የአውሮፓ ህብረትና ተመድ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ጠየቁ

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከኤርትራ ሰራዊት ጋር በመተባበር በትግራይ እያካሄዱት ያለውን የጋራ ጥቃት እንዲያቆሙ ጠየቀ።

ህብረቱ በትግራይ በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባስን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 7፣ 2015 ዓ.ም ካደረገው ስብሰባ በኋላ ነው ይህንን መግለጫ ያወጣው።

ህብረቱ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ሙሉ በሙሉ እንዲወጡም ጠይቋል።

ከህብረቱ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተመሳሳይ መልኩ በትናንትናው ዕለት የኤርትራ ወታደሮች በአስቸኳይ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

23 ወራት የዘለቀውና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንደወጣ ገልጸው የሰላም ውይይቱ በአስቸኳይ እንዲጀመር ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት በትናንትናው መግለጫው የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና አፋር አጎራባች ክልሎች ያለውን ጦርነት እንዲያቆሙና ከወታደራዊ ዘመቻ እንዲቆጠቡም አሳስቧል።

የአውሮፓ ህብረትና ተመድ ይህንን መግለጫ ያወጡት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና አጋር ኃይሎች የሽረ ከተማን መያዛቸውን እየተገለጸ ባለበት ወቅት ነው።

የትግራይ ኃይሎች በትናንትናው ዕለት ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኃይሎች የሽረ ከተማን ጥቅምት 7፣ 2015 ዓ.ም መያዛቸውን ገልጸው በበርካታ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉና ነዋሪዎች ለተደጋጋሚ መፈናቀል ተዳርገዋል ብሏል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መጠለያ የሆነችው ሽረ መያዝን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከኤርትራ ኃይሎች በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ነገር ግን የፌደራሉ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የመከላከል እርምጃ እርምጃ እየወሰድኩ ያለሁት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ በማስፈለጉ ነው በማለት በትናንትናው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የህወሓት መጠነ ሰፊ ጥቃት ቡድኑን በሚደግፉ የውጪ አገር ጠላት ኃይሎች የአየር ክልል ጥሰት ጭምር የታገዘ ነበር” ብሏል።

ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን እና የፌደራል ተቋማትን በአሰቸኳይ መቆጣጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው ሲል አክሏል።

ለአምስት ወራት የቆየው የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ጦርነቱ ካገረሸበት ነሐሴ ወር ጀምሮ በትግራይ ላይ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የረድዔት ሰራተኞች ተናግረዋል።

ህብረቱም በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሰለማዊ ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጦርነቱን ለማርገብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እና ግጭቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ ማናቸውም ተግባራት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል።

ጦርነቱ ቀጣናዊ መሆኑ በሰላማዊ ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ውድመት፣ መፈናቀል እና ግፍ በማባስ የቀጣናውን መረጋጋት አደጋ ላይ ይጥላል ብሏል።

በተደጋጋሚ ጦሯ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የተጠየቀችው ኤርትራ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ባትሰጥም ከሰሞኑ " ኤርት የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ጦርነት አጥፊ ሚና እየተጫወተች ነው" በማለት ያቀረበውን ሪፖርት “ተበዳዩን የመውቀስና ወንጀለኛውን በሰብዓዊ መብት ሽፋን የማዳን ተግባር” ስትል አጣጥላዋለች።

በቅርቡ በአዲ ዳኤሮ እና በሽረ ዙሪያ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ ውጊያዎች መበባስ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከገቡት ተደጋጋሚ ቃል በተቃራኒ የቆመ ነው ሲል የአውሮፓ ህብረት መግለጫ ወቅሷል።

በሽረ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኛ መገደልን ጨምሮ በርካታ ህዝብ መስዋዕትነት እየተከፈለ እንደሆነ ገልጾ የየለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን እና የሰብአዊ መብቶችን ማክበር የሁሉም ግዴታ መሆኑን አስምሯል።

የተባበሩት መንግሥታትም በትግራይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ባልለየ መልኩ ጥቀት እየተፈጸመ ነው ብሏል። “ሰላማዊ ነዋሪዎችን ባልለየ መልኩ በመኖሪያ አካባቢዎች ጨምሮ እየደረሰ ባለው ጥቃት ንጹሃን ዜጎች እየተገደሉ ነው። መሰረተ ልማቶች እየወደሙ ነው እንዲሁም መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተገደቡ ነው “ በማለት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናግረዋል።

የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ኢላማ እንደማያደርግ መግለጹ ይታወሳል።

በትናንትናው ዕለትም ባወጣው መግለጫ “ህወሓት ሰላማዊ ሰዎችን እና ሲቪል ተቋማትን እንደ መሸሸጊያ የመጠቀም ልምድ ስላለው፤ ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ራሳቸውን ከህወሓት የጦር እንቅስቃሴዎች ያርቁ” ሲል ጠይቋል።

በተጨማሪም እስካሁን በሰላማዊ ሰዎች እና በሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ደርሶ ሊሆን በሚችለው ጉዳት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ክስተቱ ያጋጠመበትን ሁኔታ ምርመራ አደርጋለሁ ብሏል። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአውሮፓ ህብረት በተደጋጋሚ እንዳሉት በትናንትናው ዕለትም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ወታደራዊ መፍትሄ የለውም ብለዋል።

ሁለቱም ወገኖች በአፍሪካ ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ውይይት እንዲመሉሰም ጠይቀዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ማገባደጃ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኅብረቱ ቅዳሜ ጥቅምት 4/2015 ዓ. ም. የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀጠል እንዳሳሰበው መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ፤ የትግራይ አስተዳደር ጥቅምት 5/2015 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ያወጣውን መግለጫ በበጎ ጎኑ እንደሚቀበለው አስታውቋል።

የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ የሚያደርገውን የፌደራል ማዕከላት የመቆጣጠር ወታደራዊ ዘመቻውን እንደሚቀጥል በገለጸበት መግለጫው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውይት ለመፍታት አሁንም ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

ነገር ግን “በሎጂስቲክስ አለመመቻቸት ምክንያት” ተብሎ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ አቁመው ወደ ውይይቱ እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።