ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በየመን ባካሄደችው የአየር ጥቃት ከ800 በላይ ዒላማዎችን መምታቷን አስታወቀች
የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በየመን የሁቲ ቡድን ዒላማዎች ላይ ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ወዲህ ባካሄደው የአየር እና የባሕር ዘመቻ ከ800 በላይ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በቅርብ ጊዜ በሁቲ እንቅስቃሴ ላይ ስለተደረጉት ጥቃቶች እሁድ ዕለት ባወጣው ሪፖርት ከመጋቢት 6/2017 ዓ.ም. በኋላ በተፈጸሙ ጥቃቶች "በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁቲ ተዋጊዎች እና በርካታ መሪዎቹ ተገድለዋል" ብሏል።
አሜሪካ እንዳለችው ይህንን የተጠናከረ ዘመቻ የወሰደችው በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚያቋርጡ መርከቦች ላይ የደቀኑትን ስጋት ለማስቆም ነው።
የየመንን አብዛኛውን ግዛት የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ትናንት እሁድ አሜሪካ በዋና ከተማዋ ሰነዓ ላይ በፈጸመችው አዲስ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር በሁቲ ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ሁቲዎች "ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመሰሱ" ዝተዋል።
ጨምረውም ኢራን የሁቲ በድንን ከማስታጠቅ እንድትቆጠብ ቢያስጠነቅቁም፤ ኢራን ግን የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ ስታስተባብል ቆይታለች።
የአሜሪካ ጦር እሁድ ባወጣው መግለጫ በተፈጸሙት ጥቃቶች የሁቲ የጦር መሳሪያ ማከማቻዎች እና ማምረቻዎች ከተመቱት ዒላማዎች መካከል መሆናቸውን ቢያመለክትም፣ ነገር ግን ስለቀጠለው ጥቃት ምንም "ዓይነት ዝርዝር" አላስቀመጠም።
አሜሪካ በሁቲዎች በቀይ ባሕር በኩል በሚያቋርጡ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እስኪያቆሙ ድረስ "የምታደርስባቸውን ጫና" እንደምትቀጥል አመልክታለች።
ባለፈው ዓመት ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል የሚያልፉ በርካታ የንግድ መርከቦች ላይ ሚሳኤል፣ ድሮን እና ትናንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም ጥቃት ፈጽመዋል። በዚህም ሁለት መርከቦችን አስምጠው፣ ሦስተኛውን በቁጥጥራቸው ሥር ከማዋላቸው በተጨማሪ አራት የመርከብ ሠራተኞችን ገድለዋል።
ሁቲዎች ለሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያቱ እስራኤል በጋዛ ላይ በምትፈጽመው ጥቃት ፍልስጤማውያንን በመደገፍ መሆኑን እና ዒላማ የሚያደርጓቸው መርከቦችም የእስራኤል፣ የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም የሆኑትን ብቻ ነው ቢሉም ይህ ግን ከእውነታው የራቀ ነው።
ይህ የሁቲዎች ጥቃት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቡድኑ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት እንዲፈጸም በማድረጋቸው ወይም ምዕራባውያን የጦር መርከቦቻቸውን በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ በማሰማራታቸው ሊገታ አልቻለም።
ባለፈው ጥር ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መንበራቸው ከተመለሱ በኋላ የሁቲ ኃይሎችን "የውጭ ሽብርተኛ ቡድን" በማለት ሰይመዋቸዋል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባይደን ግን በየመን ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማቃለል በሚል ይህንን የቡድኑን ፍረጃ አንስተውት ነበር።
የመን ከአስር ዓመታት በላይ በቆየው የእርስ በርስ ጦርነት የወደመች ሲሆን፣ የሁቲ ታጣቂዎች የአገሪቱን ሰሜን ምዕራባዊ ግዛትን ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው መንግሥት ነጥቀው ከተቆጣጠሩ በኋላ በሳዑዲ የሚመራው በአሜሪካ የሚደገፈው ጥምረት የየመንን መንግሥት ወደ መንበሩ ለመመለስ ዘመቻ ከከፈቱ በኋላ ጦርነቱ ተባብሷል።
በየመን እየተካሄደ ያለው ውጊያ ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነ ሲሆን በአገሪቱ ከባድ ሰብዓዊ አደጋን አስከትሏል።በዚህም 4.8 ሚሊዮን ሕዝብ ለመፈናቀል እንዲሁም 19.5 ሚሊዮን ወይም ግማሹ የአገሪቱ ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገዷል።