ሂላሪ ክሊንተን በኤፒስቲን የወሲብ ወንጀል ሰነዶችን በመደበቅ የትራምፕ አስተዳደርን ወቀሱ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሂላሪ ክሊንተን የወሲብ ወንጀለኛውን ጄፍሪ ኤፒስቲንን ሰነድ በመደበቅ የዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር ወነጀሉ።

የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበርሊን ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ሰነዶችን ይፋ አድርጉ። [ሪፐብሊካኖች] እያዘገሙ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።

የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ሰነዶችን ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ለተጎጂዎች ዲሞክራቶች ከበቂ በላይ መሆኑን በማንሳት ይከራከራሉ።

የአሜሪካ ኮንግረስ ከኤፒስቲን የወንጀል ምርመራ ጋር የተያያዙ ሰነዶች ይፋ እንዲሆኑ የሚያስገድድ ሕግ ማፅደቁን ተከትሎ ከሳምንታት በፊት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጄፍሪ ኢፒስቲን ሰነዶችን ይፋ አድርጓል።

በአስገዳጅ ሕጉ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ሁሉንም የኤፒስቲን ሰነዶች ይፋ ማድረጉን ያሳወቀ ቢሆንም ሕግ አውጪዎች ግን በቂ አይደለም እያሉ ነው።

ሕግ አውጪዎች ዐቃቤ ሕግ ከኤፒስቲን እና ተባባሪዎቹ ክስ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የሚያሳዩ የውስጥ ማስታወሻዎች ይፋ እንዲሆኑ እየጠየቁ ናቸው።

ሂላሪ ክሊንተን እና ባለቤታቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን በኮንግረስ ፊት ቀርበው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1983 ከጄራልድ ፎርድ ወዲህ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኮንግረስ ቀርቦ ሲመሰክር ይህ የመጀመሪያው ይሆናል።

በኤፒስቲን ሰነዶች ውስጥ በርካታ ጊዜ ስማቸው የተጠራው ቢል ክሊንተን ከጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር ትውውቅ ያላቸው ሲሆን ግንኙነታቸው ግን ከ20 ዓመት ገደማ በፊት እንዳቋረጠ ተናግረዋል።

ጥንዶቹ ከኤፒስቲን ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ምን ወንጀል ሰርተዋል ተብሎ የቀረበባቸው ክስ የሌለ ሲሆን ስለ ወሲባዊ ጥቃቱ በጊዜው ምንም አናውቅም ነበር ብለዋል።

ጥንዶቹ ምስክርነታቸው በዝግ ከሚሆን ይልቅ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን ጠይቀዋል።

"[ለመመስከር] እንገኛለን። ግን ለሕዝብ ክፍት ቢሆን የተሻለ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቀድሞዋ ፕሬዝዳንታዊ እጩ "ምንም የምንደብቀው ነገር የለም። በተደጋጋሚ ሰነዶቹ ይፋ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበናል" ሲሉ ባለቤታቸውን እና እርሳቸውን ትራምፕ ትኩረት ለመጥለፍ ተጠቅመውብናል ብለዋል።

በኤፒስቲን ሰነድ በተደጋጋሚ ስማቸው የሚነሳው ትራምፕ ምንም አይነት ስህተት አለመስራታቸውን እና ግንኙነታቸው ከዓመታት በፊት መቋረጡን ተናግረዋል። በኤፒስቲን ተጎጂዎችም ተከሰው አያውቁም።

ስለ ሂላሪ አስተያየት የተጠየቁት ትራምፕ የምደብቀው ምንም ነገር የለም ብለዋል።

"ነፃ ወጥቻለሁ። ከጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር ምንም የሚያገናኘኝ ነገር የለም። የሚያገኙ መስሏቸው ፍለጋ ሄዱ፤ እና ተቃራኒውን ነው ያገኙት" ሲሉ በኤርፎርስ ዋን አውሮፕላናቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ክሊንተኖች እና ዲሞክራቶች ከሰነዱ ጋር በተያያዘ እየተሳቡ ነውም ብለዋል።