ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“መኪናችሁን እንወርሳለን” - የኢራን መንግሥት ማስፈራሪያ ሂጃብ ለማይለብሱ ሴቶች
የኢራን ባለሥልጣናት በአገሪቱ የተቀጣጠሉ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ያደረጓቸው ሙከራዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትችትን እያስተናገደ ነው።
የኢራን አስገዳጅ የሆነው የአለባበስ መመሪያ መሠረት ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፍኑ እንዲሁም ገላቸውን የማያጋልጥ እና ሰፋ ያለ ልብስ እንዲለብሱ የሚያስገድድ ቢሆንም፣ ሴቶች ግን የተቃውሟቸው አካል በማድረግ ሕጎቹን በአደባባይ እየጣሷቸው ይገኛሉ።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ባለሥልጣናት የአለባበስ ሕጉን የሚጥሱ ሴት አሽከርካሪዎችን ለመከታተል ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ካሜራዎችን የተከሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ጠንከር ያለ ቅጣት ጥለዋል።
የኢራን ፖሊስ አዛዥ አህማድሬዛ ራዳን “ሂጃብ የማይጠመጥሙ ሴቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በምናደርገው ክትትል ይለያሉ” ብለዋል።
አስገዳጁን ሂጃብ የማያጠልቁ ሴቶች ጉዳያቸው ወደ ወንጀል ፍርድ ቤት ተልኮ ክስ ከመመሥረቱ በፊት ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸውም ተናግረዋል።
የፖሊስ አዛዡ ንግግር በቀላሉ አልተወሰደም። በምላሹም ሴቶች በአደባባዮች ላይ ሂጃብ ያልለበሱበትን ምስሎች እና ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ አጥለቀለቋቸው።
‘ስህተት የሚፈጽመው’ ቴክኖሎጂ
ለበርካታ ዓመታት ኢራናውያን ሴቶች በትራፊክ መቆጣጠሪያ ካሜራዎች በተደረገባቸው ክትትል የአለባበስ መመሪያውን ጥሳችኋል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች እንደደረሳቸው ሪፖርት አድርገዋል።
ነገር ግን ባለሥልጣናቱ የአለባበስ መመሪያውን ጥሰዋል ላሏቸው ሴቶች ቅጣት ወይም መኪናችሁ ይወረሳል ብለው ሲያስፈራሩ ይህ የመጀመሪያው ነው።
“ከአንድ ወር በፊት ከሴት ጓደኞቼ ጋር ዳምጋር ወደምትባል ከተማ ከሄድኩኝ በኋላ፣ የመኪና ሰሌዳ ቁጥሬን የሚገልጽ የጽሑፍ መልዕክት ደረሰኝ። በመኪና ውስጥ እያለን ሁላችንም ሂጃብ አላጠለቅንም ነበር” ስትል አንዲት ሴት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከሚያዝያ ጀምሮ በርካታ ሰዎች የመኪና ሰሌዳ ቁጥራቸው ተጠቅሶ ተመሳሳይ መልዕክቶች እንደደረሳቸው ሪፖርት አድርገዋል።
ሂጃብ ሳይለብሱ በአደባባይ ላይ እንደገና ከታዩ መኪናቸው እንደሚወረስ በመጥቀስም ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።
የተጠረጠሩበትን ጥሰት ይግባኝ የሚሉበት ድረ ገጽም ከመልዕክቱ ጋር ተያይዟል።
ሆኖም ይህ መልዕክት የደረሳቸው ሴቶች ብቻ አይደሉም። አንድ ወንድ የመኪና ሰሌዳ ቁጥሩ ተጠቅሶ የታየበት ትክክለኛ ቀን እና ስፍራ ተጠቅሶ የማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ደርሶታል።
“በተጠቀሰው ስፍራ ብቻዬን ነው መኪና ውስጥ የነበርኩት። ከሴት ጋር አልነበርኩም። ካሜራቸው ትክክል አይደለም” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው ይህ ግለሰብ ረጅም ፀጉር እንዳለው የሚያሳይ ምስል ለቢቢሲ አሳይቷል።
በፖሊስ እና በፍትሕ አካላት እየተወሰደ ያለውን ይህንን እርምጃ አንዳንድ የኢራን ጠበቆች ሕገወጥ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
“ሂጃብ አልለበሳችሁም በሚል ምክንያት መኪናዎችን መውረስ በሕገ መንግሥቱ ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት የሌለው እና ወንጀል ነው” ሲሉም ጠበቃ ሞህሰን ቦርሃኒ በትዊተር ገፃቸው ላይ ጽፈዋል።
የኢስላሚክ ሪፐብሊክ የፍትሕ አካል በበኩሉ “በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 638 የመጀመሪያ ማሻሻያ ላይ በመመሥረት በአደባባይ ላይ ሂጃብ ማውለቅ ወንጀል ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ሚያዝያ ላይ የወጣውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ባሉት ቀናት ከኢስላሚክ ሪፐብሊክ ፖሊስ መልዕክት እንደደረሳቸው በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ገልጸዋል።
“የተከበሩ ዜጋ፣ የሂጃብ ሕግን ማክበር እና መታዘዝ ያስፈልጋል” የሚል መልዕክት ደርሷቸዋል።
መልዕክቱ ማንነታቸውን ባልለየ መልኩ የተላከ ይመስላል። በርካቶችም ለዚህ መልዕክት ምላሻቸውን የሰጡ ሲሆን፣ አንዳንዶችም በማፌዝ እና በመሳለቅ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተችተውታል።
መልዕክቱ የደረሰው አንድ ወንድ በኢንስታግራም ላይ “ቴክኖሎጂያችሁ እንዲህ የረቀቀ ነው ማለት ነው?” ሲል በመሳለቅ ጽፏል።
“አልረሳነውም”
ሆኖም ተቃዋሚዎች የተጋረጠባቸውን አደጋ ከቁብ ሳይቆጥሩ አስገዳጅ የሆነው ሂጃብ ላይ የሚደረገውን ትግል ለማስቀጠል ቁርጠኛ አቋም ይዘዋል።
“ባለፉት ጥቂት ወራት ነገሮችን ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ የበርካታ ወጣቶች ሕይወት ጠፍቷል” በማለት በሴምናን ከተማ የምትኖር ግለሰብ ተናግራለች።
በኢራን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ መንግሥት በወሰደው የጭካኔ እርምጃ 71 ህጻናትን ጨምሮ 530 ተቃዋሚዎች መገደላቸውን የኢራን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የዜና አገልግሎት (ህራና) ዘግቧል።
ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል፣ እንዲሁም አራት ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤት ውሳኔ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል።
ለዚህ ተቃውሞ መነሻ የሆነው የ22 ዓመቷ ማህሻ አማኒ በኢራን በሥነ ምግባር ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች ሕይወቷ ማለፉ ነው። ማህሻ፣ ሂጃቧን ያለ አግባብ ነው የለበሰችውም በሚል ነበር የታሰረችው።
ሞቷን ተከትሎ ሴቶች ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በአደባባይ ላይ ሂጃባቸውን በማቃጠል፣ በአየር ላይ በማውለብለብ እና “ሴት፣ ሕይወት፣ ነጻነት” እያሉ የንቅናቄው መፈክርን ሲዘምሩም ተደምጠዋል።
በርካታ ታዋቂ ኢራናውያን ሴት የፊልም ተዋናዮች እና ታዋቂ ሴቶች ተቃውሞውን በመደገፍ ሂጃብ ሳይለብሱ በአደባባይ ላይ ታይተዋል።
ስምንት ወራት ያስቆጠረው ተቃውሞ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ በርካታ ኢራናውያን የግል እና የአደባባይ ሕይወታቸውን የሚቆጣጠረው ሥርዓት እንዲወገድ በመታገል ላይ ናቸው።
“ይህ እስላማዊ አምባገነንነት ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው የሴቶች ጭቆና እና ቁጥጥር ነው። ለዚህም ነው አስገዳጅ የሆነውን የሂጃብ አለባበስ ሕግ መታገል ሥርዓቱን የሚያናውጠው” በማለት በቴህራን ነዋሪ የሆነች አንዲት ግለሰብ ለቢቢሲ የተናገረችው።
በቴህራን የምትኖር ሌላ ሴት በበኩሏ፣ ዛቻዎች እና ማስፈራሪያዎች ባሉበት ሁኔታ አስገዳጅ የሆነውን የአለባበስ ሕግ የምትቃወምበትን ምክንያት ስትናገር “በተቃውሞው የምቀጥለው “ሴት፣ ሕይወት እና ነጻነት” የተሰኘው ንቅናቄያችን አሁንም እንዳለ ለማሳየት፣ እንዲሁም የማህሻን ሞትም እንዳልረሳነው ለመግለጽ ነው” ብላለች።
“አዲስ ስጋቶች”
ለሺዓ ሙስሊሞች የሃጅ ስፍራ በመባል በምትታወቀው የሃይማኖቷ ከተማ ማሽሃድ ነዋሪ የሆነች ግለሰብ “በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ባለው አብዮት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ስለምፈልግ የሂጃብን ሕግ መቃወሜን እቀጥላለሁ። ዝምታን አልመርጥም” በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
በሰሜናዊቷ የራሽት ከተማ ነዋሪ የሆነች ሌላ ግለሰብ በበኩሏ “አስገዳጁን ሂጃብ መታገል ሥርዓቱን የመታገያ አንዱ መንገድ ነው። ምንም እንኳን የአለባበስ ሕጉን ቢቀይሩትም ትግሉ ይቀጥላል” ብላለች።
ተቃውሞው መቀስቀሱን ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ታጋዮች ለእስር ተዳርገዋል።
በአሁኑ ወቅት በዋስ ከእስር የተለቀቀች ፌሚኒስት “ባለፉት ጥቂት ወራት የተረዳሁት ጉዳይ ቢኖር፣ ሴቶች እጅ እንደማይሰጡ ነው። ሴቶች አገዛዙ ባወጣቸው አዳዲስ ማስፈራሪያዎች አልተደናገጡም” በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት የኢራን ባለሥልጣናት ቅርቃር ውስጥ እንደገቡ ታምናለች።
ሂጃብ ላልለበሱ ሴቶች አገልግሎት የሰጡ የገበያ ማዕከላት፣ ሱቆች፣ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ተዘግተዋል።
ይህ ተቃውሞ ከውጭ ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላትም በአዲሱ ፖሊሲ ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
“ፖሊስ የሂጃብን ጉዳይ እንዲቆጣጠረው ማድረግ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ቅራኔ ያሰፋዋል” ሲሉ የእስልምና አብዮታዊ ዘብ የቀድሞ ከፍተኛ አዛዥ የነበሩት ሆሴን አሌይ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በፖሊስ ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ በመጥቀስ “የሥነ ምግባር ፖሊሶች ምን ያህል ተቃውሞ እንዳስነሳ እና ሂጃባቸውን የሚያወልቁ ሴቶች ቁጥር ምን ያህል እንደጨመረው አይተናል” ብለዋል።
አስገዳጁ የሂጃብ ሕግ ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ምሥረታ እኩል ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ባለሥልጣናቱ የሴቶችን አለባበስ ለመቆጣጠር በሞከሩ ቁጥር ተቃውሞው እየጨመረ እና ሂጃብ አንለብስም የሚሉ በርካቶች ሆነዋል።
በተለይም ወጣቱ ትውልድ የሥርዓቱ የሴቶችን አለባበስ ልቆጣጠር ማለቱን እየተቀበለው አይደለም፤ በተለያየ መንገድ ተቃውሟቸውን በመግለጽ በትግላቸው ቀጥለዋል።