንቺስ መቼ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ ሞራል ይነካል። እየፈለግን ስለሆነ ያጣነው ጫናው ከባድ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ጥንዶቹ ባለፉት 18 ዓመታት ልጅ በጉዲፈቻ ወስደው ለምን እንደማያሳድጉ ጥያቄ ሲነሱባቸው እነደነበርም ያስታውሳሉ።
ልጅ መውለድ እየቻሉ ሆን ብለው የተዉት የሚመስላቸው የቅርብ ሰዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ተስፋ፣ "ወደ ሥራ ስትሮጥ አንዳንድ ልጅ እንደሆነ የለህ ማንን ለማውረስ ነው የምትለፋው ይላሉ። እና የሰዉን አፍ የተቋቋምነው ፈጣሪ ረድቶን እንጂ ከባድ ነበር።"
"ጭንቀት መካንነት [ኢንፈርቲሊቲ] ያመጣል። ሴቷ ሳታረግዝ ለስድስት ወራት ስትቆይ 'ማርገዝ እችላለሁ?' በሚል ትጨነቃለች። በተለይ ከባለቤቷ ቤተሰቦች የሚመጣ ጫና ሲኖር ጭንቀቱ ይበረታል። ወንዱም መመርመር ስለማይፈልግ ችግሩ ያንቺ ነው ይላታል። አገራችን ላይ በዚህ ጉዳይ በቂ ግንዛቤ ስለሌለ ጫናው ሴቶች ላይ እንዲበረታ ያደርገዋል" ሲሉ ዶክተር እልፍነሽ ያስረዳሉ።
ወንድ መሃን የሚሆንባቸው ምክንያቶች
በኢትዮጵያ ስለ ጾታዊ ግኑኝነት እና የመራቢያ አካላት በግልጽ መነጋገር እና መማማር ዛሬም ድረስ እንደ ነውር ይቆጠራል።
በመሆኑም ባለትዳሮች ልጅ ሳይወልዱ ለረዥም ዓመታት ሲቆዩ፣ አብዛኛውን ጊዜ ኅብረተሰቡ ልጅ የመውለድ ኃላፊነት ሴቷን በማሸከም ይኮንናታል። ባለጉዳይዋም ብትሆን ችግሩ የእኔ ነው ብላ ታስባለች።
የማህጸን እና ጽንስ ሐኪሟ ዶክተር እልፍነሽ ድሪብሳ ግን ችግሩ በሕክምና ምርመራ እስካልተረጋገጠ ድረስ ሁለቱንም ጾታ መፈረጅ እንደማይቻል ያስረዳሉ።
መሃንነት በሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ መኖሩን በማስታወስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ያነሳሉ።
ከእነዚህ ውስጥም በተፈጥሮ የሚያጋጥም አስፈላጊ መጠን ያለው የዘር ፍሬ [ስፐርም] ያለማመንጨት ችግር አንዱ ነው።
ከዚህ በሻገር ሲስቲክ ፋይብሮሲስ የተባለ የጤና ችግር ያለባቸው እንዲሁም እግር ላይ የሚወጣው ቫሪኮስ ቬይን የሚባለው ዕጢ የዘር ፍሬያቸው ላይ ሲወጣ መሃንነትን ያስከትላል።
በተጨማሪም የጥጥ ልብስ ማዘውተር፣ ጥብቅ ያለ የውስጥ ሱሪ ማድረግ፣ ሳውና ማዘውተር በወንዶች ላይ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ።
በተለያየ ምክንያት የመራቢያ አካሉ ላይ (ቆለጥ) የተጎዳ ሰውም የመውለድ ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችል ያስረዳሉ።
"የጥጥ ልብስ መልበስ እንደ ጥቅም ይወራል። ጥብቅ የሚል ፓንት የሚያደርጉ ወንዶችም አሉ። እነዚህ በመራቢያ አካል ላይ ሙቀት እንዲኖረው ስለሚያደርጉ ችግር ነው፤ መሞቅ የለበትም። በተጨማሪም ሙቅ ውሃ በመራቢያ አካል ላይ እያፈሰሱ የሚታጠቡ ከሆነም የዘር ፍሬው ስለሚቀንሰው አደገኛ ይሆናል" ይላሉ።
አልፎ አልፎ ትዳር ውስጥ ልጅ ያለመውለድ ችግር ሲያጋጥም ወንዶች 'እኔ ችግር የለብኝም' ሲሉ ይስተዋላሉ። በተፈጥሮ ዝቅተኛ የዘር ፍሬ ፈሳሽ መጠን [ስፐርም ካውንት] ካላቸው ግን የሴቷ እንቁላል ጋር ደርሲ ጽንስ እንዳይፈጠር ጫና ይፈጥራል።
"አንድ ስፐርም ነው አንድ እንቁላልን ፈርቲላይዝ የሚያደርገው። በአንድ ፈሳሽ ውስጥ ደግሞ ሚሊዮን የዘር ፍሬዎች አሉ። ሆኖም በፈሳሽ ውስጥ ያለው የዘር ፍሬ ትንሽ ከሆነ የተቀሩትን እንቁላሉ ድረስ በመሄድ ከበው አልያም ሰብረው መግባት ስለማይችሉ እርግዝና ሊፈጠር አይችልም" በማለት ያስረዳሉ።
ዝቅተኛ የዘር ፍሬ ፈሳሽ መጠን ካለ፣ ወንዱ ለሦስት ወራት መድኃኒት እንዲወስድ በማድረግ፣ የአመጋገብ ለውጥ በማምጣት፣ ጠባብ የውስጥ ሱሪ መልበስን በመቀነስ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ባለሙያዋ ይገልጻሉ።
በአንጻሩ በተፈጥሮ የዘር ፍሬ የሌላቸው ሰዎች እንዳሉ የሚናገሩት ዶክተር እልፍነሽ፣ ጾታዊ ግንኙነት በአግባቡ ስለሚፈጽሙ ወይ ፈሳሽ ስለሚፈስ ብቻ መካን አይደሉም ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ። ፈሳሹ፣ የዘር ፍሬ የሚሸከም እንጂ ራሱ የዘር ፍሬ ስላልሆነ የዘር ፍሬ ማፍራት አይችልም።
በሌላም በኩል ከልክ በላይ መድኃኒቶች መውሰድ፣ በጾታዊ ግንኙነት ወቅት ፈሳሻቸው ወደ ውስጥ የሚፈስባቸው ሰዎች ከሆኑ እና የዘር ፍሬ ካንሰር ያለባቸው ከሆኑ ልጅ መውለድ ላይ ችግር ይገጥማቸዋል።
ለምሳሌ "በአገራችን አንድ ሰው አስም ሲበረታበት ስቲሮይድ ይወጋል፤ ይህንን መድኃኒት ሲለምድ ደግሞ የዘር ፍሬ ፈሳሽ ላይ ችግር ይፈጥራል። የዘር ፍሬ ካንሰር ደግሞ ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ መቆየት ይችላል። በህክምና መታወቅ የሚችል ቢሆንም በአገራችን ብዙ ስላልተለመደ ሳይታወቅ ቆይቶ መሃንነትን ሊያስከትል ይችላል" ይላሉ።
ሴት ልጅ የማትወልድባቸው ምክንያቶች
በአንዲት ሴት ጸንሳ የመውለድ ሂደት ውስጥ የወር አበባ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
የወር አበባ 28 ቀናት ጠብቆ የሚመጣ ካልሆነ፣ በሦስት ወር አንዴ ወይም በየሁለት ሳምንቱ የሚመጣ ከሆነ እንቁላል ማፍራት [ovulate] ማድረግ አትችልም። በዚህ ምክንያት የተነሳ የማርገዝ ዕድሏ እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል።
ይህ ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች ላይ የሚያጋጥመው ችግር 'ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድሮም' [PCOS] ተብሎ ይጠራል።
ከሆርሞን መዛባት ጋር የሚመነጭ ሆኖ ፒሲኦስ ያለባቸው ሴቶች አልፎ አልፎ የሚታይ ወይም የተራዘመ የወር አበባ አልያም ከልክ በላይ የሆነ የወንድ ልጅ ሆርሞን [አንድሮጅን] እንዲኖራቸው ያደርጋል።
በዚህ ምክንያት በእንቁላል ማመንጫቸው ውስጥ በርካታ ትናንሽ ፈሳሾች ስለሚፈጥር እንቁላሉ ወደ መፈልፈል ደረጃ አይደርስም።
"ይህች እኮ አምስት ወይም ስድስት ዓመት ቆይታ ነው የምትወልደው የሚባል ነገር አለ። እንዲህ የሚሆንበት የጤና ችግር እንኳ ባይሆን ሁኔታው ግን እንቁላል እንዳይፈለፈል ያደርገዋል። በተጨማሪም አንዳንድን ሴቶች በእድሜ ትንሽ ሆነው ሳለ ትልቅ ሆነው ይታያሉ። እንደ ወንድ ጺም ይኖራቸዋል፣ ቆዳቸው በፀጉር ይሸፈናል። ይህም እንቁላል እየተፈለፈለ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው" ሲሉ ዶክተር እልፍነሽ ያስረዳሉ።
ይህ የሕክምና እርዳታ በመስጠት እንቁላል እንዲፈለፈል እንደሚደረግ የሚገልፁት ባለሞያዋ፣ ሴቶች የወር አበባቸው እንዲስተካከል ሆርሞን እየተሰጣቸው [አስቸጋሪ ቢሆንም] በቀላሉ ማርገዝ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈ የኩላሊት ሕመምተኞች፣ በህይወታቸው ከማህጸን ውጪ እርግዝና ያጋጠማቸው ሰዎች፣ የስኳር ሕመም፣ ኢ-መደበኛ የሆነ አመጋገብ፣ ምግብ በአግባቡ አለመመገብ ወይም በጣም መብላት፣ አልኮል፣ ሲጋራ ማጨስ እና ሌሎች ዕጾች መጠቀም ልጅ ላለመውለድ ምክንያት እንደሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሌም በኩል የሚነሳው ግን እድሜ ነው።
እድሜ፣ በሁለቱም ጾታ ጤነኛ ልጅ እንዲረገዝ በማድረግ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ይገለጻል። ሴት ልጅ ጋር ሲሆን ደግሞ እንቁላልዋ ከእድሜዋ ጋር ነው የሚያረጀው።
ይህ የእንቁላሉ ጥራት እና ብዛት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ፣ እድሜ በገፋ ቁጥር የጽንስ መጨንገፍ፣ ጽንሱ ላይ የጀነቲክ እና ክሮሞዞም ችግሮች እንዲፈጠሩ እንዲሁም በቀዶ ጥገና የመውለድ ዕድል እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል።
ሴቶች በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ የመውለድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው የሚሉት ዶክተር እልፍነሽ፣ ከ35 ዓመት በኋላ እንቁላል መፈልፈል የሚያቆምበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይናገራሉ።
"ሴት ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ከ30 ዓመት በላይ ከሆነች የመውለድ ዕድሏ እየቀነሰ ነው የሚመጣው፤ 43 ሲደርስ ደግሞ ያልቃል። ለምሳሌ በ43 የተረገዘው በ44 ይወለዳል። ከዚያ በኋላ እስከ 55 ዓመት የወር አበባ ልታይ ትችላለች፤ ነገር ግን ልታረግዝ አትችልም። ስለዚህ እድሜ ወሳኝ ነው።"
መሃንነት ምንድን ነው?
መሃንነት አንድ ሦስተኛው ከሴቷ፣ አንድ ሦስተኛው ከወንዱ፣ ሌላኛው አንድ ሦስተኛው ደግሞ ከሁለቱም በኩል የሚመጣ መሆኑን የማህጸን እና ጽንስ ህክምና ባለሙያዋ ይገልጻሉ።
የዚህ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም፣ እድሜ ዋነኛው ነው። እንቁላሉ ከእድሜ ጋር ስለሚያረጅ ጫና እንደሚያሳድር ባለሙያዋ ይናገራሉ።
"ከ40 ዓመት በኋላ፣ ከዘጠኝ ሴቶች ስምንቱ የተለያየ መንገድ በመጠቀም ማርገዝ ይችላሉ። ይህ ግን ችግሩ ምንድን ነው የሚለው ከታወቀ ብቻ ነው። በዓለም ደግሞ ከ10 ሴቶች አንዷ መሃን ናት" ሲሉ ዶክተር እልፍነሽ ገልጸዋል።
ጥንዶች ለአንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ ምንም አይነት የመከላከያ ዘዴዎች የሌለበት ጾታዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ ቆይተው መውለድ ካልቻሉ ብቻ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።
አቶ ተስፋ እና ወይዘሮ ባንቻየሁ ከ18 ዓመታት ቆይታ በኋላ የሕክምና ክትትል አድርገው የወለዱት ልጅ 'ካኩ' [ቃልኪዳን] ሲሉ ሰይመውታል።