ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፈረንሳዊያን በመላ ሃገሪቱ የሥራ አድማ ሊመቱ ነው

የፈረንሳይ የሥራ ማሕበራት የጡረታ ዕድሜ ከ62 ወደ 64 ማደጉን ተከትሎ ሰፊ ሰልፍ ጠርተዋል።

ዕለተ ማክሰኞ በፈረንሳይ የከተማና የክፍለሃገር ባቡር አገልግሎት እንዳይሰጥ ይሆናል፤ ትምህርት ቤቶችም ይዘጋሉ።

ማሕበራቱ ካለፈው ጥር ጀምሮ አምስት ጊዜ አድማ መተዋል። ይህ ስድስተኛውና ከፍተኛው አድማ ነው።

በመዲናዋ ፓሪስና በሌሎች ከተሞች ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ሰልፍ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፈረንሳይ መንግሥት የጡረታ ዕድሜን አስመልክቶ ያወጣውን ሕግ እንዲቀይር ቢጠየቅ እምቢኝ በማለቱ ማሕበራቱ ፈረንሳይን በተቃውሞ እንንጣታለን ብለው ተነስተዋል።

አንድ የሠራተኞች ማሕበር ኃላፊ “ሃገሪቱን እናንበረክካታለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በሚቀጥሉት ቀናት ትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን የመብራት ኃይልና የጋዝ ጣቢያዎችም አድማውን እንዲቀላቀሉ ተጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም የተደረጉት ሰልፎች ድምፃቸው ጎልቶ ቢሰማም የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት የሚጎዳ አቅም አልነበራቸውም።

በዚህ የተማመነ የሚመስለው የሃገሪቱ መንግሥት አዲሱን መመሪያ ለማፅደቅ ወደ እንደራሴዎች ምክርት ቤት መርቶታል።

መመሪያው ከመፅደቁ በፊት የሥራ ማሕበራቱ በተቃውሞ ሃገሪቱን አምሰው የመንግሥት እጅ ሊጠመዝዙ የቆረጡ ይመስላሉ።

አብዛኛዎቹ ፈረንሳዊያን ተቃውሞውን የሚደግፉ ናቸው ነው ሲል አንድ የሕዝብ ድምፅ ሰብሳቢ ድርጅት ገልጧል።

ድርጅቱ ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መሠረት 56 በመቶ ዜጎች አመፅ መጠራቱን ሲሹ 59 በመቶው ደግሞ ሃገሪቱ በአመፅ በአንድ እግሯ እንድትቆም ይፈልጋሉ።

ብቻ በጠቅላላው ሁለት ሶስተኛው ሕዝብ አዲሱን የኢማኑዔል ማኽሮን መንግሥት መመሪያ ተቃዋሚ ናቸው ይላል ድርጅቱ።

ፕሬዝደንት ማኽሮን አዲሱ የጡረታ መመሪያ “ያስፈልገናል” ሲሉ ይከራከራሉ።

የመንግሥት ቃል አቀባይ ኦሊቪዬ ቬራን “ተቃውሞው ለከባቢያዊ፣ ግብርና እና የጤና ቀውስ ይዳርገናል” ብለው ነበር።

በመላው ፈረንሳይ ከ260 በላይ የተቃውሞ ሰልፎችም ዕለተ ማክሰኞ ይካሄዳሉ ተብሎ ተገምቷል።

ከ1.4 ሚሊዮን ሰዎች በሰልፎቹ ይታደማሉ ይላሉ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ።

ፈረንሳይን የሚጎራበቷት የአውሮፓ ሃገራት የጡረታ መውጫ ዕድሜን 65 እና ከዚያ በላይ አድርገዋል።