ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑ የታወጀው ኤምፖክስ ክትባት አለው?
የዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑ የታወጀው የኤምፖክስ (ዝንጀሮ ፈንጣጣ) አዲሱ ዓይነት ዝርያ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።
ከዚህ በፊት ካጋጠሙት ሁሉ የበለጠ አደገኛ መሆኑ የተነገረለት ይህ ዝርያ ወደ መካከለኛው እና ምሥራቅ አፍሪካ እየተዛመተ ይገኛል።
በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን የበሽታውን ወረርሸኝ ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ነው ሲል አውጇል።
አዲስ እና የከፋ መሆኑ የተነገረለት አዲሱ የበሽታው ዝርያ ክላድ 1 ቢ በመባል ይታወቃል።
ወረርሽኙን ለመግታት ለተጠቁ እና ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ክትባቶች መድረሱን ማረጋገጥ ቁልፍ ሥራ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አጽንኦት ሰጥቷል።
ስለ ኤምፖክስ ክትባት ምን እናውቃለን? መውሰድ ያለበትስ ማን ነው?
ለኤምፖክስ ክትባት አለው?
ለኤምፖክስ የዓለም የጤና ድርጅት የሚመክራቸው ሁለት ክትባቶች ቢኖሩም በበርካታ አገራት እስካሁን ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፍቃድ አላገኙም።
ተቋሙ ኤምቪኤ ቢኤን ወይም ኤልሲ16 የተሰኙ ክትባቶችን እነዚህ በማይገኙበት ወቅት ደግሞ ኤሲኤኤም2000 የሚሰኘውን ክትባት መከተብን ይመክራል።
ፈቃድ ላላገኙ በማደግ ላይ ያሉ ወይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ክትባቶቹ በአፋጣኝ እንዲደርሱ ለማገዝ የዓለም የጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አጠቃቀም ሂደት ተግባራዊ እንዲሆን መመሪያ አስተላልፏል።
ይህም ማለት የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ጋቪ የተሰኘው የክትባት አቅርቦት ዓለም አቀፍ ተቋም ክትባቶችን ሰብስበው በእነዚህ አገራት ማሠራጨት ይችላሉ።
የዓለም የጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት የጅምላ ክትባቶች እንዲከናወኑ አይመክርም። ተቋሙ በዋነኝነት የክትባቶች ትኩረት መሆን ያለበት ለበሽታው የተጋለጡ ወይም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ላላቸው እንዲሁም ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ መሆን አለበት ይላል።
ግለሰቦች በሚኖራቸው የጉዞ ዕቅድ ምክንያት አደጋ ላይ ይወድቃሉ ተብሎ የጤና ባለሙያዎች የሚመክሯቸው ከሆነ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ክትባት መከተብን ሊያጤኑት ይገባል።
ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ኢሲዲዲ) በወረረርሽኙ ወደተጠቁ የአፍሪካ አገራት ለመሄድ የሚያስቡ መንገደኞች ክትባቱን እንዲወስዱ ምክረ ሃሳብ አስተላልፏል።
ከዚህ ቀደም የኤምፖክስ ክትባት የወሰዱ ደግሞ አሁን የሚሰጡትን ሁለት ክትባቶች ሳይሆን፣ አንድ ብቻ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።
ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ከሁለት እስከ አስር ዓመታት ባሉት ጊዜያት የማጠናከሪያ ክትባቶችን እንዲከተቡም ይመከራሉ።
የቀድሞው የፈንጣጣ ክትባት ኤምፖክስን ይከላከላል?
ኤምፖክስም ሆነ ፈንጣጣ መንስዔያቸው በተመሳሳይ ቤተሰብ ውስጥ በሚካተቱ የቫይረስ ዝርያዎች ናቸው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ የዕድሜ ባለጸጎች የወሰዱት የፈንጣጣ ክትባት የተወሰነ ጥበቃ ሊሰጥ ይችላል።
የፈንጣጣ በሽታ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት በዓለም የጤና ድርጅት መጥፋቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ክትባቱም በዚህ ወቅት ተቋርጧል።
በቂ የኤምፖክስ ክትባቶች አሉ?
የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) በአህጉሪቱ ያለውን የበሽታውን ወረርሽኝ መዛመት ለመግታት ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ክትባቶችን በመጪው አውሮፓውያን ዓመት ለማግኘት መታቀዱን አስታውቋል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ናይጄሪያ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ክትባቱን መስጠት ይጀምራሉ ተብሏል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ክትባቱን ከአሜሪካ እና ከጃፓን፣ ናይጄሪያ ደግሞ ከአሜሪካ ያገኘችው ክትባቶች ጥቅም ላይ ያውላሉ።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሮጀር ካምባ በበሽታው የሚያዙ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ቁጥር ከፍ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሕጻናት ቅድሚያ ክትባቱ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ባቫሪያን ኖርዲች ከተባለ የዴንማርክ አምራች ኩባንያ ጋር ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ በአህጉሪቱ ክትባቶችን ለማምረት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የመድኃኒት አምራቾች በይፋ እውቅና ያልተሰጣቸው የኤምፖክስ ክትባቶቻቸውን ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲያውሉት ጥሪውን አቅርቧል።
ናይጄሪያ የመጀመሪያ ዙር 10 ሺህ ክትባቶችን በመጪው ሳምንት ከአሜሪካ መንግሥት እንደምትቀበል ገልጻለች።
ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በበኩሏ አሜሪካ 50 ሺህ ክትባቶች እንዲሁም ጃፓን 3.5 ሚሊዮን ክትባቶችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል ብላለች።
የኤምፖክስ ክትባት ምን ያህል ውጤታማ ነው?
የዓለም የጤና ድርጅት የኤምፖክስ ክትባቶች “በህመሙ ከመያዝ እንዲሁም ለከፋ በሽታ ከመዳረግ የተወሰነ የመከላከል ጥበቃን ያደርጋሉ” ብሏል።
ኤምፖክስ “አዲሱ ኮቪድ” እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዳይሬክተር ዶክተር ካንስ ክሉጅ ገልጸዋል።
አዲሱ የበሽታው ዝርያ ከበድ ያለ ቢሆንም “አድሏዊ ያልሆኑ የሕዝብ ጤና እርምጃዎችን በመከተል እንዲሁም ፍትሃዊ የክትባት ተደራሽነትን በማረጋገጥ መቆጣጠር” ይቻላል ብለዋል።
ክትባቱን የወሰዱ ሰዎችም ቢሆኑ በበሽታው ከመያዝ ወይም እንዳይዛመት ለማድረግ ጥንቃቄ እንዳይለያቸው የዓለም ጤና ድርጅት መክሯል።
ለዚህም ከክትባቱ በኋላ የበሽታ መከላከልን ለማዳበር በርካታ ሳምንታት ይወስዳል። በተጨማሪም በዓለማችን ባሉ ጥቂት ሰዎችም ክትባቱ ላይሠራ እንደሚችል ተጠቁሟል።
ክትባት ከተወሰደ በኋላም በኤምፖክስ በተያዙ ህመሙ እንዳይከፋ ይከላከላል ተብሏል።
ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፈው ይህ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዲሁም ከሰው ወደ ሰው በንክኪ፣ በወሲብ ግንኙነት፣ በቅርበት በመጠጋት እና በትንፋሽ እንደሚተላለፍም ተጠቁሟል።
በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ህሙማን የሚያሳዩዋቸው ዋና ዋና ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ናቸው።
እስካሁን ድረስ ሁለት ዓይነት የቫይረሱ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2022 ተከስቶ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ እና በአሜሪካ የተከሰተው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ይጠቀሳል።
ብዙም አስፈሪ ያልሆነው ይህ ዝርያ በዋነኝነት በወሲብ ግንኙነት አማካይነት ይተላለፋል። ሁለተኛው በቅርቡ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተገኘው ዝርያ ሲሆን ገዳይ ነው ተብሏል።