ስፔስኤክስ ለሁለት ወራት ሕዋ ላይ የከረሙትን ጠፈርተኞች በሚቀጥለው ዓመት ወደ ምድር ሊመልሳቸው ነው

ከሁለት ወራት በላይ ሕዋ ላይ የቆዩትን የናሳ ጠፈርተኞች በሚቀጥለው ዓመት እንደሚመልሳቸው ስፔስኤክስ አሳወቀ።

የአሜሪካ የሕዋ ምርምር ተቋም ናሳ እንደገለፀው ሱኒታ ዊሊያምስ እና ባሪ ዊልሞር የተባሉትን ጠፈርተኞች ይዞ ወደ ሕዋ የሄደው ቦይንግ ስታርላይነር መንኩራኩር “ሰው ሳይጭን” ወደ ምድር ይመለሳል።

ሁለቱ ጠፈርተኞች አሁን ሕዋ ላይ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የሕዋ ምርምር ጣቢያ [አይኤስኤስ] ላይ ነው የሚገኙት።

ሁለቱ ጠፈርተኞች ባለፈው ሰኔ መባቻ ለስምንት ቀናት ቆይታ ነበር ወደ ሕዋ የመጠቁት። አሁን ግን ከስምንት ወር በላይ ሕዋ ላይ ሊቆዩ ይችላሉ።

ቦይንግ ስታርላይነር የተባለው መንኩራኩር ወደ አይኤስኤስ እያቀና ሳለ በገጠመው ችግር ምክንያት ነው ወደ ጠፈርተኞቹን ጭኖ መመለስ ያልቻለው።

ቦይንግ እና ስፔስኤክስ የተባሉት ተቋማት ጠፈርተኞችን ይዞ ወደ ሕዋ ለመውሰድ ከናሳ ጋር የቢሊዮን ዶላሮች ስምምነት ገብተዋል። ቦይንግ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ሲሰጠው የኢላን መስክ ንብረት የሆነው ስፔስኤክስ ደግሞ 2.6 ቢሊዮን ዶላር አግኝቷል።

ስፔስኤክስ እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ጠፈርተኞች ወደ ሕዋ ያጓጓዘ ሲሆን ሌሎችም የመንገደኞች ጉዞ አድርጓል። ቦይንግ በመጀመሪያ ሙከራው ነው ችግር ያጋጠመው።

የናሳ እና ቦይንግ ኢንጂነሮች ለወራት የገጠመው ችግር ምን እንደሆነ ለማጣራት ምርመራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የሳይንቲስቶቹ ዕቅድ የነበረው ችግሩን በመፍታት ጠፈርተኞቹን በስታርላይነር ወደ ምድር መመለስ ነበር።

ቅዳሜ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን፤ ቦይንግ ከናሳ ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሆነ ተናግረው ማሻሻያ ለማድረግ መታቀዱንም አስረድተዋል።

“ወደ ሕዋ የሚደረግ ጉዞ አደገኛ ነው። ደኅንነቱ የተጠበቀ ሆኖ በሚታወቅ መንገድ የሚደረግ የሙከራ ጉዞ ቢሆን እንኳ አደገኛ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

“የኛ ዋናው ዓላማችን ደኅንነት ነው። እሱ ነው መመሪያችን።”

ሁለቱ ጠፈርተኞች በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት 2025 ወርሀ የካቲት ክሩው ድራገን በተሰኘው የስፔስኤክስ መንኩራኩር ወደ ምድር ይመለሳሉ።

የስፔስኤክስ መንኩራኩር ጠፈርተኞቹን ይዞ ለመመለስ በሚመጣው መስከረም መጨረሻ ወደ ሕዋ ይበራል ተብሎ ይጠበቃል።

መጀመሪያው የታሰበው አራት ጠፈርተኞችን ይዞ ለመሄድ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሱኒታ እና ባሪን ይዞ ለመመለስ በሚል ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው ወደ ሕዋ የሚጓዙት ተብሏል።

ናሳ እንዳለው ሁለቱ ጠፈርተኞች ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ወደ ሕዋ ተጉዘው ለረዥም ወራት ቆይተው የተመለሱ ሲሆን ከታቀደው በላይ ሕዋ ላይ መቆየት ሊያጋጥም እንደሚችል ያውቁታል።

የ61 ዓመቱ ባሪ እና የ58 ዓመቷ ሱኒታ ወደ ምድር ለመመለስ የታሰበውን ዕቅድ “ሙሉ በሙሉ” የደገፉት ሲሆን እስከዚያው ድረስ ያለውን ጊዜያቸውን በዓለም አቀፉ የምርመር ጣቢያ ሳይንሳዊ ምርመር እያደረጉ ይቆያሉ።

ቦይንግ ስታርላይነር ከዚህ ቀድሞ በረራ ማድረግ ቢያስብም ባጋጠሙት ችግሮች ምክንያት ለዓመታት ያሰበውን ማድረግ ሳይችል ቀርቷል። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ሰው አልባ የሙከራ በረራዎችም ችግር ገጥሟቸዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ቦይንግ ትኩረቱ አሁንም “በተሳፋሪዎች እና በመንኩራኩር ደኅንነት ላይ መሆኑን” ገልጿል።

ምንም እንኳ ለስምንት ቀናት ብለው ተጉዘው ለወራት ሕዋ ላይ የከረሙት ሁለቱ ጠፈርተኞች መምጫቸው እስካሁን ባይታወቅም እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በ1990ዎቹ አጋማሽ ሩሲያዊው ቫለሪ ፖሊያኮቭ ለአጭር ጊዜ ወደ ሕዋ አቅንቶ ለ437 ቀናት ከርሞ መምጣቱ የሚታወስ ነው።

ባፈለው ዓመት ደግሞ ፍራንክ ሩቢዮ ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ ተጉዞ 371 ቀናት ቆይቶ መምጣቱ ይታወሳል።

አሁንም ሕዋ ላይ በሚገኘው ጣቢያ ላይ የሚኖረው ሩሲያዊው ኦሌግ ኮኖኔንኮ ከ1000 በላይ ቀናት በማስቆጠር የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።