ኮቪድ-19 አጣዳፊ የዓለም የጤና ስጋት መሆኑ ማብቃቱ ታወጀ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው እና ለሦስት ዓመት ያህል የቆየው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ “አጣዳፊ የዓለም የጤና ስጋት” መሆኑ እንዳበቃ የዓለም ጤና ድርጅት አወጀ።

ይህ ውሳኔ ከሦስት ዓመታት በፊት ቫይረሱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ጊዜ የታደወጀው የወርወሽኙ ስጋት ወደ ማብቃቱ መቃረቡን ያመላከተ ወሳኝ እርምጃ ነው ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣናት እንዳለው፣ ከሁለት ዓመት በፊት ጥር ወር ላይ በበሽታው ሰበብ በሳምንት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ለሕልፈት ይዳረጉ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ አሃዙ ወደ 3,500 ወርዷል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ዓለም ቢያንስ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል።

ነገር ግን ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር በይፋ ከተጠቀሰው ከሦስት እጥፍ በላይ በመሆን ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ሳይሆን እንደማይቀር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ጨምረውም ቫይረሱ አሁንም ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኖ ይቀጥላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

“ለ15ኛ ጊዜ የተሰበሰበው የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ በሽታው ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑ ማብቃቱን እንዳውጅ ወስኗል። ስለዚህም ከታላቅ ተስፋ ጋር ኮቪድ-19 አጣዳፊ የዓለም የጤና ስጋት መሆኑ እንዳበቃ አውጃለሁ” ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ።

ከፍተኛው የበሽታው የማስጠንቀቂያ ደረጃ መነሳቱ በሽታው የደቀነው አደጋ ተወግዷል ማለት እንዳልሆነ ያስጠነቀቁት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ያለው ሁኔታ ተለውጦ ከተባባሰ የስጋትነት ማስጠንቂያው መልሶ ሊታወጅ ይችላል።

“አገራት ይህንን ዜና ተከትለው የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ከተዉ፣ የዘረጉትን ሥርዓት ካስወገዱ ወይም ዜጎቻቸው ስለኮቪድ-19 እንዳይጨነቁ መልዕክት ካስተላለፉ መጥፎ ነገር ሊከሰት ይችላል” ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድን በተመለከተ የመጀመሪያውን የሕዝብ ጤና ስጋትነት ማስጠንቀቂያን ያወጣው በጥር ወር 2012 ዓ.ም. ነበር።

ወረርሽኙን በመግታት በኩል ተግባራዊ የተደረጉት ክትባቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከበሽታው ከባድ ህመም እና ሞት ለመከላከል አስችለዋል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን የመሳሰሉ አገራት ምርመራን እና ማኅበራዊ ቅርርብን በተመለከተ ያስቀመጧቸውን ግዴታቸው በማንሳት “ከቫይረሱ ጋር መኖር የሚቻልበትን መንገድ” እያበረታቱ ነው።

አስካሁን በበርካታ የዓለም አገራት ውስጥ ክትባቱ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አልተዳረሰም።

የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ፕሮግራም ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማይክ ርያን፣ “የኮቪድ አጣዳፊ ስጋትነት አብቅቶ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን አደጋው አሁንም አብሮን አለ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“ቫይረሱ መተላለፉን እንደሚቀጥል እንጠብቃለን፤ ከዚህ ቀደም ያጋጠሙ ወረርሽኞች እስኪጠፉ ድረስ አስርት ዓመታትን እንደፈለጉ የወረርሽኞች ታሪክ ያስረዳናል።

“በአብዛኛው ጊዜም ወረርሽኞች በትክክል የሚያበቁት ቀጣዩ ወረርሽኝ ሲጀምር ነው” ብለዋል።