ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስከ 18 ዓመቱ ማንበብ እና መጻፍ ሳይችል የቆየው በእድሜ ትንሹ ፕሮፌሰር ለመሆን በቃ
ያሰን አርዴ ልጅ ሳለ ኦቲስቲክ [የአእምሮ እድገት ውስንነት] እንዳለበት በሐኪም ተነግሮት ነበር።
እስከ 11 ዓመቱ መናገር አይችልም ነበር። 18 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ደግሞ ማንበብም ሆነ መፃፍ አይችልም።
እነሆ አሁን በ37 ዓመቱ በዩናይትድ ኪንግደም ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በዕድሜ ትንሹ ጥቁር ፕሮፌሰር ተብሏል።
ምንም እንኳ ልጅ እያለ መናገር ባይችልም ጥያቄ ከመጠየቅ አላገደውም።
“ለምንድነው ሰዎች ቤት አልባ የሚሆኑት? ጦርነት ለምን ይነሳል?” እያለ ይጠይቅ እንደነበር ያስታውሳል።
ክላፋም በተሰኘችው የለንደን መንደር ተወልዶ ያደገው ሶሺዮሎጂስቱ አርዴ አሁን ላለው ማንነቱ የኔልሰን ማንዴላ ከእሥር መለቀቅ እና ደቡብ አፍሪካ የ1995ቱን የራግቢ ዓለም ዋንጫ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገ ይናገራል።
“ህልሜ እግር ኳስ ተጫዋች መሆን አሊያም ፕሮፌሽናል ፑል [ቢሊያርድ] ተጨዋች መሆን ነበር። ካልሆነ ደግሞ ዓለምን ማዳን አለብኝ የሚል ምኞት ነበረኝ።”
እናቱ በራስ መተማመኑ እንዲጨምር እና ችሎታውን እያዳበረ እንዲሄድ ብዙ ደክማለች።
ቋንቋን የበለጠ መረዳት እንዲችል በልጅነቱ ሙዚቃን ታስትምረው ያዘች።
አርዴ ማንበብ እና መፃፍ የጀመረው በአስራዎቹ መጨረሻ በረዳቱ እና ጓደኛው ሳንድሮ ሳንድሪ እገዛ ነው።
ወደ ሰሬይ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ፈዚላክ ኤዱኬሽን እና ኤዱኬሽን ሳይንስ [የትምህርት ጥናት] የተባሉ የትምህርት ዓይነቶችን አጠና።
ያደገበት ሥፍራ ከሌሎች የለንደን ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚኖሩበት ነው።
ትምህርቱን እንደጨረሰ በአስተማሪነት ሥራ የጀመረው አርዴ ነጭ ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዴት ስልታዊ በመሆን መንገድ ፍትሕ እንደሚነፈጋቸው ይታዘብ ጀመር።
አርዴ በ22 ዓመቱ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ድግሪ መማር እንደሚልፈግ ለጓደኛው ያማክረው ነበር።
“ሳንድሮ 'ልታደርገው ትችላለህ። ዓለምን ልንረታት እንችላለን' ሲለኝ አስታውሳለሁ” ይላል።
“አሁን ሳስበው የዚያን ጊዜ ነው በራሴ ሙሉ በሙሉ ማመን የጀመርኩት። ብዙ ምሑራን በአጋጣሚ እዚህ እንደደረሱ ሲናገሩ እሰማለሁ። እኔ ግን ይህ ዕቅዴ ነበር።”
ነገር ግን መንገዶቹ አልጋ ባልጋ አልሆኑለትም። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ እንዴት አድርጎ ይህን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል የሚያውቀው ነገር የለም።
ቀን ቀን ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትምህርት ይሰጣል። ከሰዓት እና አመሻሹን ደግሞ ሶሺዮሎጂ እያጠና የትምህርት ፅሑፍ ያዘጋጃል።
“ገና ስጀምረው ምን እንደማደርግ አላውቅም ነበር። የሚያስጠናኝ አሊያም የሚያሳየኝ ሰው አልነበረም።”
ብዙዎቹ ያቀረባቸው ፅሑፎች ተቀባይነት ሳያገኙ ቀሩ። ነገር ግን ይሄ እሱን ወደኋላ የሚጎትተው እንቅፋት አልነበረም።
አርዴ፤ ውጣ ውረዱን አልፎ ሁለት የማስተርስ ድግሪ እና በትምህርት ጥናት የዶክትሬት ድግሪውን ጫነ።
ሶሺዮሎጂስት ከሆነ ከስምንት ዓመታት በኋላ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሶሺዮሎጂ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሊሰጠው ነው።
ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አምስት ጥቁር አስተማሪዎች የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አላቸው።
የትምህርት መረጃ ኤጀንሲ በ2021 ባወጣው መረጃ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከ23 ሺህ የዩኒቨርሲቲ አስማሪዎች መካከል 155ቱ ብቻ ናቸው ዘራቸው ከአፍሪካ የሚመዘዘው።
በሚቀጥለው ሳምንት በይፋ የፕሮፌሰርነት ማዕረጉን የሚቀበለው አርዴ ነጭ ያልሆኑ ሰዎችን ውክልና ለማሳደግ እንደሚሠራ ይናገራል።
“ትልቁ ትኩረቴ የሚሆነው ትምህርትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ እና ከባድ ሁኔታን አልፈው ለሚመጡ ሰዎች በር መክፈት ነው።”
አርዴ በፈረንጆቹ 2018 የመጀመሪያ ፅሑፉን አሳትሞ በሮሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግን አግኝቶ ወደ ደርሃም ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
በ2021 በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሶሺዮሎጂ ፕሮፌሰር በመሆን በዩናይትድ ኪንግደም ካሉ ወጣት ፕሮፌሰሮች መካከል አንዱ መሆን ችሎ ነበር።