ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቱርክ የተከሰቱት ርዕደ መሬቶች ለምን አስከፊ ጉዳት አደረሱ?
ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. ማለዳ። በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ ከሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በደረሰ ከባድ ርዕደ መሬት ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በቱርኳ ጋዚያንቴፕ ከተማ አቅራቢያ ነበረ የመጀመሪያው ከባድ ርዕደ መሬት የተከሰተው። በቅርብ ርቀት ደግሞ ሌላ ተከታይ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። ሁለተኛውም ከባድ የሚባል ነበረ።
በተደጋጋሚ ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎች ፈራርሰዋል። በዚህም ሳቢያ ሺዎች በፍርስራሾች ስር ተቀብረው ሊሆን ይችላል በሚል ነፍስ አድን ሠራተኞች እያካሄዱት ያለው ፍለጋ ተስፋ አሰቆራጭ ሰዓት ላይ ደርሷል።
አደጋው ከደረሰ አራተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በአካባቢው ባለው ከባድ ቅዝቃዜ ሳቢያ ሰዎችን በሕይወት ለማትረፍ ያለው ዕድል ተመናምኗል።
በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈው ከ11 ሺህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በቱርክ በኩል በደረሰው ጉዳት የሞቱ ሲሆን፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሶሪያውያንም የአደጋው ሰለባ ሆነዋል።
ለምን በርካታ ሰዎች ሞቱ?
ከባድ ርዕደ መሬት ነበር። በጋዚያንቴፕ አቅራቢያ የደረሰው በሳይንሳዊው የርዕደ መሬት መለኪያ “ግዙፍ” የተባለ ነው።
ይህም በሬክተር ስኬል 7.8 እንደሆነም ይገመታል። ርዕደ መሬቱ ማዕከል 18 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ የተፈጠረ ሲሆን፣ በዚህም በሕንጻዎች ላይም ከፍተኛ ውድመትን አድርሷል።
በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአደጋ ስጋት እና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆአና ፋዉር ዎከር “ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱ እጅግ አስከፊ ርዕደ መሬቶች ሁለቱ ብቻ አሁን በቱርክ ከተከሰተው ጋር ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ናቸው” ብለዋል።
ከባዱን ጉዳት ያስከተለው የመሬት መንቀጥቀጡ ኃይል ብቻ አይደለም። ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እንዲሁም መኝታ ላይ በሚሆንበት ንጋት ላይ መፈጠሩ አደጋውን የከፋ አድርጎታል።
የሕንፃዎቹ ጥንካሬም ለውድመቱ እና ለተከተለው ጉዳት ሌላው ምክንያት ነው።
በፖርትስማውዝ ዩኒቨርሲቲ የእሳተ ገሞራ ጥናት እና የአደጋ ተጋላጭነት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ካርመን ሶላና በበኩላቸው “በደቡብ ቱርክ እና በተለይም በሶሪያ ውስጥ ያሉ መሠረተ ልማቶች በሚያሳዝን ሁኔታ የደከሙ ናቸው። ስለሆነም ሕይወትን ለማዳን አብዛኛው ትኩረት የሚደረገው ነፍስ አድን ሥራው ላይ ነው” ብለዋል።
አክለውም ከአደጋው በኋላ ያሉት 24 ሰዓታት በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ወሳኝ ናቸው። ከ48 ሰዓታት በኋላ የተረፉት ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እንደሚቀንስ አመልክተዋል።
ይህ ከ200 ዓመታት በላይ ከባድ ርዕደ መሬት ያልታየበት ወይም ማስጠንቀቂያዎች ያልተሰጡበት አካባቢ ነበር። ስለሆነም ርዕደ መሬት ከለመዱ አካባቢዎች አንጻር የዝግጁነት ደረጃው ያነሰ ይሆናል።
የርዕደ መሬቱ ምክንያት ምንድን ነው?
ውሳዊው የምድር አካል እንደ ቅርፊት እርስ በእርሳቸው ተደራርበው በተቀመጡ ጠፍጣፋ አካላት (ፕሌት) የተሠራ ነው።
እነዚህ አካላት ብዙውን ጊዜ ለመንቀሳቀስ ይሞክራሉ። ነገር ግን ከሌላው ጋር በመተሻሸት እንዳይንቀሳቀሱ ይሆናሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ግፊቱ አንዱ አካል በድንገት እስኪያልፍ ድረስ ይበረታል። ይህም የመሬት ንጣፉን እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል።
በዚህኛው የአረቢያን ፕሌት ወደ ሰሜን እየተንቀሳቀሰ ከአናቶሊያን ፕሌት ጋር ይፋጫል። ከዚህ በፊት ለደረሰው የርዕደ መሬት መንስኤ የፕሌቶች ግጭት ትልቁ ምክነያት ነው።
እአአ ነሐሴ 13/1822 የደረሰው ርዕደ መሬት 7.4 የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ሰኞ ዕለት ከተመዘገበው 7.8 መጠን ያነሰ ነው።
ያም ሆኖ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የደረሰው ርዕደ መሬት በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በአሌፖ ከተማ ብቻ የ7,000 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። የድኅረ መንቀጥቀጥ አደጋዎች ደግሞ ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ቀጥለዋል።
የአሁኑን ርዕደ መሬት ተከትሎ በርካታ ድኅረ መንቀጥቀጦች ተከስተዋል። ሳይንቲስቶች ቀደም ሲል በክልሉ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ አዝማሚያ እንደሚከተል ይጠብቃሉ።
ርዕደ መሬት የሚለካው እንዴት ነው?
ርዕደ መሬት የሚለካው የአፍታ መጠን መለኪያ በሚባል መስፈርት ነው።
2.5 ወይም ከዚያ ያነሰ መንቀጥቀጥ ሊሰማን አይችልም። ነገር ግን በመሳሪያዎች እገዛ ሊታወቅ ይችላል።
እስከ አምስት የሚደርሱ መንቀጥቀጦች የሚታወቁ ቢሆንም የሚያደርሱት አነስተኛ ጉዳት ነው። በቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት 7.8 ሲሆን፣ ትልቅ በሚባለው ደረጃ ውስጥ ተካቷል።
በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎችን ወደ ፍርስራሽነት በመቀየር፣ አስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ነገር ግን ቁጥሩ በየደቂቃው የሚጨምር ሕይወትን በመቅጠፍ አሁን እንደተፈጠረው ዓይነት ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል።
በርዕደ መሬት መለኪያ ከ8 በላይ የሚመዘገብ ነውጥ አስከፊ ጉዳት ያስከትላል። በዚህም የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተበት ማዕከላዊው ስፍራ እና በአቅራቢያው የሚገኙ ግንባታዎችን እና ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ይችላል።
እአአ በ2011 በጃፓን የባሕር ዳርቻ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 9 ሆኖ ተመዝግቧል። ምድር ላይ ሰፊ ውድመት ከማስከተሉም በላይ ተከታታይ ግዙፍ ሱናሚዎችንም ፈጥሯል።
አንደኛው ሱናሚም በባሕህር ዳርቻው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ትልቅ አደጋ አስከትሏል።
አስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ ከፍተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ 9.5 ሲሆን በ1960 በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቺሊ ውስጥ የተከሰተው ነበር።