ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለግብፅ ጥቅም ለመሥራት ጉቦ የተቀበሉት ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
የቀድሞው የኒው ጀርዚ ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ በተከፈተባቸው የሙስና ወንጀል የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።
ባለፈው ሐምሌ ሜኔንዴዝ የውጭ መንግስታትን ለመርዳት ጥፍጥፍ ወርቅ፣ ጥሬ ገንዘብ እና መርሴዲስ ቤንዝ የተባለ ውድ መኪና በስጦታ መልክ መቀበልን ጨምሮ በ16 ክሶች ጥፋተኛ ተብለው ነበር።
አቃብያነ ህግ የቀድሞው ሴናተር የፈጸሙትን "ከባድ ጥፋት" በፍርድ ቤት በመጥቀስ ቢያንስ የ15 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ጠይቀው ነበር።
የሜኔንዴዝ ጠበቆች በበኩላቸው ከማኅበረሰብ አገልግሎት ጋር የተጣመረ አጠር ያለ ቅጣት እንዲጣልባቸው ጠይቀው ነበር።
ጉዳዩን የተከታተሉት ዳኛው ሲድኒ ስታይን ውሳኔውን ከማስተላለፋቸው በፊት "ይህንን በማለቴ ይቅርታ ይደረግልኝና ከሆነ ጊዜ በኋላ ሙሰኛ ፖለቲከኛ ሆነው ነበር" ማለታቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ሜኔንዴዝ ቅጣቱን ከመቀበላቸው በፊት ለፍርድ ቤቱ ንግግር ሲያደርጉ ማልቀሳቸው ታውቋል።
የፍርድ ቤት ጋዜጠኞች እንደገለፁት "ከቤተሰብ ሌላ የእኔ የምላቸውን ሁሉ አጥቻለሁ። እያንዳንዱ ቀን ለእኔ ቅጣት ነው" ብለዋል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ የኮንግረስ አባል ሆኑት የሜኔንዴዝ ልጅ ሮብ ሜኔንዴዝ እና የኤምኤስኤንቢሲ ጋዜጠኛዋ ሴት ልጃቸው አሊሺያ ሜኔንዴዝ ከአባታቸው ጀርባ ፍርድ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ታይተዋል።
ረቡዕ ሁለት የሜኔንዴዝ ተባባሪዎች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
በኒው ጀርዚ የሪል እስቴት አልሚ የሆነው እና ለሴናተሩ ወርቅ እና ጥሬ ገንዘብ እንደሰጠ የተነገረለት ፍሬድ ዳይቤስ የሰባት ዓመት እስራት እና 1.75 ሚሊየን ዶላር ተቀጥቷል።
በሜኔንዴዝ እና በግብጽ መንግስት መካከል ድልድይ ሆኖ አገልግሏል የተባለው ዋኤል ሃና የተባለ ግብጻዊ-አሜሪካዊ ነጋዴ ደግሞ ከስምንት ዓመት በላይ እስራት እና 1.25 ሚሊየን ዶላር ተወስኖበታል።
ሜኔንዴዝ በተደጋጋሚ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ ከመካዳቸውም በላይ ውሳኔውን ይግባኝ ለማለት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ይመሩ የነበሩት የኒው ጀርዚ ሴናተር በነሐሴ ወር ከምክር ቤቱ ለቀዋል።
ውሳኔው የተሰጠው ከዘጠኝ ሳምንታት የፍርድ ሂደት በኋላ ነው። በዚህ ወቅት ዳኞች ሜኔንዴዝ ከ100 ሸዒህ ዶላር በላይ የሚያወጡ የወርቅ ጥፍጥፎች እና ከ480 ሺህ ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብ ስጦታዎች መቀበላቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ተመልክተዋል። ወርቆቹ እና ገንዘቡ በኤፍቢአይ ወኪሎች በሜኔንዴዝ ቤት የተገኙ ናቸው።
ጉቦውን በማግኘታቸውም ሜኔንዴዝ ግብጽ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከአሜሪካ በእርዳታ መልክ እንድታገኝ ረድተዋል ተብሏል።
ስጦታዎቹ እንደ ጉቦ ለመታየት ብቁ አይደሉም ሲሉ የሜኔንዴዝ ጠበቆች ተከራክረዋል። ሜኔንዴዝ በጉቦው ምክንያት ስለወሰዱት እርምጃ አቃብያነ ህጎች ማረጋገጫ አልሰጡም ብለዋል።
የቀድሞው ሴናተር ከሁለቱ ተባባሪ ተከሳሾቻቸው (ሃና እና ዳይቤስ) ጋር በተያያዘ በሚደረገው የወንጀል ምርመራ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር በመሞከርም ጥፋተኛ ተብለዋል።
በጉዳዩ ላይ የተሳተፈው ሦስተኛው ነጋዴ ጆሴ ዩሪቤ ጥፋተኛ መሆኑን ያመነ ሲሆን በያዝነው ዓመት መጨረሻ ላይ የቅጣት ውሳኔ እንደሚተላለፍበት ይጠበቃል። በፍርድ ሂደቱ ወቅትም በሜኔንዴዝ ላይ መስክሯል።
የቀድሞው ሴናተር ባለቤት ናዲን ሜንዴዝ በሦስቱ ሰዎች እና በግብጽ ባለስልጣናት መካከል መልዕክቶችን እና ጉቦ በማመላለስ ተሳታፊ ናቸው በሚል ተወንጅለዋል።
የጡት ካንሰር ህክምና እንዲያገኙ በሚል የፍርድ ሂደታቸው ዘግይቶ በመጋቢት ወር ይጀምራል። በቀረበባቸው ክስ ዙሪያ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት አስተባብለዋል።