ከዋክብትን ከመግዛት የክለብ አውቶብሶችን ወደ መሸጥ የወረደው የቻይናው ሱፕር ሊግ

የ29 ዓመቱ ብራዚላዊ ሃልክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እአአ ሰኔ 2016 ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ እግር ኳስ ደጋፊዎች በሻንጋይ አውሮፕላን ማረፊያ ተሰብስበዋል።

ታዋቂ ከሆኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱን ከተማዋን መኖሪያው ለማድረግ በመምረጡ አቀባበል ሊያደርጉለት ነው የተሰባሰቡት።

የ29 ዓመቱ ብራዚላዊ ሃልክ በብቃቱ ጣራ ላይ እያለ ነው ለሻንጋይ ኤስአይፒጂ ለመፈረም የተስማማው።

ስቬን-ጎራን ኤሪክሰን የክለቡ አሰልጣኝ ነበሩ። ለሃልክ ዝውውር ከ46 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ ተደርጎ ነበር።

ስምምነቱ በሳምንት 320 ሺህ ፓውንድ ደሞዝ እንደሚያስገኝለት ሪፖርት ተደርጓል።

አየር ማሪፊያውን አቋርጦ ሲወጣ በአበባ እቅፍ አቀባበል ተደረገለት። የሻንጋይ ኤስአይፒጂ ስካርፍ አንገቱ ላይ ተጠለቀለት።

በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ሃልክን በርካታ ትልልቅ ተጫዋቾች ተከትለውት ቻይና ደርሰዋል። አንዳንዶቹ የዝውውር ዋጋ ከብራዚላዊው በለጠ ጭምር ነው።

የቼልሲው ኮከብ ኦስካር ከስድስት ወራት በኋላ ቻይና ደረሰ። ለዝውውሩ ተከፈለው 60 ሚለዮን ፓውንድ ገደማ ሲሆን ሳምንታዊ ደመወዙ ደግሞ 400 ሺህ ፓውንድ እንደነበር ይታመናል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከማንቸስተር ዩናይትድ እና ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው ካርሎስ ቴቬዝ ወደ ቻይና ሲያቀና ከዚህ የበለጠ ደመወዝ እንዳገኘ ተዘግቧል።

የፓሪስ ሴንት ዠርሜይኑ ኮከብ ኢዝኪኤል ላቬዚ፣ ሊቨርፑል ሊያስፈርመው የነበረው አሌክስ ቴክሴራ እና ኮሎምቢያዊው አጥቂ ጃክሰን ማርቲኔዝ በከፍተኛ የዝውውር ክፍያ እና ደመወዝ ቤጂንግ ደርሰዋል።

ሱፐር ሊጉ መነቃቃት የጀመረው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ አገሪቱን ወደ እግር ኳስ ማዕከልነት ለመቀየር ካላቸው ፍላጎት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።

እአአ በ2011 የወንዶቹ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ እንዲበቃ እና ቻይናም ውድድሩን እንድታዘጋጅ ማቀዷን አስታወቁ።

ሱፐር ሊጉ በርካታ ገንዘብ ማውጣት ሲጀምር አገሪቱን ወደ እግር ኳስ ልዕለ ኃያልነት የመቀየር ፍላጎታቸው እውን መሆን የጀመረ መሰለ።

ኦስካር ወደ ቻይና ማቅናቱን የተመለከቱት የወቅቱ የቼልሲ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ "የቻይና ገበያ ለቼልሲ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ክለቦች በሙሉ አደጋ ነው" ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል።

"ቻይና ሁሉንም የአውሮፓ ሊግ ወደ ቻይና ለማዘዋወር የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ያላት ትመስላለች" ሲሉ የአርሰናል አሰልጣኝ የነበሩት አርሰን ቬንገር ተናገሩ።

ብዙ የተወራለት ይህ ሱፐር ሊግ፣ አስር ዓመት ሳይሞላው ጉዞው በተቃራኒው አቅጣጫ ሆኖ ተስፋው መፈረካከስ ጀመረ።

ጃክ ሲሊ ትልቅ ስም ካላቸው የቻይና ፈራሚዎች መካከል አይመደብም። የቀድሞው የኪውፒአር አጥቂ ቶኒ ሲሊ ልጅ ሲሆን ለሲኤስኤል ቻንግቹን ያታይ በ2015 ፊርማውን አኑሯል።

28 ዓመቱ የነበረው ሲሊ በሆንግ ኮንግ ይጫወት ነበር። ወደ ሱፐር ሊግ የተሳበው ሊጉን በተቀላቀሉ ትልልቅ ተጫዋቾች፣ በከፍተኛ የእግር ኳስ ደረጃው እና ባለው ከፍተኛ ገንዘብ ነበር።

"ወደዚያ ያቀናሁት ገና ሊጉ በማደግ ላይ እያለ ነበር። ስለዚህ በወቅቱ እዚያ መሆን በጣም አስደሳች ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ሰዎች ስለ ጉዳዩ ከዚህ በፊት ሰምተው ሊሆን ይችላል። ማንም ግን በትክክል የሚያውቀው አልነበረም። እናም እግር ኳስን ለሚያውቅ ሰው ብትናገር 'ኦህ ዋው፣ ወደ ሱፐር ሊግ ልትሄድ' ይላል።”

"በዚህ ጉዳይ ምንም አልተጸጸትም። በጣም አስደናቂ ነበር።"

ተጫዋቾች በግጥምያ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አስደናቂ ግን ደግሞ እንግዳ ነገር ነው።

“አንተ ማንነታቸውን ሙሉ በሙሉ መርሳት አለብህ” ሲል ስለአንዳንድ ታዋቂ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች አክሏል።

"ወይ አንተ አድገሃል ወይም እነሱ ዝቅ ብለዋል። ካንተ እኩል እንደሆኑ በማሰብ የተቻለህን ሁሉ ትሞክራለህ። ግን ህልም አልነበረም።”

"ኦስካር ለቼልሲ ሲጫወት ተመልክቼዋለሁ። ፊፋን (እግር ኳስ ጌም ነው) ከመጫወት ጀምሮ ሁሉንም ተጫዋቾች ታውቃለህ። በጣም የሚገርም ነበር።"

እአአ በ2019 ሊጉ በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ ደረሰ። በአንድ ወቅት የዓለማችን ውዱ ተጫዋች የነበረውን የሪያል ማድሪዱ ጋሬዝ ቤልን ወደ ጂያንግሱ ሰኒንግ ለማዘዋወር አቀደ። የሦስት ዓመት ኮንትራት በመስጠት በሳምንት አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ነበር ዕቅዱ።

ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን ጂያንግሱ ሱኒንግ በደረሰበት የፋይናንስ መቃወስ ሥራ አቆመ። የቡድኑን አውቶብስ ለመሸጥ ጨረታ እስከማውጣት ደረሰ።

የቻይና እግር ኳስ ትዕይንት በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዴት ታየ?

ትላልቅ የገንዘብ ዝውውሮችን የማይቀመስ የሚያደርግ እና ስፖንሰሮችን በራሳቸው ስም እንዳይሰይሙ የከለከለውን 'የቅንጦት ታክስ' ያስተዋወቀው የቻይና እግር ኳስ ማህበር በታህሳስ 2020 ደግሞ የደመወዝ ጣሪያ ይፋ አደረገ።

እርምጃው የገንዘብ እግር ኳስን እንደሚገድብ እና በቻይና ብሔራዊ ቡድን ላይ "የኢንቨስትመንት ተስፋ" እንደሚፈነጥቅ ሲኤፍኤ ተስፋ አድርጎ ነበር።

የቻይና ስፖርት ሚኒስቴር የሊጉን ወጪን በተመለከተ ጥንቃቄ ሲያደርግ ነበር። እአአ በ 2017 ወጪዎችን ለመግታት እና "ምክንያታዊ ያልሆነ ኢንቨስትመንት" ለመቆጣጠር ቆረጠ። ክለቦች "ገንዘብ ያባክናሉ" እና ለውጭ ተጫዋቾች "ከልክ በላይ ደመወዝ" ይከፍላሉ ሲል ይከሳል።

የደመወዝ ጣሪያ ማውጣት የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል። በገደቡ መሠረት የባህር ማዶ ተጫዋቾች በሳምንት የሚያገኙት ከፍተኛ ደመወዝ 52 ሺህ እንዲሆን ተወሰነ። ይህም ቀደም ሲል ለከዋክብት ተጫዋቾች ከቀረቡት ኮንትራቶች በጣም ያነሰ ነው።

በዕዳ ውስጥ ለተዘፈቁት አንዳንድ ቡድኖች እንደዚህ አይነት እገዳዎች ያስፈልጋቸው ነበር።

የብዙ ክለቦች ባለቤቶች በሪል ስቴት ውስጥ ይሳተፋሉ። በገንዘብ ፍሰት ምክንያት ያልተረጋጉት ባለሃብቶች የክለቦቹን ችግሮች የከፋ አድርጎታል።

በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝ ተጨመረበት።

የቻይና ጥብቅ ቁጥጥር ፖሊሲዎች የጨዋታ ፕሮግራሞችን ቀንሰዋል። ጨዋታዎችም ከሁለት ዓመት በላይ በዝግ ስታዲየሞች እንዲደረጉ አስገድዷል። የብሮድካስት እና የስፖንሰርሺፕ ገቢዎችም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

ተጫዋች እና ዳኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቦስኒያ-ሄርዞጎቪናው ተከላካይ ሳሚር ሜሚሴቪች ከየካቲት 2020 ጀምሮ ለሄቤይ ተጫውቷል። በክለቡ በቆየበት በሁለተኛው የውድድር ዘመን በስተጀርባ ችግሮች እንዳሉ ተመልክቷል።

"በሁለተኛው የውድድር ዘመን የሆነ ችግር እንዳለ ተሰምቶኝ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ከጥቂት ወራት በኋላ የፋይናንስ ችግሮች መታየት ጀመሩ። ቻይናውያን ተጫዋቾች ላይ ትልቅ ችግር ገጠማቸው። ለብዙ ወራት ደመወዝ አልከፈላቸውም። በዚያ ዓመት መጨረሻ ላይ ሄቤይ እንደክለብ እንደማይቀጥል እርግጠኛ ነበር።"

ሜሚሴቪች ከሊጉ ትልቅ ክለቦች አንዱ ለሆነው ቤጂንግ ጉዋን በውሰት እንዲሄድ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀበለ።

ላቬዚን፣ እና የቀድሞ የፕሪሚየር ሊግ ተጨዋቾችን ሃቪየር ማሼራኖን እና ዠርቪንሆን ያስፈረመው ሄቤይ በሊጉ ለመቆየት በማሰብ የወጣት ቡድኖቹን በተነ።

የክለቡ ባለቤት የሆነው ሪል ስቴት በዕዳ ቢዘፈቅም ለወራት ደመወዝ ያለገኙ ሠራተኞቹ ለክለቡ በነጸ ለመሥራት ጥሪ እስከማቅረብ ደርሰዋል።

ሁሉም ነገር ግን አልተሳካም። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሄቤይ ተበታተነ።

አሁን ዱባዩ ለአል ናስር የሚጫወተው ሜሚሴቪች "በሄቤይ ለተፈጠረው ነገር በጣም አዝናለሁ። ምክንያቱም ትልቅ ስም እና ገንዘብ ካላቸው ትላልቅ ቡድኖች መካከል አንዱ ነበሩ።"

"አሁን ሙሉ ለሙሉ የለም።በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ይህ ግን የብዙ የቻይና ክለቦች ታሪክ ነው። ጓንግዡ እና ዉሃንንም እየፈረሱ ነው። በጣም ያሳዝናል።”

"ብዙ ገንዘብ ስላፈሰሰ የቻይና እግር ኳስ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ግን እንደ በፊቱ አይነት ይሆናል ብዬ አላስብም።"

ለጓንግዡ ሲቲው ደጋፊ ጆን ሃሴት የቻይና ሱፐር ሊግ ከአሁን በኋላ እንደዚህ ቀደሙ አይሆንም። በኤሪክሰን እና በቀድሞው የአርሰናል እና የሬንጀርስ ኮከብ ጆቫኒ ቫን ብሮንክሆስት ሲሰለጥን የነበረው ክለብ በመጋቢት ወር ከስሟል።

በእያንዳንዱ በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ሀሴት ከሌሎች ደጋፊዎች ጋር ለመገናኘት እና ቡድኑን ለማበረታታት ይጓጓል።

"ለበርካታ ሰዎች ማህበራዊው ሁኔታ የእግር ኳሱን ያህል አስፈላጊ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"አነስተኛ ሱቅ ከስቴዲየሙ ውጭ ስለነበረን ከጨዋታው በፊት እና በኋላ እዛ እንጠጣ ነበር።”

"ሁላችንም በግነናል። ክለቡ ከተዘጋ በኋላ እዚያ ተገናኝተዋል። ከሌሎች ቡድኖች ጋር ተገናኘን እና ከስታዲየም ውጭ ቢራ ጠጥተናል። ጥሩና አዝናኝ ነበር።”

"የችግሩ የትኛውም ክለብ ገንዘብ ለማግኘት ራሱን አላዘጋጀም ነበር።”

"ትኬት በጣም ርካሽ ነው። የአንድ የውድድር ዘመን ትኬታችን ዋጋ 50 ወይም 60 ፓውንድ ነበር። አንዳንድ ተማሪዎች ትኬቶችን ከዛም በረከሰ ዋጋ ይገዙ ነበር። አብዛኛዎቹ ደጋፊዎች ይፋዊ ማሊያ አይገዙም። ከስታዲየም ውጪ በሦስት ፓውንድ ይገዛሉ።”

"የክለቦች ገቢ ማመንጨት ችግር ሱፐር ሊጉ ትልቁ ፈተና ነው። ኢኮኖሚው እየዋዠቀ ሲሄድ ገንዘቡ ከየት ነው የሚመጣው?"

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ስታዲየሞች በድጋሚ ለደጋፊዎች መከፈት ሲጀመሩ፣ ሌላ ጥያቄ ይነሳ ጀመር። ገንዘቡ የት ጠፋ?

በሀገር ውስጥ ሊግ ከፍተኛ ኃላፊዎች ዘንድ ሙስና ተንሰራፍቷል።

የቀድሞው የኤቨርተን አማካይ እና የቻይና ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሊ ቲዬ ጉቦ በመስጠት “ከባድ የህግ ጥሰት” ምርመራ ተካሂዶበታል።

የቀድሞው የቻይና እግር ኳስ ማህበር ሊቀመንበር ቼን ዡዩአን ተመሳሳይ ውንጀላ እየቀረበባቸው ነው። ለሻንዶንግ ታይሻን የተጫወተው የደቡብ ኮሪያው አማካይ ሶን ጁን-ሆ ጉቦ በመቀበል ተጠርጥሮ ከግንቦት ወር ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ በሊጉ የቀሩት ጥቂት የውጪ ተጫዋቾች ብቻ ናቸው። አሁን በቻይና የሚጫወቱት የአገር ውስጥ እና የውጭ ተጫዋቾች ከቢቢሲ ለቀረበላቸው የቃለ መጠይቅ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

የሊጉ ችግር እንዳለ ቢሆንም ለአገር ውስጥ እግር ኳስ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው።

የቤጂንግ ጉዋን ከኮቪድ በኋላ ደጋፊዎች ወደ ስታዲም በተመለሱበት የመጀመሪያ ጨዋታ የቲኬት ሽያጭ በአምስት ደቂቃ ተጠናቋል።

ደጋፊዎች

ከላሊ ጋ ጋር በቻይና የሠራው እና በእስያ እንደ ወኪል ሆኖ ያገለገለው አልቤርቶ ዶልዳን በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ቡድኖች በአሁኑ ጊዜ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የቻይና ሱፐር ሊግን የሚያስታውስ ነው ብሏል።

የቻይና ሊግ በአንድ ወቅት ሊያሳከው ካለመው የተለየ ቢሆንም አሁንም ተስፋ እንዳለው አጥብቆ ተናግሯል።

"በቻይና ብዙ ቡድኖች በፋይናንስ ችግር ከስዋል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ከወጣት ተጫዋቾች ጋር ሲሠሩ ስለነበር ወደፊት የተሻሉ ይሆናሉ። በሚቀጥሉት አምስት፣ ስድስት ወይም ሰባት ዓመታት ውስጥ ጥራት ያላቸው ብዙ የአገር ውስጥ ተጫዋቾችን እናገኛለን።”

"ቻይና አሁንም ጥሩ ቦታ ነች። መጪው ጊዜ ለአገር ውስጥ ተጫዋቾች የሚሆን ይመስለኛል።"

አሁን ወደ ቻይና የሚያቀኑ ኮከቦች ቁጥር አነስተኛ ነው። ትኩረቱ የአገር ውስጥ ኮከቦችን በማፍራት ሊጉን ለማሳደግ እና አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ተሳተፉበት የዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድልን ለማሻሻል ነው።