ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ዋንጫ አሸናፊን ቀድሞ ለመገመት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ መንገዶች
ኳታር እያስተናገደችው ያለውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን የትኛው አገር ይወስዳል? የበርካቶች ጥያቄ ነው።
አንዳንዶች ስፖርታዊ ትንታኔን ተከትለው ለመገመት ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ‘ጠቋሚ ምልክት’ ይፈልጋሉ።
ተስፋቸውን ‘አስማት’ ላይ የጣሉ፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ኤአይ) የሚታገዙም አሉ።
የኳስ ውጤት መገመት በእርግጥ ቀላል አይደለም። ምክንያታዊ ግምት ቢከተሉም በቁማር ገንዘብ የሚበሉ የበዙትም ለዚያ ይሆናል።
የፋይናንስ ተቋማት የወደፊቱን የሚገምት ሞዴል ቢያዘጋጁም፣ የኳስ ውጤት ባልተጠበቀ ሁኔታ መለዋወጡ ለኪሳራ ሲዳርጋቸው ታይቷል።
‘አስማታዊ ኃይል’ ተጠቅመው የወደፊቱን መተበይ እንደሚችሉ የሚያምኑ፣ የኳስ ውጤትን ለመገመት ሲሞክሩ ይስተዋላል።
ለምሳሌ ብራዚላዊው አቶስ ሳሎሜን እንውሰድ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚነሳና፣ ሩሲያ ዩክሬንን እንደምትወር ቀድሞ እንዳወቀ ይናገራል። ምናልባት የዓለም ዋንጫ አሸናፊውንም ይተነብያል።
ኳስ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች እና ጋዜጠኞች ተሰባስበው በመወያየት አሸናፊውን ይገምታሉ። ብዙውን ጊዜ ግምታቸው ስህተት ይሆናል።
የዓለም ዋንጫ እጅግ በጉጉት ከሚጠበቁ ሁነቶች አንዱ ነው።
የዘንድሮው የኳታር የዓለም ዋንጫ አምስት ቢሊዮን ተመልካቾች እንዳሉት ፊፋ አስታውቋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ፕሮፌሰር ሮበርት ሳይመንስ “ሰዎች በተለይም ገንዘብ የሚያገኙ ከሆነ በቁማር ይደሰታሉ” ይላል።
የዓለም ዋንጫ ለመገመት አዳጋች ቢሆንም፣ ተመልካቾች ከመቆመር ወደኋላ አላሉም።
ለምሳሌ ሳዑዲ አረቢያ አርጀንቲናን፣ ጃፓን ጀርመንን ያሸንፋሉ ብሎ ለመገመት ከባድ ነበር።
የዓለም ዋንጫ አሸናፊን ለመገመት ተመልካቾች የሚጠቀሙባቸውን አስደናቂ መንገዶች እንዲህ ቃኝተናል።
የኮምፒውተር ግምት
የኮምፒውተር ቀመር እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቀመር በመጠቀም የዓለም ዋንጫ አሸናፊን ለመገመት እየተሞከረ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደሙ (ዩኬ) አለን ተሪንግ ተቋም ምርምር ከሚያደርጉት መካከል ይገኝበታል።
ሳይንቲስቶች 64 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በመጠቀም 100,000 የኮምፒውተር ስሌቶች ሠርተዋል።
ለዚህ የተጠቀሙት የቀደሚ ውጤቶችን ነው።
አንደኛ ደረጃ ግምት የተሰጠው ለአምስት ጊዜ ባለ ድሏ ብራዚል ነው። በመቀጠልም ቤልጄየም እና ሁለት ጊዜ ያሸነፉት አርጀንቲ እና እና ፈረንሳይ ለዋንጫ ይጠበቃሉ ብሎ ነበር፤ ነገር ግን ቤልጂየም ከምድብ ውድድሩ ባሻገር ማለፍ አልቻለችም።
ተቋሙ በኮምፒውተር ስሌት የታገዘ ግምቱን ቢያስቀምጥም “የእኛን ግምት ተከትሎ ማንም ሰው እንዳይቆምር። ምክንያቱን ኳስ ለመገመት አዳጋች ነው” ሲል አስጠንቅቋል።
ከዚህ በፊት ጎልድማን ሳችስ፣ ዩቢኤስ፣ አይኤንጂ የተባሉ ተቋማት በሁለት የዓለም ዋንጫዎች ግምታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ለንደን የሚገኘው ሊብሪየም ካፒታል የ2014 እና የ2018 አሸናፊዎችን በትክክል መገመት ችሏል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ግምት መስጠት እንደማይቻል ያምናል።
ክሌመንት የተባለው ተቋም እንዳለው፣ አንድ ቡድን የማሸነፍ ዕድሉን 45 በመቶ መገመት ቢችልም የተቀረው 55 በመቶ የቡድኑ ዕድል ላይ የተመሠረተ ይሆናል።
‘ጠንቋይ’ እንስሳት
የዓለም ዋንጫ አሸናፊን መገመት እንደሚችሉ የሚነገርላቸው ‘አስማተኛ’ እንስሳት አሉ።
ፓንዳዎች፣ ግመሎች እና ኦክቶፐስ የተባለው የዓሣ ዝርያ ይጠቀሳሉ።
‘ፖል ዘ ኦክትፑስ’ የተባለው ዓሣ የ2010 የዓለም ዋንጫ አሸናፊን በትክክል ከገመተ ወዲህ ሌሎች የዓለም ዋንጫ አሸናፊዎችንም በትክክል ይገምታል ተብሎ ይታሰባል።
ዓሣው ሁለት የአገራት ሰንደቅ አላማ ያለው ሳጥን ይቀርብለታል። ሁለቱም ሳጥን ውስጥ ምግብ ይቀመጣል። ያሸንፋል የሚለው አገር ሰንደቅ አላማ ከተቀባው ሳጥን ይመገባል።
14 ጊዜ ሙከራ ተደርጎ 12ቱ የዓሣው ግምቶች ትክክል ሆነዋል።
ይህ ዓሣ አሁን ሕይወቱ አልፏል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፣ ዓሣው እግር ኳስ ማን እንደሚያሸንፍ የሚያውቅበት ‘አስማታዊ’ ኃይል የለውም። ዓሣ በተፈጥሮው ከአግድም መስመር ቀጥተኛ መስመር ያለበትን ምሥል ይመርጣል።
ከቀረቡለት የሰንደቅ አላማ ምርጫዎች ቀጥተኞቹን የመረጠውም ለዚያ ይሆናል።
ቁማር
ሳይንቲስቶች ቁማርን አያበረታቱም።
ፕሮፌሰር ሳይመንስ እንደሚሉት፣ ምክንያታዊ ግምት በማስቀመጥ ቁማርን የሚያሳልጡ ባለሙያዎች (ቡክሜከርስ) የተሻለ አማራጭ ናቸው።
እነዚህ ባለሙያዎች ግምታቸው ትክክል ካልሆነ ገንዘብ ስለሚከፍሉ፣ ትክክለኛ ግምት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።
በእርግጥ ግምት የተሰጣቸው ቡድኖች ሊያሸኝፉም ሊሸነፉም ይችላሉ። ነገር ግን ምክንያታዊ ግምት የማሸነፍ ዕድልን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።
የዓለም ዋንጫ በ1930 በኡራጓይ ከተጀመረ ወዲህ ብዙ ተለውጧል።
ባለፉት ዓመታት በውድድሩ ከቀረቡ 79 አገራት መካከል ያሸነፉት ስምንት ብቻ ናቸው።
ብራዚል (አምስት ጊዜ)፣ ጣልያን እና ጀርመን (አራት ጊዜ)፣ ፈረንሳይ፣ ኡራጓይ እና አርጀንቲና (ሁለት ጊዜ) እንዲሁም ስፔን (አንድ ጊዜ)።
ከ1978 ወዲህ ዋንጫውን ያልወሰዱና የጨዋታቸውን የመጨረሻ ዙር የተቀላቀሉ አገራት ሦስት ናቸው።
ከአህጉራቸው ውጭ ዋንጫውን የወሰዱ አገራት ብራዚል፣ ጀርመን እና ስፔን ናቸው።
እስከ መጨረሻው ዙር የተጓዘ አፍሪካዊ አገር የለም። ከእስያ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው ደቡብ ኮርያ ብቻ ናት።
ከ1982 ወዲህ ከጀርመን ወይም ከጣልያን አንድ ተጫዋች ያልተሳተፈበት የዓለም ዋንጫ የለም።
ለዚህ ነው በዓለም ዋንጫ የባየር ሙኒክ እና ኢንተር ሚላን ስም በተደጋጋሚ የሚነሳው።
በኳታር የዓለም ዋንጫ ባየር ሙኒክ 17 ተጫዋዎች አሰልፏል። ኢንተር ሚላን ደግሞ ስድስት ተጫዋቾች አሉት።
ታዲያ የኳታሩን የዓለም ዋንጫ ማን ይወስድ ይሆን?