ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ብርሃኑ አዴሎ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ
የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ብርሃኑ አዴሎ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነርነ ሆነው በፖርላማው ተሾሙ።
በተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ የሠሩት አቶ ብርሃኑ የመጨረሻ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸው የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተርነት ነበር።
የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬው ጥር 22/2017 ዓ.ም. በሚያካሂደው ጉባኤ ኮሚሽነር የሚሰይምው ባለፈው ኣመት ሰኔ ወር የሥራ ጊዜያቸውን አጠናቀው የተሰናበቱትን ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ለመተካት ነው።
ዳንኤል (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ሆነው ለአምስት ዓመታት በዋና ኮሚሸነርነት አገለግለዋል።
አሁን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ለመሆን በዕጩነት የቀረቡት አቶ ብርሃኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንግሥታዊ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ከኃላፊነታቸው የተነሱት "በቀረበባቸው ቅሬታ" መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ከአስር ዓመታት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
አቶ ብርሃኑ "ከሠራተኞች እና ከተቋሙ ደንበኞች ቅሬታዎች ይቀርቡባቸው እንደነበር" ጋዜጣው በወቅቱ ዘግቧል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አቶ ብርሃኑን ከዚህ ኃላፊነት ማንሳታቸውም የሪፖርተር ዘገባ ያሳያል።
አቶ ብርሃኑ የአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬከተር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ከ1996 እስከ 2002 ዓ.ም. ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል።
በሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ መሠረት አቶ ብርሃኑ ከዚህ ኃላፊነታቸው የተነሱትም በቀረበባቸው ቅሬታ ምክንያት ነው።
"ከተወለዱበት ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት በአቶ ብርሃኑ ላይ የተፈራረሙትን የቅሬታ አቤቱ" በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ማቅረባቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያስታውሳል።
ይህን ተከትሎ "በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተቋቋመ አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበባቸው ሪፖርት ከካቢኔ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው እና ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲነሱ" መደረጉን ሪፖርተር ከአስር ዓመታት በፊት በሠራው ዘገባ ጠቅሷል።
አቶ ብርሃኑ በመንግሥታዊ ተቋማት ከነበራቸው ኃላፊነት በተጨማሪ አወዛጋውን የ1997 ምርጫ ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ።
ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ብርሃኑ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ከሕንድ አገር የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
አቶ ብርሃኑ የማስትር ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸውን የሰሩት "Implementation of International Human Rights: The Role of Human rights Commissions" በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላይ ነው።
አቶ ብርሃኑ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል። በዞን ፋይናንስ መምሪያ የህግ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል። በተጨማሪም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ባገኙበት የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋካልቲ ለሶስት ዓመታት አስተምረዋል።
የአቶ ብርሃኑ የመጀመሪያ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት በቀድሞው ደቡብ ክልል የፍትህ ቢሮ ኃላፊነት ነው። ከዛ በመቀጠልም በቀረበባቸው ቅሬታዎች ከስልጣን ወደተነሱባቸው የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አቅንተዋል።
ከመንግስታዊ የሥራ ኃላፊ ከተነሱ በኋላ ላለፉት አስር ዓመታት በጥብቅና እና በህግ ማማከር ስራ ላይ መሰማራታቸውን ለፓርላማ አባላት የቀረበው የስራ ልምድ ያሳያል።
በኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት አቶ ብርሃኑ እንደ ዋና ኮሚሽነርነት "በማንኛውም ሥፍራ የተፈፀመ የሰብአዊ መብት መጣስ ጉዳይን" ራሳቸው የመመርመር ኃላፊነት አለባቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት መጣስ ጉዳዮችን አጥንቶ ከመፍትሔ ሃሳብ ጋር ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ። "የፌዴራል መንግሥት የሰብአዊ መብቶችን ጥበቃ አስመልክቶ በሚያዘጋጀው ሪፖርት ላይ አስተያየት መስጠት" ሌላኛው ኃላፊነታቸው ነው።
"ሰብአዊ መብቶችን የሚመለከቱ ረቂቅ ሕጎችን አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ማቅረብ፥ በሌሎች አካላት በተዘጋጁትም ላይ አስተያየት መስጠት" እና "የሰብአዊመብትጉዳዮችንናየኮሚሽኑንየሥራአካሔድ አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማቅርብ" በአዋጁ ለዋና ኮሚሽነሩ የተሰጡ ተግባራት ናቸው።