ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በየቤቱ እና በየጎዳናው የሚደፈሩ ሴት የአእምሮ ህሙማን
ወጣቷ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረች ። በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የአእምሮ መታወክ ይገጥማትና በአማኑኤል ሆስፒታል ህክምና ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች።
ህመሟ በረታ፣ ግን ነገሮችን ተከታትሎ ህክምናዋ ከዳር እንዲደርስ የሚያደረግ ሰው ከጎኗ ስላልነበረ ጎዳና ላይ ወደቀች።
ከዓመታት በፊት ጎዳና ተዳዳሪነት ላይ ለሚደረግ ጥናት መረጃ እየሰበሰበች የነበረችው ዶ/ር ማጂ ኃይለማሪያም ያገኘቻት ይህች ወጣት በወቅቱ አስራ አምስት በሚሆኑ የተለያዩ ወንዶች መደፈሯን ገልፃላት ነበር።
አጥኚዎቹ ወጣቷ አማኑኤል ሆስፒታል በቋሚነት ገብታ እንድትታከም አደረጉ። በተደጋጋሚ የሚደፈሩ የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች ኤች አይ ቪ የሚያዙ ቢሆንም ይቺ ወጣት ግን እንደ እድል ሆኖ ውጤቷ ኔጌቲቭ ሆነ።
ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ወጣቷ ከአማኑኤል ሆስፒታል አገግማ ወደ አንድ መጠለያ ተላከች።
ቢሆንም ከዓመታት በኋላ ይቺን ወጣት ዳግም አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ የምትወስደውን መድሃኒት አቁማና ተጎሳቁላ ጎዳና ላይ እንዳገኘቻት ዶ/ር ማጂ ታስታውሳለች።
ስለ ደረሰባቸው ነገር፣ ስለ ማንነታቸው እንዲሁም ከየት እንደመጡ፤ እንዲህ እንዲያ ነው ብለው መናገር የማይችሉ የተደፈሩ የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች ሁሌም ለተደፈሩ ሴቶች ድጋፍ ወደ ሚሰጠው የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር ይሄዳሉ።
አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሴቶች አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው፣ አርግዘው ወይም ጨቅላ ህፃን ይዘው ወደ መጠለያው እንደሚሄዱ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር ኃላፊ ነርስ የሆነችው ስምረት ተስፋዬ ትናገራለች።
ስምረት እንደምትለው ስለተፈጸመባቸው ጥቃት መናገር አለመቻላቸው ለእነሱ የሚደረገውን እርዳታ እጅግ ከባድ ያደርገዋል።
እነዚህ ሴቶች ብዙ ጊዜ የሚደፈሩት ጎዳና ላይ ቢሆንም "በአባት፣ በወንድም፣ በጎረቤትና በአስተማሪም ተደፍረው የሚመጡም የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች አሉ" ትላለች ስምረት።
እነዚህ ሴቶች የቅርብ በሚሏቸው ወንዶች መደፈራቸው የሚታወቀው ራሳቸው ተናግረው ሳይሆን ሌሎች የቅርብ ሰዎች ተከታትለው ነገሮች ላይ ሲደርሱ እንደሆነም ታስረዳለች።
እነዚህን የተደፈሩ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ሴቶችን ለመርዳት መጠለያው መጀመሪያ የሚያደርገው አካላዊና አእምሯዊ የህክምና ምርመራ እንዲያደርጉና ወደ ጤናቸው እንዲመለሱ ማገዝ ነው።
ተደፍረው ወደ መጠለያው የሚሄዱት ብዙ ጊዜ እድሜአቸው ከ10 - 30 የሚሆን ነው። በኤች አይ ቪ መያዝም ሌላው አስከፊ ጥቃቱን ተከትሎ ሊያጋጥም የሚችል ችግር ነው።
ሁሉንም ነገር 'ስለሚያማት ነው' በሚል ከማለፍ የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶችን ከህመማቸው ባሻገር መመልከት እንደሚያስፈልግ "የአእምሮ ችግር አንድ ነገር ነው፤ ጥቃቱ ደግሞ ከሴትነት ጋር የተያያዘ ሌላ ችግር ነው። ስለዚህ ይህች ሴት ይህ ችግር ደርሶባት ሊሆን ይችላል የሚለው ነገር ወደ ሰዎች አእምሮ ቢመጣ ጥሩ ነው" በማለት ታስረዳለች ስምረት።
የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች በህክምና ተቋማት ውስጥም እንደሚደፈሩ በተወሰኑ ክፍለ ከተሞች ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ የአእምሮ ህምምተኞች ማገገሚያዎች ትኩረት ባልተሰጠበት ቀደም ባሉት ዓመታት መጠለያዎቹ የሚገኙባቸው አካባቢ ያሉ አንዳንድ ነዋሪዎች ሴትም ሆነ ወንድ የአእምሮ ህመምተኞችን ያለ ክፍያ የጉልበት ሥራ ያሰሯቸው፣ እርሻ ያሳርሷቸው ጭምር እንደነበር ዶ/ር ማጂ ታስታውሳለች።
ሴቶቹ ደግሞ በአካባቢው ኗሪ ወንዶች ይደፈሩ ሁሉ እንደነበርም ታስታውሳለች።
በተደጋጋሚ መደፈር
እንደ አማኑኤል ሆስፒታል ካሉ ተቋማት ተሽሏቸው እየወጡ ዳግም ጎዳና ወድቀው በተደጋጋሚ የሚደፈሩ የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች ጥቂት አይደሉም።
አብዛኛውን ጊዜ በተለይም ቤተሰብ ወይም መጠጊያ የሌላቸው የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች የሚላኩት ወደ መጠለያዎች ሲሆን፤ ያለ ልምምድ በአንድ ጊዜ ቁጥጥር ያለበትን እንደዚህ አይነት ህይወትን መልመድ አቅቷቸው በተደጋጋሚ ጎዳና እንደሚወጡ ዶ/ር ማጂ ታስረዳለች።
የኮሌጅ ትምህርቷን በአእምሮ ህመም አቋርጣ ጎዳና የወጣችው ወጣት የህይወት እውነታም ይኸው ነው።
በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የሴቶች ለጥቃት ተጋላጭነት ላይ የአእምሮ ህመምተኝነት ሲጨመርበት ነገሩ ምን ያህል እንደሚከፋ "ተከታትሎ የሚያሳክማት ሰው የሌላት፤ ለራሷ መናገርና መቆም የማትችል የአእምሮ ህመምተኛ ሴት ለመደፈር ተጋላጭነቷ ከሁለም የከፋ ይሆናል" በማለት ትገልፃለች።
እሷ እንደምትለው ከጎዳና የሚነሱ ሰዎችን ወደ መጠለያ የመመለስ ሂደት፤ ማለትም ቁጥጥርና ሥርዓት ከሌለበት ነፃ የኑሮ ዜዬ ወደ መደበኛ ኑሮ የመመለስ ሂደት ሽግግር ቢያስፈልገውም በኢትዮጵያ ለዚህ ሽግግር የሚሆን መዋቅር አለመኖሩ ሴቶችን ይበልጥ ተጋላጭ አድርጓል።
ወጣቷ የአእምሮ ህመምተኛ ከመጠለያ ለምን እንደወጣች ስትጠየቅ መልሷ "እዚህ ጋር ፀጉርሽን ማበጠር አትችይም፣ እዚህ ጋር መቀመጥ የለብሽም ፣ መብላት ያለብሽ በዚህ ሰዓት ነው" የሚሉ ነገሮችን መቋቋም እንዳቃታት ነበር የተናገረችው።