ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ ወታደሮችን ማሰማራቷን አመነች

ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ዩክሬንን የሚዋጉ ወታደሮችን መላኳን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋገጠች።

በመንግሥታዊው የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ላይ አገሪቱ ጦር ባሠራጨው ዘገባ ወታደሮቹ በመሪው ኪም ጆንግ ኡን ትዕዛዝ የኩርስክን ክልል "ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲያወጡ" ረድተዋል ሲል ገልጿል።

የፒዮንግያንግ ይህንን ያሳወቀችው የሩሲያ አዛዥ ቫለሪ ጌራሲሞቭ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን "ጀግንነት" ካደነቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲሆን፣ ይህም ሞስኮ ተሳትፏቸውን በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳወቀችበት ሆኗል።

ከሰሜን ኮሪያ ከተላኩት 11 ሺህ ወታደሮች መካከል ቢያንስ አንድ ሺህ ያህሉ በሦስት ወራት ውስጥ መገደላቸውን እንደሚያምኑ ቀደም ሲል የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሄራሲሞቭም አክለውም ሞስኮ የኩርስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ መልሳ መቆጣጠሯን ተናግረዋል። ይህ ግን በዩክሬን ውድቅ ተደርጓል።

ለመግለጫው ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ጦርነቱን በማስቀጠሏ ኃላፊነቱን መሸከም አለባት ብላለች።

ባለፈው ዓመት ፒዮንግያንግ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ኩርስክ መላኳን የደቡብ ኮሪያ እና የምዕራቡ ዓለም አገራት ዘግበዋል።

ወታደሮችን ለማሰማራት የተወሰነው በፒዮንግያንግ እና በሞስኮ መካከል በተደረገው የጋራ የመከላከያ ስምምነት መሠረት ነው ሲል ኬሲኤንኤ ዘግቧል።

"ለፍትህ ሲሉ የተዋጉት በሙሉ ጀግኖች እና የእናት ሀገር ክብር ተወካዮች ናቸው" ሲሉ ኪም መናገራቸውን ኬሲኤንኤ አክሏል።

ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ "ጥምረት እና ወንድማማችነታቸውን" በኩርስክ ያሳዩ ሲሆን "በደም የተረጋገጠ የወዳጅነት" ግንኙነታቸውን "በሁሉም መንገድ" ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ሰሜን ኮሪያ የሩሲያ ጦርን በድጋሚ እንደምትደግፍም አክሏል።

የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የኩርስክ ተልዕኳቸው ካበቃ በኋላ ምን እንደሚሆኑ እና ወደ አገር ቤታቸው ስለመመለሳቸው ኬሲኤንኤ አልዘገበም።

በኪም እና ፑቲን መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከርን ተከትሎ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሩሲያ ጎን ለመሰለፍ መሰማራታቸውን የሚገልጹት ዘገባዎች በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር ብቅ ማለት የጀመሩት።

ይህም የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን ሁለቱም አገራት "ጥቃት" ከተሰነዘረባቸው እርስ በርስ ለመደጋገፍ የተስማሙበትን ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።

ስቶርም ኮርፕስ ከተባለው "ከፍተኛ" ክፍል እንደተወጣጣ የተነገረለት የሰሜን ኮሪያ ጦር ለዘመናዊ ጦርነት ዝግጁ እንዳልሆነ ወታደራዊ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

"እነዚህ ብዙም ያልሠለጠኑ ወታደሮች በይግባቧቸው በሩሲያ መኮንኖች የሚመሩ ናቸው" ሲሉ የቀድሞው የብሪቲሽ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ሃሚሽ ደ ብሬተን ጎርደን ከወራት በፊት ተናግረው ነበር።

የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሲርስኪ በበኩላቸው የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ግንባር ላይ ላሉ የዩክሬን ተዋጊዎች ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸው አስጠንቅቀዋል።

"እነሱ ብዙ ናቸው። ከ11 ሺህ እስከ 12 ሺህ ከፍተኛ ተነሳሽነት ያላቸው እና ጥሩ ዝግጅት ያላቸው ወታደሮች በማጥቃት ላይ ናቸው። በሶቪየት ስልቶች ላይ ተመሥርተው ይንቀሳቀሳሉ። በቁጥራቸው ይተማመናሉ" ሲሉ ጄነራሉ ለዩክሬኑ ቲኤስኤን ታይዥዴን ተናግረዋል።