ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት በትግራይ የመከላከል እርምጃ የምወስደው የአገር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ነው አለ
የፌደራሉ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የመከላከል እርምጃ እየወሰድኩ ያለሁት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ በማስፈለጉ ነው አለ።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ጥቅምት 7/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የህወሓት መጠነ ሰፊ ጥቃት ቡድኑን በሚደግፉ የውጪ አገር ጠላት ኃይሎች የአየር ክልል ጥሰት ጭምር የታገዘ ነበር ብሏል።
ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን እና የፌደራል ተቋማትን በአሰቸኳይ መቆጣጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው ሲል አክሏል።
የፌደራሉ መንግሥት ይህን ያለው የትግራይ ኃይሎች የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ ተፈጻሚ እንዲሆን በጠየቁበት እና በትግራይ የሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች መበራከታቸው በሚገለጽበት ወቅት ነው።
የአፍሪካ ኅብረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ያቀረበው ጥሪ ተፈጻሚ እንዲሆን የትግራይ ኃይሎች ጠይቀው ነበር።
የትግራይ ኃይሎች ትናንት ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት ያወጡትን መግለጫ በበጎ ጎኑ እንቀበለዋለን ብለዋል።
ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት ቅዳሜ ጥቅምት 4/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ጦርነቱ በአስቸኳይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆሞ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲጀመር በአጽንኦት ጠይቀው ነበር።
በትግራይ ክልል በተለይ ደግሞ በሽረ ከተማ እየተፈጸሙ ነው የተባሉትን የአየር ጥቃቶች በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ጥቃቶቹ አሳሳቢ ናቸው ብለዋል።
ሳማንታ በትዊተር ገጻቸው ባለፉት ቀናት በትግራይዋ ሽረ ከተማ ተፈጽመዋል የተባሉት የአየር ጥቃቶች እጅጉን አሳሳቢ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ቀናት በሽረ ከተማ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አንድ የረድዔት ሰራተኛው መገደሉን ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ቡድን (ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ) መግለጹ ይታወሳል።
"ለሰላም ንግግር ዝግጁ ነኝ"
የፌደራሉ መንግሥት በዚህ መግለጫው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን በንግግር ለመፍታት አሁንም ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።
መግለጫው መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የሰላም ንግግር ዝግጁ ነኝ ካለ በኋላ መንግሥት “አጠቃላይ የሆነ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ድርድር መደረግ አለበት” ብሎ እንደሚያምን በመግለጫው ተመላክቷል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ነገር ግን ምክንያቱ በግልጽ ባልተገለጸ ሁኔታ ንግግር ሊደረግበት የታሰበው ቀን ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ከመነገሩ ባሻገር፣ አሸማጋይ ይሆናሉ ከተባሉት ሦስት የቀድሞ አፍሪካውያን መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የኬንያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መሳተፍ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
“መከላከያ ለሕግ ተገዢ ነው”
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መርሆች እንደሚገዛ ግልጽ ማድረግ ይፈልጋል” ብሏል።
የፌደራል መንግሥት ሠራዊቱ የሰላማዊ ሰዎች ጉዳትን ለመቀነስ በከተሞች አካባቢ ውጊያ ላለማድረግ ጥረት ያደርጋል ያለ ሲሆን፤ ይህን ተፈጻሚ ለማድረግም ለሠራዊት አባላቱ መመሪያ መሰጠቱን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በቁጥጥሩ ስር በሚገኙ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እና የሠራተኞችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሚሰራ ገልጿል።
ህወሓት ሰላማዊ ሰዎችን እና ሲቪል ተቋማትን እንደ መሸሸጊያ የመጠቀም ልምድ ስላለው፤ ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እራሳቸውን ከህወሓት የጦር እንቅስቃሴዎች ያርቁ ሲል ጨምሮ ጠይቋል።
በመጨረሻም በትግራይ ክልል ያሉ ዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ አለብኝ ያለው መንግሥት፤ እስካሁን በሰላማዊ ሰዎች እና በሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ደርሶ ሊሆን በሚችለው ጉዳት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ክስተቱ ያጋጠመበትን ሁኔታ ምርመራ አደርጋለሁ ብሏል።