አንድ ግለሰብ በጀርመን በይሖዋ ምስክሮች የማምለኪያ ስፍራ ተኩስ ከፍቶ በርካታ ሰዎች ተገደሉ

ሀምቡርግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ አንድ ግለሰብ በይሖዋ ምስክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተኩስ ከፍቶ በርካቶች ተገደሉ።

ፖሊስ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ብቻውን ተኩስ መክፈቱን እና በጥያቁ ከ6 እስከ 7 ሰዎች መደገላቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ፖሊስ ግለሰቡ ጥቃቱን እንዲፍት ምን እንዳነሳሳው እስካሁን ግልጽ አይደለም ብሏል።

ከሟቾች በተጨማሪ በርካቶች በጥቃቱ ቆስለዋል።

ፖሊስ ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም ያለውን ግለሰብ አስክሬን ማግኘቱን አስታውቋል።

የድረሱልኝ ጥሪ ለጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች በደረሰ በዲቃዎች ልዩነት ፖሊስ በስፋራው ሲደርስ በጥይት ተመትተው ክፉኛ የቆሰሉ እንዲሁም ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ማግኘቱን የፖሊስ ቃል አቀባይ ሆልገር ቬህሬን ተናግረዋል።

“እስካሁን የምናውቀው በርካታ ሰዎች በቦታው መገደላቸውን፣ በርካቶች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ግለሰቡ ጥቃቱን ለማድረስ ምን እንዳነሳሰው “እስካሁን ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም” ብለዋል።

የግዛቷ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ኤንዲ ግሮት የልዩ ፖሊስ ኃይል አባላትን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጸጥታ ኃይል አባላት በስፍራው መስማራታቸውን በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።

የጀርመን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ፖሊስ ተጎጂዎችን ወደ አምቡላንስ ውስጥ ሲያስገባ አሳይተዋል።

ፖሊስ ጥቃት ከደረሰበት ስፋራ ደርሶ ኦፕሬሽኑን በሚያከናውንበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ተነግሯቸው ነበር።

ዋና መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው የይሖዋ ምስክሮች በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካ የተመሰረተ ሲሆን የክርስትን እምነት መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ነው።