“በርዕደ መሬቱ ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊ የለም” በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር

በቱርክ በደረሰው አስከፊ ርዕደ መሬት ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊ መረጃ እንዳልደረሳቸው በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገለጹ።

በቱርክ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ፣ ከተማሪዎች እንዲሁም በቱርክ እና በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ቤተሰቦች በሰበሰቡት መረጃ የሞተ ወይም የተጎዳ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ አምባሳደር አደም መሐመድ ማህሙድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቱርክ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ተማሪዎች ከአደጋው አካባቢ በሰላም ወጥተው ወደ መጠለያ ጣቢያ የገቡ እንዳሉ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

መጠለያ ገብተው የደወሉ ተማሪዎች እንዳሉ የሚናገሩት አምባሳደሩ፣ አንዳንዶቹም ወደ አንካራ እየመጡ ነው ብለዋል። ከእነዚህ ተማሪዎች በተገኘ መረጃ አደጋ የደረሰበት እንደሌለ ገልጸው በመጠለያው ያሉ ተማሪዎች ከአስር አይበልጡም።

ኢትዮጵያውያኑ በተጠለሉበት ቦታ “ለማንኛውም የቱርክ ዜጋ እንደሚደረገው እርዳታን እያገኙ ነው” ብለዋል።

በተማሪዎች እና በማኅበረሰቡ አደረጃጀት በኩል ያለውን ሁኔታ በቅርበት ክትትል እያደረጉ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር አደም፣ አዳዲስ መረጃዎችም ካሉ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚያስታውቁ ገልጸዋል።

ቁጥራቸው ባይታወቅም በቱርክ ያሉ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ ተማሪዎች እና ተመላላሽ ነጋዴዎች ናቸው ያሉት አምባሳደር አደም፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እና ነዋሪዎች ርዕደ መሬቱ ከደረሰበት ራቅ ባለ ስፍራ እንዳሉም ተናግረዋል።

በቱርክና በሶሪያ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ሰኞ ዕለት በደረሱ አስከፊ ርዕደ መሬቶች ሳቢያ የሟቾች ቁጥር ከ22 ሺህ አልፏል።

በሺህ የሚቆጠሩ ከርዕደ መሬቱ አደጋ የተረፉ ዜጎች ለሳምንት ያህል ከባድ ቅዝቃዛ ባለበት ሁኔታ ጎዳና ላይ እያደሩ ነው።

አደጋው ከደረሰ አምስት ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን ከፍርስራሹ ውስጥ ከዚህ በኋላ በሕይወት የሚወጡ ሰዎች ይኖራሉ ወይ የሚለው ተስፋም እየከሰመ መጥቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት በከፍተኛ ቅዝቃዜ የተነሳ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው በርካታ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደሚኖረ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲቀጥል ተማጽኗል።

ሕይወታቸውን ካጡት ባሻገር በአደጋው ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገዋል ወይም ተጋልጠዋል ተብሏል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአስከፊ ውሽንፍር እና ዝናብ ጋር በመታገል በሺዎች ከሚቆጠሩ የሕንጻዎች ፍርስራሽ ስር በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለመታደግ እየሞከሩም ይገኛሉ።

የቱርክ እና የሶሪያን አዋሳኝ አካባቢዎች በመቱት በእነዚህ ርዕደ መሬቶች የበርካቶች ሕይወት ከመቀጠፉ በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎች ተደርምሰዋል።

ሆኖም በቱርክ በአንዳንድ አካባቢዎች የነፍስ አድን ሠራተኞች ምላሽ የዘገየ ነው በማለት ቤተሰቦቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን በመፈለግ ሕይወታቸውን ለማዳን ነዋሪዎች ያላቸውን መሳሪያዎች ይዘው ወጥተዋል።

በርዕደ መሬቶቹ ክፉኛ በተጎዱ 10 የቱርክ ግዛቶች ለሦስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።

በሶሪያ ያለው ሁኔታ ከቱርክ የከፉ ሲሆን፣ ከአስር ዓመታት በላይ በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው እርዳታ በበቂ ሁኔታ ለማድረስ ፈተና ሆኗል።

የአውሮፓ ኅብረት ሦስት ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ለሶሪያ የአደጋ ጊዜ ምላሽ የለገሰ ሲሆን፣ እርዳታው በአማጺያን በተያዙ አካባቢዎችም ሆነ በመንግሥት እጅ ላሉት እኩል እንዲደርስ አሳስቧል።

በሶሪያ እስካሁን ሦስት ሺህ ሰዎች በርዕደ መሬቱ እንደሞቱ ሲገመት፣ ይህ አሐዝ ግን በአማጺያን በተያዘው አካባቢ የደረሰውን ጉዳት አይጨምርም።

በሶሪያው አምባገነን መሪ ባሻር አልአሳድ እና በመንግሥታቸው የተጣለው ዕቀባ በቂ እርዳታ በአማጺያን እጅ ወዳሉ የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል።