በብራዚል በሕይወት ከሌለች እናት በተለገሰ ማሕፀን የመጀመሪያዋ ህፃን ተወለደች

በህይወት ከሌለ ሰው ስለሚደረግ የአይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ሰምተን እናውቅ ይሆናል። ከወደ ብራዚል የተሰማው ግን በሕይወት ከሌለች እናት በተለገሰ ማሕፀን ልጅ ወልዶ መሳም መቻሉን ነው።

በብራዚል በሕይወት ከሌለች እናት በተለገሰ ማህፀን ሙሉ ጤናማ ሴት ልጅ መወለዷ ተሰምቷል።

በአውሮፓውያኑ 2016 በብራዚል ሳኦ ፓኦሎ ከተማ አንዲት የ32 ዓመት እናት 10 ሰዓት በፈጀ ቀዶ ሕክምናና ክትትል ካለማህፀን ልጅ መውለድ ችላ ነበር።

እስካሁን እናት ለልጇ የለገሰችውን ጨምሮ በሕይወት ካለ ሰው በተለገሰ 39 የማህጸን ንቅለ ተከላ 11 ሕጻናት ተወልደዋል። ይሁን እንጂ በሕይወት ከሌለች እናት በተለገሰ 10 የማህፀን ንቅለ ተከላ በፅንስ መጨንገፍ ምክንያት አንዱ እንኳን ሳይሳካ ቀርቷል።

አሁን ላይ የተሰማውና በሕይወት ከሌለች እናት የሚለገስ ማህፀን ልጅ ማፍራት በመቻሉ ለበርካታ ወላጆች ተስፋ የሰጠ ሆኗል።

ለጋሿ በ40 ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ የ3 ልጆች እናት ነበረች፤ ሕይወቷ ያለፈውም በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ሳቢያ ነው።

የእርሷ ማህፀን የተለገሳት እናት ደግሞ ሜየር ሮኪታንስኪ ኩስተር ሁሰር የተባለ የሆርሞን መዛባት( syndrome) ችግር አለባት። ይህ ችግር በሴቶች ላይ የሚፈጠር ሲሆን የመራባት ሒደታቸውን የሚገታ ነው፤ ለዚህ የጤና ችግር የተዳረጉ ሴቶች የውጫዊ መራቢያ አካላቸውና ማህፀናቸው እድገቱን ያቆማል አሊያም ጭራሽ ሊጠፋ ይችላል።

እርሷም ታዲያ ይሄው ከ4500 ሴቶች በአንዷ የሚከሰተውና ማህፀንንና የሴት ልጅ ውጫዊ የመራቢያ ክፍል የሚያጠቃ የጤና ችግር አጋጥሟታል። በዚህ ምክንያትም ማህፀኗ ፅንስ መሸከም አይችልም ነበር።

ነገር ግን ዕንቁላል የሚሸከመው ክፍል ግን ችግር አልነበረበትም፤ ሐኪሞቹም እንቁላሉን ከግድግዳው ላይ ማስወገድና ከወንዱ ፈሳሽ (ስፐርም) ጋር በማዋሃድ ማቀዝቀዝ ችለው ነበር።

ከዚያም እናትየዋ ንቅለ ተከላውን የሚከላከልና ለማስወገድ የሚያስችለውን በሽታ የመከላከል አቅሟን የሚያዳክም መድሃኒት ተሰጥቷል።

ከዚያም ከስድስት ሳምንት በኋላ የወር አበባ ማየት ጀመረች፤ ከሰባት ወራት በኋላ ደግሞ ከወንዱ የዘር ፈሳሽ ጋር የተዘጋጀው እንቁላል በማህፀኗ እንዲቀመጥ ተደረገ። ከዚያ በኋላ ጤናማ በሆነ እርግዝና 2.5 ኪሎ ግራም የምትመዝን ህፃን በቀዶ ሕክምና ለመገላገል ችላለች።

በሳኦ ፓኦሎ ዳስ ክሊኒካስ ሆስፒታል ሐኪም ዶ/ር ዳኒ ኢጂዘንበርግ "መካንነት ላጋጠማቸው ሴቶች በሕይወት ካለች ሴት የማህፀን ንቅለ ተከላ ማድረግ የሕክምና መርቀቅን ያሳያል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ በሕይወት ያሉ የማህፀን ለጋሾች ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ፤ ብዙ ጊዜ ፈቃደኛ የሚሆኑትም የቤተሰብ አባላትና የቅርብ ጓደኞች ናቸው ይላሉ - ዶ/ር ዳኒ።

በእንግሊዝ ኢምፔሪያል ኮሌጂ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ስርጃን ሳሶ በቡላቸው አሁን የተገኘው ውጤት በጣም የሚያስደስት እንደሆነ ይናገራሉ።

ይህም ብዙዎች ልጅ ወልደው መሳም እየፈለጉ በጤና ችግር ያልቻሉ ወላጆች ተስፋቸውን ያለመለመላቸው አጋጣሚ ሆኗል። በርካታ ለጋሾች ይመጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልፀዋል።

"በሕይወት እያሉ ማሕፀናቸውን የሚለግሱ እናቶች በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚያጋጥማቸውን አደጋም ያስወግዳል" ሲሉ በታየው ውጤት ተስፋቸው እንደለመለመ አስረድተዋል።