ዓለም አቀፉ የሙስና ጠቋሚ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመለከተ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በዓለም ላይ በሕዝባዊ አገልግሎቶች ዘርፍ ያለውን የሙስና ሁኔታ እየተከታተለ ዓመታዊ ሪፖርት የሚያወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በአውሮፓውያኑ 2025 የአገራትን የሙስና ደረጃን ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ የ182 የዓለም አገራትን የሙስና ደረጃ ያወጣ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር ስትነጻጸር በሙስና ሁኔታ የተሻለ ደረጃ ላይ መሆኗን አሳይቷል።

የዓለም አቀፉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ በሚያወጣው የሙስና ጠቋሚ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ከ182 አገራት 96ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2025 በተሰበሰበው መረጃ መሠረት ከ100 ነጥብ 38 የተሰጣት ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ ከዓለም አቀፍ አማካይ ነጥብ (42/100) ዝቅ ያለ ሆኗል።

ጎረቤት አገር ኬንያ በዚህ ሪፖርት ያስመዘገበችው ነጥብ 30/100 ሲሆን፣ ኤርትራ 13/100፤ ሱዳን 14/100 አስመዝግበዋል።

የመጨረሻውን ረድፍ የያዙት የኢትዮጵያ ተጎራባች አገራት የሆኑት ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን 9/100 በማስመዝገብ ከ182 አገራት የመጨረሻዎቹ ረድፍ ላይ ተቀምጠዋል።

ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት አማካይ ነጥብ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 32/100 ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሷል።

በአገራት ውስጥ ያለውን የሙስና ሁኔታ የሚከታተለው ተቋሙ 182 አገራትን ከፍተኛ ሙስና የሚታይባቸውን (0) ከሙስና የጸዱ የሚላቸውን ደግሞ (100) ነጥብ በመስጠት በአንድን አገር የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉ የሙስና ተግባራትን በባለሙያዎች እና በንግድ ባለቤቶች ዕይታ ይመዝናል።

መመዘኛው በቀጥታ በአንድ አገር ውስጥ የተከናወነውን የሙስና መጠን አያሳይም።

የአገራትን የሙስና ሁኔታን በሚያሳየው ደረጃ ላይ ከሚሰጠው 100 አጠቃላይ ነጥብ ከግማሽ በላይ የሚያስመዘግቡ አገራት በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉ የሚባሉ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2025 የዓለም አማካይ የሙስና መጠን ወደ 42 ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ዙሪያ በመንግሥት አስተዳደር ላይ ሰፊ ተግዳሮቶችን መኖራቸውን ያሳያል።

የካቲት 10/2026 በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ይፋ የሆነው የ2025 የሙስና መረጃ ጠቋሚ ከሰሃራ በታች የሚገኙ በርካታ የአፍሪካ አገራት ሙስናን በመከላከል ረገድ ያላቸው አፈጻጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል።

መረጃው እንደሚያሳየው ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ከባድ የአስተዳደር ፈተናዎች እየተጋፈጡ የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አገራት ከዓለም አቀፍ አማካይ በታች ውጤት አስመዝግበዋል።

ይህም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የአሰራር ግልጽነት አለመኖር እና ደካማ አፈጻጸም ነፀብራቅ ነው።

ይሁን እንጂ ከበርካታ ጎረቤት አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ የሙስና ደረጃ አንጻራዊ የተሻለ ሲሆን ከቀደመው ዓመት ደረጃዋ አንድ እርከን መሻሻል አሳይታለች።

በሪፖርቱ ከተካተቱት 49 የአፍሪካ አገራት ከአውሮፓዊያኑ 2012 ጀምሮ አብዛኞቹ ደረጃቸው እያሽቆለቆለ የሄደ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።

በተጠናቀቀው 2025 ከ49ኙ የአፍሪካ አገራት መካከል ከ50 በላይ ነጥብ ያገኙት አራት አገራት ብቻ ናቸው።

ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ዝቅተኛውን 9ኛ ደረጃ ሲያገኙ፣ ኤርትራ 13ኛ እንዲሁም ሱዳን 14ኛ ደረጃ ይዘዋል።

ተቋሙ በአፍሪካ የፀረ ሙስና ጥረቶች ደካማ መሆናቸውን፣ የሲቪክ ምኅዳር መጥበቡን እና የዜጎች ፍትሕ የማግኘት ዕድል የተዛባ መኾኑን በሪፖርቱ ገልጧል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ ሙስና ያለባቸው አገራት ዴንማርክ፣ ፊንላንድ እና ኒውዚላንድ ናቸው።

በዚህ መመዘኛ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ነጥብ ያስመዘገበችው በ2021 ሲሆን፣ ያመጣችው ነጥብም በወቅቱ 39 ከ100 ነበር።

በ2024 ሪፖርት መሠረት የአገሪቱ ነጥብ 37 ከ 100 ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህ ሪፖርት ዴንማርክ (89)፤ ፊንላንድ (88) እና ሲንጋፖር (84) ነጥብ በማስመዝገብ ሙስናን በመቆጣጠር ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፣ ኃያላን ከሚባሉት አገራት መካከል አሜሪካ (64)፣ ቻይና (43)፣ ሩሲያ (22) ነጥብ አግኝተዋል።

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚፈጸም ሙስናን በሚያሳየው በዚህ ዓለም አቀፍ ሪፖርት ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት የተሻለች ሆና የተገኘችው ሲሼልስ (68) ነች።

በመቀጠል ኬፕ ቬርዴ (62)፣ ቦትስዋና (58) እና ሩዋንዳ (58) በማስመዝገብ ይከተላሉ።