በዘንድሮው በቢቢሲ ተፅእኖ ፈጣሪ መቶ ሴቶች ዝርዝር የተካተቱት ኢትዮጵያውያን እነማን ናቸው?

ቢቢሲ በየዓመቱ በዓለማችን ላይ ተደማጭነት ያላቸው፣ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑ እንዲሁም ድምፃቸውን ለሰብዓዊነት እያዋሉ ያሉ መቶ ሴቶችን ይመርጣል።

የዘንድሮውንም መቶ ሴቶች ዝርዝርን ይፋ አድርጓል።

በዘንድሮውም ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያውኖቹ የራይድ መሥራች ሳምራዊት ፍቅሩ እንዲሁም በትግራይ ጦርነት ለተጎዱ ሴቶች ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ የምትገኘው ወጋሕታ ገብረዮሐንስ ተካትተውበታል።

ከኢትዮጵያውያኖቹ በተጨማሪ ዩቲዩብን በመጠቀም ቀጣዪን ትውልድ በትምህርት ለመቅረጽ እየሞከረች ያለችው ኤርትራዊቷ ቅሳነት ቴዎድሮስ ተካታበታለች።

ሳምራዊት ፍቅሩ- ኢትዮጵያ-የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ

ምንም እንኳን እስከ 17 ዓመቷ ድረስ ኮምፒውተር ተጠቅማ ባታውቅም፣ የኮምፒውተር ፕሮግራመሯ ሳምራዊት ፍቅሩ፣ ከራይድ የታክሲ መተግበሪያ ጀርባ ካሉት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የሃይብሪድ ዲዛይን መስራች ነች።

ከሥራ በኋላ ታክሲ ለመያዝ ደኅንነት ስላልተሰማት እንዲሁም፣ ከሾፌሮች ጋር ይህንን ክፈይ በሚል የማያቋርጥ ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባትም ስትል ይህንን መተግበሪያ እንደፈጠረች ትናገራለች።

ሳምራዊት ሥራውን ስትጀምረውም የነበራት መነሻ ካፒታል ከሁለት ሺህ ዶላር ያነሰ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ኩባንያዋ በርካታ ሴት ሠራተኞችን ቀጥሯል። በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉት ሴቶች ጥቂት ሲሆኑ፣ ሳምራዊት የመጪውን ጊዜ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችንም ማነሳሳት ትፈልጋለች።

“ሴቶች በባለቤትነት የሚቆጣጠሯቸው ማዕከላት በቁጥር እያደገ ነው። በአሁኑ ወቅት ወጣት ሴቶች የፈጠራ ሀሳቦቻቸው እውን እንዲሆኑ ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ ሊመቻችላቸው ይገባል” ብላለች።

ወጋሕታ ገብረዮሐንስ - ትግራይ፣ ኢትዮጵያ - የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኛ

የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኛ የሆነችው ወጋሕታ ገብረዮሐንስ በትግራይ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቅረፍ አላማ ያለው “ህድሪና” የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሥራች ናት።

ህድሪና በጦርነት የተጎዱ ሴቶችን እና ህጻናትን ለመርዳት በርካታ ፕሮጀክቶችንም ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከሚጠቀሱትም መካከል በአገር ውስጥ ተፈናቅለው በየመጠለያዎቹ ላሉ የምገባ ፕሮግራም እና የከተማ አትክልት ማብቀል ይገኙበታል።

ድርጅቱ በጦርነቱ የተደፈሩ ሴቶችን ድጋፍ መስጠት እንዲሁም በትግራይ በተጣለው እገዳ የተነሳ ሕይወታቸውን ለማቆየት ወደ ወሲብ ንግድ የገቡ ሴቶችም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አሉት።

ቅሳነት ቴድሮስ - ኤርትራ - የትምህርት ሥራ ፈጣሪ

“በለስ ቡቡ” ኤርትራውያን ህፃናት ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን የሚያስተምር የዩቲዩብ ቻናል ነው። የዚህም መሥራች ኤርትራዊቷ ቅሳነት ቴድሮስ ናት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው ቅሳነት ከልጅነቷ ጀምሮ ቋንቋን ማወቅ የራስን ማንነት ለመረዳት መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ትናገራለች።

የፕሮዳክሽን ቡድን አባላቷ ከኤርትራ፣ ከኡጋንዳ፣ ከዲሞክራቲል ሪፐብሊክ ኮንጎ የተውጣጡ ዲጂታል አርቲስቶችን ያካተተ ሲሆን ይህም መድረክ ሥራቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

ቅሳነት በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የመጀመሪያውን የበለስ ቡቡ የህጻናት ፌስቲቫል አዘጋጅታ ነበር።

በዘንድሮ መቶ ሴቶች ዝርዝር ዓለምን እያናወጣት ባለው የዩክሬን ጦርነት ግንባር ላይ ህክምና እየሰጠች ያለች ባለሙያ እንዲሁም፣ የኢራንን መንግሥት እየፈተኑ ካሉ ተቃዋሚዎች መካከል አንዷ ተካትተውበታል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ ስማቸው የተነሱ የዩክሬኗ ቀዳማዊት እመቤት ኦሌና ዜሌንስኪ፣ እንዲሁም በትውልድ አገሯ ኢራን አስገዳጅ የሆነውን ሂጃብ አሽቀንጥራ በመጣል ተቃውሟዋን ፀጉሯን በማሳየት የገለጸችው የተራራ መውጣት ስፖርት ተወዳዳሪዋ ኤልናዝ ሬካብ አሉበት።

አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ቢሊ ኤሊሽ እና ሕንዳዊቷ ተዋናይ እና ፕሮዲዩሰር ፕሪያንካ ቾፕራ የሴቶችን ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና በሚሰጠው በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።

በዝርዝሩ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያተረፉ፣ ለማኅበረሰባቸው በጎ እየሰሩ ያሉ የመብት አቀንቃኞች፣ ተሟጋቾች ይገኙበታል።

ቢቢሲ ሀንድረድ ውሜን (የቢቢሲ መቶ ሴቶች) የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2012 ነው። ለዚህም መነሻ የሆነው በዴልሂ በደቦ ተደፍራ የተገደለችው ግለሰብ ስትሆን፣ የሴቶችን ታሪክ በመገናኛ ብዙኃን ለማሻሻል የሚደረገውም ጥረት አካል ነው።

ዘንድሮው 10ኛ ዓመቱን ያከበረው የቢቢሲ መቶ ሴቶች መሪ ቃል “ግስጋሴ” (ፕሮግረስ) በሚል እሳቤ ሲሆን፣ ባለፉት አስር ዓመታትም በሴቶች ሕይወት ላይ የመጡ ለውጦችን ይዳስሳል።

ለመጀመሪያ ጊዜም በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካትተው የነበሩ ሴቶች ዕጩ አባላትን እንዲመርጡ ተጠይቀዋል።

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ማላላ ዩሱፍዛይ ለምሳሌ የአየር ንብረት ተሟጋች፣ ጋዜጠኛ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችውን ብራዚላዊቷን አሊስ ፓታክሶን መርጣለች።