ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀሲስ በላይ መኮንን በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር ተቀጡ
በሐሰተኛ ሰነድ ከአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ገንዘብ ለማውጣት በመሞከር የሙስና ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ቀሲስ በላይ መኮንን በአምስት ዓመት እስራት እና በ10 ሺህ ብር ተቀጡ።
ከቀሲስ በላይ ጋር አንድ ላይ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው የአራት ዓመት እስራት እና የ3 ሺህ ብር ቅጣት እንደተፈረደባቸው ጠበቃቸው አቶ ዮናታን ዘውዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው ሐሙስ ጥር 22/2017 ዓ.ም. የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ መድብ ሦስተኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች ዐቃቤ ሕግ ክስ የቀረበባቸው የወንጀል ሕጉን እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ተላልፈዋል በሚል ነበር።
ግለሰቦቹ ላይ የተመሠረተው ክስ በአፍሪካ ኅብረት ስም የተዘጋጀ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ስድስት ሚሊዮን 50 ሺህ ዶላር ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ነው።
ለወራት በፍርድ ቤት ሲታይ በቆየው የክስ ሂደት ከሳምታት በፊት ተከሳሾቹን የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተላላፈ በኋላ ቅጣት ከችሎቱ ብይን በፊት የተከሳሾች ጠበቆች የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አቅርበው እንደነበር ጠበቃ ዮናታን ዘውዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በችሎቱ የቀሲስ በላይ ጠበቆች ተከሳሹ ከዚህ በፊት በወንጀል ተጠርጥረውም ተቀጥተውም አለማወቃቸውን፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እንዲሁም በተለያዩ ሥራዎች እና በማኅበራዊ ዘርፍ መሳታፋቸውን እንዲሁም የስኳር ህምምተኛ መሆናቸውን ለቅጣት ማቅለያነት አቅርበዋል።
በዚህም የቅጣት ማቅለያዎቹ በችሎቱ ተቀባይነት በማግኘቱ የቅጣት እርከኑ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ተበይኖባቸዋል።
ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸው ክስ እንዲሻሻል መቃወሚያ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ ግን ሳይቀበለው መቅረቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ግለሰቦቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ሦስት ምስክሮችን በችሎት አሰምቷል።
የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ማረጋገጡን ጠቅሶ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ በሚገባ መከላከል ባለማቻላቸው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ናቸው ሲል ከሁለት ሳምንት በፊት ወስኗል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ መሠረት 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ቀሪዎቹ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በአራት ዓመት እስራት እና የ3 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በችሎቱ የተላለፈው ቅጣት ተግባራዊነት በገደብ እንዲሆን ቢጠይቁም ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን እና በብይኑ ላይ በቀናት ውስጥ ይግባኝ እንሚጠይቁ ጠበቃ ዮናታል ዘውዴ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ችሎቱ የቅጣት ውሳኔውን ባስተላላፈበት ጊዜ ቀሲስ በላይ መኮንን ምንም ዓይነት አስተያየት አለመስጠታቸው ተገልጿል።
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ለመመሥረት በነበራቸው እንቅስቃሴ የሚታወቁት ቀሲስ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበሩ።