ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፖስታ ቦምብ በመላክ አሜሪካዊያንን ያሸበረው ቴድ ካዚንስኪ እሥር ቤት ሞቶ ተገኘ
ቴዎዶር ካዚንስኪ ይባላል። ኤፍቢአይ ዩናቦምበር የሚል ስም ሰጥቶታል። በፖስታ ቦምብ በመላክ አሜሪካዊያንን ለዓመታት ሲያሸብር የቆየ ግለሰብ ነው። የግለሰቡን የወንጀል ታሪክ የሚተርክ ተከታታይ ፊልም ተሰርቷል።
ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ግለሰቡ እሥር ቤት ሞቶ ተገኝቷል።
የ81 ዓመቱ ካዚንስኪ ሶስት ሲገድል 23 ደግሞ አቁስሏል። ይህን ያደረገው በሚልካቸው ፖስታዎች ቦምብ በመደበቅ ነው።
ይህ የሆነው በፈረንጆቹ ከ1978 እስከ 1995 ባለው ጊዜ ነበር።
ለ20 ዓመታት ያክል ከፖሊስ ሲሸሽ ቆይታ በስተመጨረሻ የተያዘው ቴድ በ1996 የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ተፈረደበት።
ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ትምህርት ያጠናው ካዚንስኪ በአሜሪካዋ ሞንታና አንድ ጫካ ውስጥ በሠራው አነስተኛ ቤት ሳለ ነው የተያዘው።
አሜሪካዊያንን ለዓመታት ያህል ሲያስደንቅ የቆየው ቴድ በርካታ ፊልሞች ተሠርተውለታል።
ያለፉት ሶስት አሥርት ዓመታት እሥር ቤት ያሳለፈው ካዚንስኪ ከመሞቱ በፊት ኖርዝ ካሮላይና የሚገኝ ማረሚያ ቤት ነበር።
የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች በአካባቢው አቆጣጠር እሑድ ለሊት 6፡25 የግለሰቡን ሬሳ እንዳገኙት የአሜሪካ እሥር ቤቶች አለቃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሞቱ ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን አልተጣራም።
ባጋጠመው የጤና እክል ምክንያት ወደ ኖርዝ ካሮላይና ማረሚያ ከመዘዋወሩ በፊት ኮሎራዶ በሚገኝ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግለት እሥር ቤት ነበር።
ቴድ፤ ዋሺንግተን ፖስትና ኒው ዮርክ ታይምስ የተባሉትን ጋዜጦች አስገድዶ ‘ማኒሰፌስቶውን’ እንዲያትሙ አስደርጓል።
መስከረም 1995 ‘Industrial Society and Its Future’ በግርድፍ ትርጉም ኢንዱስትሪ መር ማሕበረሰብና የወደፊት ዕጣ ፈንታው የተሰኘ ፅሑፍ ነው በግድ ጋዜጦቹ እንዲያትሙ ያደረገው።
ኤፍቢአይ እና የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕግ በሰጡት አስተያየት ነው ሁለቱ ግዙፍ ጋዜጦች የግለሰቡን ማኒፌስቶ ያተሙት።
ቴድ፤ ጋዜጦቹ ይህን ፅሑፍ ካተሙለት ጥቃት ማድረሱን እንደሚተው ቃል ገብቶ ነበር።
35 ሺህ ቃላት የቴድ ፅሑፍ ዘመናዊ ሕይወትን የሚቃወም ሲሆን ቴክኖሎጂ አሜሪካዊያንን አቅም አልባና ብቸኛ አድርጎ ወደ ጥፋት ይመራቸዋል የሚል ሐሳብ አለው።
ይህ ፅሑፉ እስኪታተም ድረስ የፀጥታ ሰዎችም ሆኑ ሌሎች ስለግለሰቡ ማንነት የሚያውቁት ነገር አልነበረም።
ግለሰቡ በፖሊስ ዓይን ሥር የገባው የቴድ ወንድምና ሚስቱ ፅሑፉን ካነበቡ በኋላ እሱ ሊሆን ይችላል ብለው ለኤፍቢአይ በመጠቆማቸው ነው።
ሚያዚያ 1996፤ የፀጥታ ሰዎች ሊንከን በተሰኘችው የሞንታና ክፍለ ግዛት ካለ አንድ ጫካ ከእንጨት በሠራው 3 በ4 ቤቱ ውስጥ በቁጥጥር ሥር አዋሉት።
ቤቱ ስትበረበር በርካታ መፃሕፍት፣ በልዩ ቋንቋ የተፃፈ ግለ ሕይወት፣ ፈንጂዎችና ሁለት ያለቀላቸው ቦምቦች ተገኝተዋል።
ምንም እንኳ በርካቶች ሰውዬውን እንደ የበቃ ፖለቲከኛ ቢመለከቱትም እሱ ግን በፍፁም ከበቀል ውጭ ሌላ ዓይነት ዓላማ እንደሌለው ይናገር ነበር።
ግለሰቡ ወንጀል መሥራት የጀመረው ወንድሙ ከቤተሰብ ንግድ ሲያሰናብተው ወደ ጫካ ገብቶ ራሱ ቤት ሠርቶ ያለምንም ዘመናዊ ቁስ ኑሮ ከጀመረ በኋላ ነው።
የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጥቃቶች ያደረሰው የኖርዝዌስት ዩኒቨርሲቲ ላይ ነው። ቀጥሎ ደግሞ የአሜሪካ አየር መንገድ ላይ።
ግለሰቡ ዩኒቨርሲቲዎችና አየር መንገዶች ላይ ባደረሰው ጥቃት ምክንያት ነው ዘ ዩናቦምበር የተሰኘ ስም የተሰጠው።
ቴድ በልጅንቱ የወሰደው የአይኪው [የአእምሮ ምጠቀት ልኬት] ፈተና ውጤት 167 ሲሆን ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የገባው ገና በ16 ዓመቱ ነበር።