የትራምፕ ተቋም በግብር ማጭበርበር ጥፋተኛ ተባለ

የቀድሞው የዶናልድ ትራምፕ ቤተሰብ ሪል ስቴት በግብር ማጭበርበር ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ።

‘ዘ ትራምፕ ኦርጋናይዜሽን’ የተባለው ተቋም ኒው ዮርክ ውስጥ በተካሄደ የፍርድ ሂደት ነው ጥፋተኛ የተባለው።

በፍርድ ሂደቱ ላይ ትራምፕም ይሁን ቤተሰቦቻቸው አልተገኙም።

ትራምፕ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “ያስቆጣል” ካሉ በኋላ ይግባኝ እንደሚሉ አስታውቀዋል።

በተቋሙ መዝገብ ያልተያዙ ጥቅማ ጥቅሞችን ለከፍተኛ አመራሮቹ በመስጠት ለዓመታት ንብረት እንደተበዘበዘ ተገልጿል።

ግብር ካልተከፈለባቸው ጥቅማ ጥቅሞች መካከል ቅንጡ መኪናዎች እና የግል ትምህርት ቤት ክፍያዎች ይገኙበታል።

ለሠራተኞቹ የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛ እንደሆነ በማስመሰል ግብር እንደተጭበረበረም ተገልጿል።

ተቋሙ እስከ 1.6 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ቅጣት እንደሚከፍል እና በቀጣይም ብድር ለማግኘት እንደሚቸገር ተገልጿል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት የፍርድ ሂደቱ ፖለቲካዊ አጀንዳ አለው ማለታቸው ይታወሳል።

የተቋሙ የፋይናንስ ዋና ኃላፊ አል ዌስልበርግ ባለፈው ነሐሴ ጥፋተኛነታቸውን አምነው የተቋሙን ስህተት በፍርድ ቤት ከተናገሩ በኋላ ትራምፕ አልን ወርፈዋቸዋል።

ዋና ኃላፊው “በግላቸው በፈጸሙት የግብር ማጭበርበር” ምክንያት ተቋሙ መቀጣት የለበትም ሲሉም ተከራክረዋል።

“ተቋማችን የተከበረ የሂሳብ ሰራተኛና ሕግ ተቋማትን ቀጥሮ እያሠራ ነበር። ለክስ የሚያበቃ ነገር የለም። በአገራችን ታሪክ አሳፋሪው ፖለቲካዊ ክስ ነው” ይላል በትራምፕ ቢሮ የወጣው መግለጫ።

የትራምፕ ተቋም በተለያዩ አገራት ሆቴሎች፣ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎችና ሌሎችም ንብረቶች ባለቤት ነው።

ተቋሙ ከግብር ማጭበርበር ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳለው የሚታማ ሲሆን፣ አመራሮቹ የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም አሳንሶ በማስመዝገብ መክፈል ከሚገባቸው ያነሰ ግብር እንደሚከፍሉ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ይህ የሚደረገው “ከፍተኛ አመራሮችን ለማስደሰትና ታማኝነታቸውን ለማስጠበቅ” እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ገልጿል።

የዚህ ተቋም አጋር ቅርንጫፍ የሆኑት ‘ትራምፕ ኮርፕ’ እና ‘ትራምፕ ፔይሮል ኮርፕ’ ከግብር ማጭበርበር እና ሐሰተኛ የንግድ ሰነድ ከማቅረብ ጋር በተያያዘ 17 ክሶች ቀርቦባቸዋል።

የማንሀተን ዐቃቤ ሕግ “ለ13 ዓመታት ትራምፕ ኮርፖሬሽን እና ትራምፕ ፔይሮል ሲያጭበረብሩ ቆይተዋል። አመራሮቻቸውን ሲጠቅሙ ግብር ሰብሳቢውን ጎድተዋል” ሲሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አሞግሰዋል።

 ስለ ተቋሙ ምስክርነት የሰጠው ዋና ኃላፊ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ስለተባበረ ከተወሰኑ ወራት በላይ አይታሰርም።

በሌላ በኩል ትራምፕ እና ሦስቱ ልጆቻቸው ሌላ የፍርድ ቤት ክስ ይጠብቃቸዋል።