ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስካሁን ግማሽ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በኮቪድ-19 ሲያዙ ከ7 ሺህ በላይ ሞተዋል
በቅርቡ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑ እንዳበቃ የታወጀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ሲያጠቃ የ7 ሺህ 574 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ተገለጸ።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ያስከተለውን ሞትና የጤና ቀውስ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የተሠሩ ተግባራትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ትናንት ሚያዝያ 30/ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው ይህ የተገለጸው።
የዓለም ጤና ድርጅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የቀጠፈው እና ለሦስት ዓመት ያህል የቆየው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አጣዳፊ የዓለም የጤና ስጋት መሆኑ እንዳበቃ ሚያዝያ 27/ 2015 ዓ.ም አስታውቋል።
አገሪቷ የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ታካሚ ከመዘገበችበት ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ5.5 ሚሊዮን በላይ የላብራቶሪ ምርመራ አከናውናለች።
በዚህ ምርመራ መሠረት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት በኮቪድ-19 ሲያዙ 7 ሺህ 574 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸቸው አልፏል።
በጽኑ ታመው በበሽታው ካገገሙት መካከል 6 በመቶ የሚሆኑት ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የጤና እክል እንደገጠማቸውም የጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
ለረዥም ጊዜ የሚዘልቀው የጤና እክል ለሳምንታት፣ ለወራት፣ ወይም ለዓመታት የሚቆይ ሲሆን ውስብስብ የሆኑ የጤና ችግሮችን ያስከትላል።
ለረዥም ጊዜ የሚዘልቁ ኮቪድ ሕመሞች ከሚባሉት መካከል ከፍተኛ ድካም፣ የደረት ላይ ሕመም፣ የማሰብ ወይም የአትኩሮት ማነስ፣ የእንቅልፍ ችግር፣ ድብርት፣ የጡንቻ ሕመምና ሌሎች ከበድ ያሉ የጤና እክሎች ይገኙበታል።
ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መከላከያ የሆነውን ክትባት ካስገባች በኋላ 44 ሚሊዮን 285 ሺህ 561 ሰዎች አንድ ዶዝ ሲከተቡ፣ 37 ሚሊዮን 96 ሺህ 736 ተከታታይ ክትባቶችን እንዲሁም ከ3 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የማጠናከሪያ ክትባቶችን ወስደዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ጥር 21/ 2012 ዓ.ም ኮቪድ-19ን ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የኅብረሰተብ የጤና ስጋት ብሎ ከፈረጀበት ወቅት ጀምሮም ኢትዮጵያ ስርጭቱን ለመግታት፣ በሽታውን እና ሞት ለመቀነስም ስትሠራ መቆየቷንም መግለጫው አስታውሷል።
አገሪቷ በነዚህ ዓመታት ስታከናውናቸው ከቆዩ ተግባራት መካከል የማኅበረሰብ ግንዛቤን ማሳደግ፣ ወደ አገር ውስጥ መግቢያ ኬላዎች ምርመራ ማካሄድ፣ የቅኝት ሥርዓት መዘርጋት፣ የላብራቶሪ ምርመራ አቅምን ማሳደግ፣ የሕክምና አቅምን መጨመርና እንደ ትምህርት ተቋማት ሆቴሎች እና የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመሳሰሉ ህዝባዊ መገልገያዎችን ወደ ጊዜያዊ ማዕከልነት መቀየሯም ተጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የስርጭት መግቻ ሂደትንም በመከተሏ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎችን ማስተናገድ እንዳስቻላት የጠቆመው ይህ መግለጫ በተጨማሪም የጤና፣ የማኅበራዊ እና የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴዎችም ሳይገታም ቀጥላለች ብሏል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 የሚጠቁ፣ በጽኑ የሚታመሙ እንዲሁም የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 እንደ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሆኖ የሚቀጥል ጉዳይ ነው ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑ ቢነሳም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሳርስ ኮቪድ-2 የሚያዙ፣ በርካቶችም የሚሞቱና እንዲሁም አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያም ሊከሰትበት የሚችልበት ስጋት በመኖሩም አገሪቷ ሌሎችንም ጥረቶች እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
የኮቪድ-19 ስርጭት፣ ሕመምና ሞትን ለመቀነስና በሽታውንም ለመከላከል የምትሠራቸው ተግባሮችም እንደማይቋረጡና ኅብረተሰቡም የወረርሽኙን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ እንዲቀጥልም መግለጫው አሳስቧል።
ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በጤና ተቋማት ውስጥ በነጻ የሚሰጠውን የኮቪድ-19 ክትባትም እንዲወስዱ ጥሪ ቀርቧል።
ኢትዮጵያ በቀጣይነትም በሚቀጥለው የምላሽ ምዕራፍ የምትከተላቸውን አቅጣጫዎችም አስቀምጣለች።
በዚህም መሠረት ወደፊት ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች እና ወረርሽኞች አቅምን በበለጠ ማጠናከር እንዲሁም የኮቪድ-19 ክትባትን ከመደበኛ የክትባት ጋር ማቀናጀት ሰፍሯል።
በተጨማሪም የኮቪድ-19 ቅኝት እና ምላሽ ተግባራትን ከመደበኛ የጤና ፕሮግራሞች ጋር ማቀናጀትና የሕክምና ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረውን ጅማሮ ማጠናከርም እንደ ሌላ አቅጣጫ ተጠቅሷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣናት ከሁለት ዓመት በፊት ጥር ወር ላይ በበሽታው ሰበብ በሳምንት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ለሕልፈት ይዳረጉ እንደነበረና በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ አሐዙ ወደ 3 ሺህ 500 መውረዱን ከሰሞኑ አስታውቀዋል።
የተቋሙ ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ዓለም ቢያንስ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል።
ነገር ግን ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር በይፋ ከተጠቀሰው ከሦስት እጥፍ በላይ በመሆን ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ሳይሆን እንደማይቀር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ጨምረውም ቫይረሱ አሁንም ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኖ ይቀጥላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።