የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀረበለትን የማስተካከያ ጥያቄ መቀበሉን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀርጌሳ ከተማ የሚያደርገውን በረራ ላይ የሚጠቀመውን የቦታ አገላለጽ እንዲያስተካክል የሶማሊያ መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ “ተቀባይነት አግኝቶ ማስተካከያ መደረጉን” የአገሪቱ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቬዬሽን ሚኒስቴር ለቢቢሲ ገለጸ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ ገጽ ላይ እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስ “ሀርጌሳ” ብቻ በሚል ተጠቅሶ የነበረው ወደ ከተማዋ የሚደረግ በረራ ከሰዓት በኋላ “ሀርጌሳ፣ ሶማሊያ” በሚል ተቀይሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ማስተካከያ ያደረገው የሶማሊያ መንግሥት ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም. ለአየር መንገዱ በላከው ደብዳቤ “የሉዐላዊነት ጥሰት” ነው በሚል ማስተካከያ እንዲደረግ መጠየቁን ተከትሎ ነው።

የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በጻፈው ደብዳቤ “የሉዐላዊነት ጥሰቱ” ደብዳቤ፤ አየር መንገዱ አገልግሎት ለሚሰጥባቸው መዳረሻዎች ከሚጠቀመው አገላለጽ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ጠቅሷል።

የሶማሊያ መንግሥት ቅሬታ ያቀረበበት መዳረሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ወደሆነችው ሀርጌሳ ከተማ ከሚደረግ በረራ አገላለጽ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሶማሊያ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቬዬሽን ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞሃመድ አብዲ ኡስማን ለቢቢሲ ሶማሊ ተናግረዋል።

ሶማሊላንድ እ.አ.አ ከ1991 አንስቶ ነጻነቷን ብታውጅም ሶማሊያ የምትቆጥራት የራሷ ግዛት አካል አድርጋ ነው።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በድረ ገጹ ላይ ወደ ከተማዋ የሚያደርገውን በረራ የሚጠቅሰው “ሀርጌሳ፤ ሶማሊላንድ” የነበረ ሲሆን፣ ይህ አገላለጽ በቅርቡ “ሀርጌሳ” ብቻ ወደሚል ተቀይሮ ነበር።

የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በጻፈው ደብዳቤ አየር መንገዱ ያደረገውን ማስተካከያ እንደማይቀበለው አስታውቆ ነበር። አየር መንገዱ ጥያቄ የቀረበበትን “የሉዐላዊነት ጉዳይ በመፍታት ፋንታ፤ የሶማሊያ መዳረሻው ላይ የነበረውን አገላለጽ አስወግዶ የአየር መንገድ ኮድን ብቻ አስቀርቷል” ሲል ወቀሳውን ገልጿል።

“ይህ ድርጊት ዋነኛዎቹን ስጋቶች የሚያባብስ እና የሶማሊያን ሉዓላዊነት ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ነው” ሲልም ቅሬታውን አሰምቷል።

አየር መንገዱ ቅሬታ የተነሳበትን ይህንን ጉዳይ እስከ ዛሬ አርብ ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም. እንዲፈታ ያሳሰበው የአገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፤ ማስተካከያው የማይደረግ ከሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሶማሊያ የሚያደርጋቸውን “በረራዎች በሙሉ ለማገድ እንደሚገደድ” አስጠንቅቆ ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ትናንት ሐሙስ ለባለሥልጣኑ ደብዳቤ መጻፉን የሶማሊያ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቬዬሽን ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞሃመድ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አየር መንገዱ ምላሽ በሰጠበት ደብዳቤ ጉዳዩን እየተመለከተው መሆኑን ገልጾ፤ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የተቀመጠው ቀነ ገደብ ግን “በጣም አጭር” መሆኑን አስረድቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ “ባለፉት ዓመታት የተገነባውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማስቀጠል ሲባል ጉዳዩን ለመመልከት እና ምላሽ ለመስጠት የተወሰነ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠን በትህትና እንጠይቃለን” ሲል በደብዳቤው ጠይቋል። ቢቢሲ አማርኛ ስለዚህ ደብዳቤ ከአየር መንገዱ አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደብዳቤውን በተጻፈበት ዕለት ምላሹን የሰጠው የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን ግን የአየር መንገዱን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል። “[ጥያቄውን] በጥንቃቄ በመመልከት እና ያለውን የቴክኖሎጂ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ አስፈላጊውን እርማት ለማድረግ ከሁለት ቀን በላይ ሊወስድ አይገባም ብለን እናምናለን” ሲል ተጨማሪ ቀናት ያልፈቀደበትም ምክንያት አስረድቷል።

በተቀመጠው ቀነ ገደብ ማስተካከያው የማይደረግ ከሆነም “ጉዳዩ በአጥጋቢ ሁኔታ እስከሚፈታ ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሶማሊያ ውስጥ የሚኖረውን ሥራ ከማገድ ውጪ አማራጭ እንደማይኖር” በድጋሚ ገልጿል።

ከትናንቱ የእነዚህ ደብዳቤዎች ልውውጥ በኋላ በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች በስልክ ንግግር ማድረጋቸውን የአገሪቱ ትራንስፖርት እና ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ሞሃመድ ለቢቢሲ ሶማሊ ገልጸዋል።

ኃላፊዎቹ ባደረጉት ንግግር መግባባት ላይ መድረሳቸውን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ መንግሥት የተጠየቀውን ማስተካከያ ለማድረግ መስማማቱን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ቢቢሲ አማርኛ ይህንን የስልክ ልውውጥ አስመልክቶ ወደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎችም ምላሽ አላገኙም።

ይሁንና በአየር መንገዱ ድረ ገጽ ላይ እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስ “ሀርጌሳ” ብቻ በሚል ሲጠቀስ የነበረው በረራ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል። ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ይህ በረራ “ሀርጌሳ፤ ሶማሊያ” በሚል እንደተቀየረ ቢቢሲ ከአየር መንገዱ ድረ ገጽ ተመልከቷል።

ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያን ያስቆጣውን የባሕር በር የሚያስገኝ ስምምነት በታኅሣሥ ወር ከሶማሊላንድ ጋር ከተፈራረመች በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሶማሊያ መንግሥትን የሚያወዛግብ ጉዳይ ሲፈጠር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በጥር ወር ደግሞ ወደ ሀርጌሳ ከተማ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የሶማሊያ አየር ክልል ውስጥ ከመግባቱ በፊት “ፈቃድ የለውም” በሚል በሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንዲመለስ ተደርጎ ነበር።

በተጨማሪም የካቲት ላይ በሶማሊያ የአየር ክልል ውስጥ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከሌላ አቅጣጫ ሲመጣ ከነበረ የኳታር አውሮፕላን ጋር በተመሳሳይ ከፍታ ላይ መብረራቸው ውዝግብ ፈጥሮ ነበር።

የሶማሊላንድ አቪዬሽን ባለሥልጣን ባወጣው መግለጫ ሁለቱ አውሮፕላኖች ለግጭት ሊዳርግ በሚችል ሁኔታ በተመሳሳይ ከፍታ ላይ እየበረሩ የነበሩት በሞቃዲሾ የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በሰጡት “የተሳሳተ መረጃ” ነው ሲል ከስሶ ነበር።

ይሁንና የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን “በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም” ሲል አስተባብሏል።

ይህንን ከስተተት ተከትሎ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስያ አገራት ለሚያደርጋቸው በረራዎች የሶማሊያ የአየር ክልልን መጠቀም ማቆሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከኳታር አውሮፕላን ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ክስተት በሶማሊያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት “አስተማማኝ ሆኖ እንዳያገኘው” በማድረጉ እንደሆነ አቶ መስፍን ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ ከወጣ ከሰዓታት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ የቢቢሲን ዘገባ “ትክክል ያልሆነ እና የተዛባ” ነው በማለት ጉዳዩን አስተባብሏል።