ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ እንደሌለ ተገለጸ
በመላው አፍሪካ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መሆኑ የታወጀው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) በሽታ በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አለመከሰቱን የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ባለው በዚህ በሽታ 517 ሰዎች መሞታቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች መያዛቸውን የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) አስታውቋል።
በሽታው ከጥር ወር ጀምሮ 450 ሰዎች የሞቱባት ኮንጎን ጨምሮ በጎረቤት አገር ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክን ጨምሮ በአስራ ሶስት አገራት ተከስቷል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከሞቱት በተጨማሪ በባለፉት ወራት ከ13 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ተይዘዋል።
አሁን እየታየ ያለው የዝንጀሮ ፈንጣጣ አዲስ ዓይነት የበሽታው ዝርያ እየተዛመተበት ያለው ፍጥነት እንዳስደነገጣቸው የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕክል ሳይንቲስቶች አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ሲዲሲ ኃላፊ ዣን ካሴያ በሽታውን ለመቆጣጠር አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በድንበር ባሉ እንደ ሞያሌ እና ሌሎች የመግቢያ ቦታ ላይ የቁጥጥር እና ማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሆነም የጤና ሚኒስቴር አክሎ ገልጿል።
በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ህሙማን የሚያሳዩዋቸው ዋና ዋና ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ናቸው።
እነዚህ ምልክቶች የታዩበት እንዲሁም በቅርቡ በሽታው ወደተከተሰተባቸው አገራት የተጓዙ ግለሰቦች በአቅራቢያው ወደሚገኙ የጤና ተቋም እንዲሄዱም የጤና ሚኒስቴር ምክሩን ለግሷል።
በአሁኑ ወቅት በሽታው በአህጉሪቷ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መሆኑ መታወጁ መንግሥታት ምላሻቸውን አቀናጅተው በተጎዱ አካባቢዎች የህክምና አቅርቦቶችን እንዲሁም እርዳታዎችን ለማዳረስ እንደሚያግዝም ተገልጿል።
ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፈው ይህ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዲሁም ከሰው ወደ ሰው በንክኪ፣ በወሲን ግንኙነት፣ በቅርበት በመጠጋት እና በትንፋሽ እንደሚተላለፍም ተጠቁሟል።
እስካሁን ድረስ ሁለት አይነት የቫይረሱ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2022 ተከስቶ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ እና በአሜሪካ የተከሰተው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ይጠቀሳል።
ብዙም አስፈሪ ያልሆነው ይህ ዝርያ በዋነኝነት በወሲብ ግንኙነት አማካይነት ይተላለፋል። ሁለተኛው በቅርቡ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተገኘው ዝርያ ሲሆን ገዳይም ነው ተብሏል።
እስካሁን ድረስ ለበሽታው ሶስት ክትባቶች ያሉ ሲሆን ነገር ግን ለአደጋ የተጋለጡ ወይም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ላላቸው ነው የሚሰጠው።
በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ ያለውን የበሽታ ስርጭት ለመግታት ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ክትባቶችን ለማግኘት መታቀዱን የሲዲሲ አፍሪካ ዳይሬክተር ተናግረዋል።