ታዋቂው ቻይናዊ ሳይንቲስት ኮሮናቫይረስ ከቤተ ሙከራ ‘አምልጦ ሊሆን ይችላል’ አሉ

ኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ሳለ አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምጦ ወጥቶ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ነበር።

አሁን ወረርሽኙ አጣዳፊ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት አይደለም ቢባልም ከቤተ ሙከራ አምልጧል የሚለው መላ ምት ግን ችላ ሊባል እንደማይገባ ቻይናዊው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጆርጅ ጋዎ ይናገራሉ።

ከፍተኛ የቻይና መንግሥት ሳይንቲስት እና የቻይና የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ኃላፊ ሆነው በሽታውን በመከላከል ብዙ ሠርተዋል። የበሽታውን መነሻ ለማወቅም ሞክረዋል።

ቻይና፣ ዉሃን ውስጥ የሚገኝ ቤተ ሙከራ የቫይረሱ መነሻ ነው የሚለውን መላ ምት የቻይና መንግሥት አይቀበልም።

ፕሮፌሰር ጆርጅ ግን ከዚህ የተለየ ምልከታ አላቸው።

ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “መጠርጠር ሁሌም ጥሩ ነው። ሳይንስ ነው። ሊሆን አይችልም አይባልም” ብለዋል።

ከዓለም ታዋቂ የተህዋሲያን እና የበሽታ መከላከል ባለሙያዎች (ቫይሮሎጂስት እና ኢምዮኖሎጂስት) አንዱ ናቸው።

አሁን ዓለም አቀፉን የቻይና ክትባት ተቋምን ይመራሉ።

ቻይና በይፋ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምልጧል የሚለውን መላ ምት ብታጣጥልም፣ ንግግራቸው ምናልባትም ነገሩን በስክነት እያጤነች እንደሆነ ጠቋሚ ነው እየተባለ ይገኛል።

በዉሃን የቫይሮሎጂ ተቋም ምርመራ እንደተደረገበት ይናገራሉ። በዚህ ምርመራ የቻይና የበሽታ ቁጥጥር ተቋም አልተሳተፈም።

ይህ ቤተ ሙከራ ለዓመታት ኮሮናቫይረስን አጥንቷል።

አንድ የመንግሥት ክፍል በተናጠል ምርመራውን እንዳደረገ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

“በሙያው ባሉ ሠራተኞች ቤተ ሙከራው በድጋሚ ተፈትሿል” ብለዋል።

በይፋ ምርመራ መደረጉ ሲገለጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የምርመራውን ውጤት ፕሮፌሰር ጆርጅ አላዩትም።

ቤተ ሙከራው በንጽህና የተያዘ ነው የሚል ውጤት እንደተሰጠው ግን ሰምተዋል።

“ሁሉንም ቅድመ ሁኔታ ማሟላታቸውን ነው ድምዳሜው የሚያሳየው። ስህተት አላገኙም” ይላሉ።

ኮሮናቫይረስን ያስከተለው ቫይረስ በአንድ ወቅት በሌሊት ወፎች ላይ እንደተከሰተ እርግጥ ነው።

ከሌሊት ወፎች እንዴት ወደ ሰዎች እንደተላለፈ ግን አወዛጋቢ ነው።

ሁለት መላ ምቶች ግን አሉ።

አንደኛው፣ ቫይረሱ በተፈጥሯዊ መንገድ በሌሎች እንስሳት አማካይነት ወደ ሰዎች መተላለፉ ነው።

ሳይንቲስቶች በዚህ መላ ምት እርግጠኛ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ማስረጃዎች አግኝተዋል።

ሁለተኛው መላ ምት በቫይረሱ ጥናት የተሳተፈ ሰው በቫይረሱ ተይዞ በሽታው መሰራጨቱ ነው።

እነዚህ ሁለት መላ ምቶች ሳይንሳዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም ሆነዋል። የሴራ ትንታኔ መነሻ መሆናቸውም አልቀረም።

የዘመናችን አወዛጋቢው እና በፖለቲካ የተወጠረው ክርክር የኮሮናቫይረስ መነሻ ነው።

ፕሮፌሰር ዋንግ ሊንፋ ሲንጋፖር ውስጥ ሳይንቲስት ናቸው። እአአ በ2020 የዉሃንን ቤተ ሙከራ ጎብኝተዋል።

ያኔ ቫይረሱ ገና መሰራጨት እየጀመረ ነበር።

የሥራ ባልደረባቸው ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምልጧል ብላ ትሰጋ እንደነበር እና ኋላ ላይ ግን ሐሳቧን እንደቀየረች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሲንጋፖር ዱክ ኤንዩኤስ ዩኒቨርስቲ የተላላፊ በሽታዎች ምሁር ናቸው።

በዉሃን የቫይረስ ጥናት ማዕከል ከሚሠሩት ፕሮፌሰር ሺ ዛንግሊ ጋር ጓደኞች ናቸው።

ሁለቱም በሌሊት ወፎች የኮኖራናይረስ ምርምር ይታወቃሉ።

“ለሁለት ቀናት እንቅልፍ አጥታ እንደነበር ነግራኛለች። ከቤተ ሙከራዋ ሳይታወቅ በቫይረሱ ተበክሎ ያመለጠ ነገር እንዳለ ሰግታ ነበር” ይላሉ ፕ/ር ዋንግ።

ከዚያ ግን ፕ/ር ሺ የሰበሰቧቸውን ናሙናዎች አጣርተው ኮሮናቫይረስን ሊያስከትል የሚችል ቫይረስ የያዘ ናሙና ከእሳቸው ቤተ ሙከራ በፍጹም እንዳልወጣ አረጋገጡ።

“ፕ/ር ሺ ወይም በእሷ ቡድን ውስጥ ያለ ማንም ሰው ምንም እንዳልተፈጠረ ሊያስመስሉ የሚችሉበት ዕድል ዜሮ ነው። ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ እንደሆነ ማስረጃ ቢያገኙ ኖሮ ምንም እንዳልተፈጠረ እራት እየበሉ ሕይወትን ሊገፉ አይችሉም” ሲሉ ነው የሚያረጋግጡት።

የአሜሪካ ደኅንነት ይፋ ያደረገው ሰነድ እአአ በ2019 በዉሃን የሚሠሩ ብዙ ተመራማሪዎች “ጉንፋን” ታመው እንደነበር ማስረጃ እንዳለ ይጠቁማል።

ፕ/ር ሺ በ2020 በቤተ ሙከራቸው የሚሠሩ ሠራተኞችን ኮሮናቫይረስ መርምረዋቸው ሁሉም ነጻ እንደሆኑ ፕ/ር ዋንግ ያስረዳሉ።

ፕ/ር ዋንግ የሚያምኑት በዉሃን በሚገኝ ገበያ ቫይረሱ ወደ ሰዎች እንደተላለፈ በቂ ማስረጃዎች እንዳሉ ነው።

የዓሣ ዝርያዎች የሚሸጡበት ገበያ የዱር እንስሳትን ጨምሮ ሌሎችም እንስሳት ይሸጡበታል።

መጀመሪያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በዚያ ገበያ የሚሠሩ ወይም ከገበያው የሸመቱ ናቸው።

ቻይና በግልጽነት መረጃ እያወጣች አይደለም።

መጀመሪያ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች በተገኘው መረጃ፣ እንዲሁም ከገበያው በተወሰዱ ከባቢያዊ ናሙናዎች መሠረት ከቤተ ሙከራ ቫይረሱ አምልጧል የሚለውን የሚጠራጠሩ ሳይንቲስቶች አሉ። ለዚህም በቂ ማስረጃ እንዳለ ይናገራሉ።

በ2020 አንድ የጥናት ወረቀት ወጥቶ ነበር። ጥናቱ ይህንን መላ ምት የሚያጠናክር ነው። መላ ምቱ ከመጀመሪያው የቫይረሱ መነሻ ጊዜ አንስቶ እንደነበር ይጠቁማል።

ባለንበት የኢንተርኔት ዘመን እጅግ አወዛጋቢ ከሆኑ ሳይንሳዊ ጥናቶች አንዱ እንደሆነ ይገለጻል።

"The Proximal Origin of Sars-Cov-2" የተባለው ጥናት “ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ጋር የተያያዘ ነው የሚለው አሳማኝ መላ ምት አይደለም” ይላል።

ከቤተ ሙከራ ቫይረሱ አምልጧል የሚለው የሴራ ትንታኔ እንደሆነ የሚጠቁሙ ዘገባዎችም መሰራጨት ጀመሩ።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕ/ር ኢን ሊፕኪን፣ በመላው ዓለም የበሽታዎችን መነሻ በማጥናት ይታወቃሉ።

ቻይና ውስጥም ሠርተዋል።

ቫይረሱ የተነሳው ከገበያው እንደሆነ ጠንካራ እምነት ቢኖራቸውም፣ ሁሉም ከቤተ ሙከራ ጋር የተያያዙ መላ ምቶች በአጠቃላይ ገና መሰረዝ እንደሌለባቸው ይገልጻሉ።

ቫይረሱ የተነሳው ከገበያው ነው ማለት ቫይረሱ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው የሚለውን እምነት የሚቃረን አቋም ነው።

የእሳቸው መላ ምት ሌላ የዉሃን ቤተ ሙከራን ይመለከታል።

በዉሃን የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል የሚመራ ቤተ ሙከራ ላይ ነው ትኩረታቸው።

ቤተ ሙከራው ከዉሃን የባሕር ውስጥ እንስሳት ገበያ በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል።

ከዱር የሌሊት ወፎች የተሰበሰበ በሺዎች የሚቆጠሩ የደም አና የሰገራ ናሙና በቤተ ሙከራው አለ።

ምርምሮች አንዳንዴ ያለ ጥንቃቄ ሊከናወኑ ይችላሉ። ይህም በሽታውን ያስተላልፋል።

“እዚያ የሚሠሩት ሰዎች ዋሻ ውስጥ የሌሊት ወፍ እየሰበሰቡ ሳሉ በበሽታ ተይዘው ሊሆን ይችላል” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

በ2020 የጥናት ጽሑፍ ሲሠሩ ይህ ቤተ ሙከራ እንዳለ አላወቁም ነበር።

ምርምራቸው ቫይረሱ የተነሳው ከገበያው እንደሆነ ይጠቁማል።

በገበያው የሚገኙ የራኩን ውሻዎች የቫይረሱ መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ የቅርብ ጊዜ ግኝታቸው ያመላክታል።

“ቫይረሱ ከገበያው ውጪ ተነስቶ በገበያው ተስፋፍቶ ይሆናል” ይላሉ።

ፕሮፌሰር ጆርጅ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምልጧል የሚለውን መላ ምት ውድቅ አታድርጉት ማለታቸው ከቻይና ፖሊሲ ጋር የሚጻረር ይመስላል።

በዩናይትድ ኪንግደም የቻይና ኤምባሲ “ከቤተ ሙከራ አምልጧል የሚለው መላ ምት በቻይና ጠሎች የተፈጠረ ነው። ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው እና ፖለቲካዊ ነው” ሲል መልሷል።

የቻይና ፕሮፓጋንዳ መልስ በመረጃ ያልተደገፈ ራሱን የቻለ መላ ምት ነው።

ቫይረሱ የተነሳው ከቤተ ሙከራው ወይም ከገበያው ሳይሆን ከውጭ አገር ወደ ቻይና ከገባ የደረቀ ምግብ ማሸጊያ ጋር እንደሚያያዝ ነው የቻይና መላ ምት።

የፕሮፌሰሩ ምላሽ የቻይና አቋም ሳይንሳዊ ገጽታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ፕሮፌሰሩ የትኛውንም መላ ምት ውድቅ አያደርጉም። በቂ ማስረጃ ነው ያጡት።

“ቫይረሱ ከየት እንደመጣ አናውቅም። አሁንም ጥያቄው አልተመለሰም” ይላሉ።

ቻይና ለቫይረሱ መነሻ በቂ ማስረጃ ለማግኘት አልሞከረችም ወይም በይፋ አላጋራችም ብለው የሚተቹ ብዙ ናቸው።

በቫይረሱ ለሞቱ፣ ለተጎዱ እና አሁንም እየተጎዱ ላሉ ሰዎች ቫይረሱ ከየት መጣ? የሚለውን ማወቅ ዋጋ አለው።