ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ይህንን እየጻፍኩ ወታደራዊ ድሮን በከተማዬ ላይ እያንዣበበ ነው”- ጋዜጠኛው ከመቀለ
በትግራይ ክልል ጦርነቱ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ነዋሪዎች የጦርነቱ ተሳታፊ ሆነዋል።
የትግራይ ኃይል አዛዦች እንደ አዲስ ሕዝቡ እንዲከት ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም ሰላማዊ ሰዎች ወደ ጦርነቱ እንዲገቡ አስገድደዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት በመወገን ወደ ጦርነት የገባችው ኤርትራ የክተት ጥሪ እንዲሁም አፈሳዎችን እያካሄደች ስለመሆኑም ተነግሯል።
ቢቢሲ ከዓለም ተቆራርጣ በምትገኘው በትግራይ ዋና ከተማ መቀለ የሚገኝ ጋዜጠኛ እያለፈበት ያለበትን መንገድ ልዩ ዘገባ አግኝቷል።
300 ሺህ ሕዝብ የሚጠጋ ነዋሪ ባላት መቀለ ድሮኖች (ሰው አልባ አውሮፕላኖች) በየቀኑ በሚባል ሁኔታ በከተማዋ ሰማይ ላይ ይበርራሉ።
ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ ራሱ ድሮኖች በላዬ ላይ ሲያንዣብቡ ይሰማኛል።
እርግጠኛ ያለመሆን ስሜት ይሰማኛል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች የሕጻናት መጫዎቻ እና የመኖሪያ ስፍራዎችን መትተዋል። ኢላማዎቹ ምን እንደሆኑ ግን ግልጽ አይደለም።
በዚህ ሳምንት የትግራይ ጦር አቅም ያለው ሰው ሁሉ ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል።
ለሁለት ዓመት ያህል ጦርነት ቢያደቀውም ሕዝቡ ለመዋጋት ጥሪውን ተቀብሎ እየከተተ ነው።
“ትግሉን አለመቀላል እንደ ነውር ነው የሚታየው” ስትል ለደኅንነቷ ሲባል ስሟን ቢቢሲ የማይጠቅሳት ነዋሪ ትናገራለች።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የትግራይ ተወላጆች የፌደራሉን አስተዳደር አንቀበልም በሚል በጽናት ቆመዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የክልሉ አመራሮች ከአራት ዓመት በፊት ያጡትን ሥልጣን ለማስመለስ ሲሉ አምጸዋል ሲሉ ይከሳሉ።
በትግራይ ያሉ ነዋሪዎች ሁሉ መብታቸውን ለማስከበር ተነስተዋል።
በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከአምስት ወራት ቆይታ በኋላ መፍረሱን ተከትሎ ጦርነቱ ነሐሴ ወር ላይ አገርሽቷል።
የህወሓት አመራሮች ሕዝቡ ለህልውናው እንዲታገል ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ሴቶች እና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍሎች ዘመቻውን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ሴቶች ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ከተጠሩ ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን እየተናገሩ ነው።
“ትግራዋይ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል። መብቶቼን ለማስከበርና መሬቴን ለማስጠበቅ ሥልጠና በመውሰዴ ደስተኛ ነኝ” ስትል የ23 ዓመቷ ወጣት ነገረችኝ።
ትግራይ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ እገዳ ስለተጣለባት የኑሮ ሁኔታውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መጥቷል።
የስልክ መስመሮች እና የኢንተርኔት አገልግሎት ከቆሙ ከአንድ ዓመት በላይ አልፎናል። ከሌላው ዓለም ተቆራርጠን ነው ያለነው።
በርካቶች ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቸቻው መልዕክት ለመላክ ደብዳቤ ወደመጻፍ ተመልሰዋል።
አንዳንዶች ደግሞ ወደ አማራ ክልል ድንበር በመሄድ ስልክ ይደውላሉ፣ እንዲሁም ከውጭ አገር ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ፣ ከዘመድ የተላከላቸውን ገንዘብ ይቀበላሉ።
ዜና ለመስማትም ሆነ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ በርካቶች በመንገድ ዳር በአንድ ሬድዮ ዙሪያ ይሰባሰባሉ። ሁሉም ነዋሪ ስለሰላም ሂደቱ ያወራል እንዲሁም ዜናዎቹን በትኩረት ይከታተል።
ነገር ግን የትግራይ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ውይይት ዝግጁ እንዳልሆነ ነው የሚያምኑት፤ ለዚህም ያልቆመውን የቦምብ ጥቃት ይጠቅሳሉ።
በትግራይ መሥራትም ሆነ ገንዘብ ማፍራት አንችልም። ባንኮችም ስለተዘጉ ገንዘባችንንም ማውጣት አንችልም። በዚህም የተነሳ የንግድ ተቋማት እንቅስቃሴያቸው ቀጥ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ክፍት ቦታ ላይ ያሉ ገበያዎች ተስፋፍተዋል። ገንዘብም የሚዘዋወረው በጥቁር ገበያ ሲሆን፤ ደላሎች ቢያንስ 30 በመቶም ኮሚሽን ይጠይቃሉ።
ከጥቂት ወራት በፊት 50 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ መጠነኛ መሻሻልም አሳይቷል።
ጎረቤቶቼ ኑሯቸውን የሚገፉት ከአሜሪካ እና ከካናዳ ቤተሰቦቻቸው በሚልኩላቸው ገንዘብ ነው።
አንደኛው ጎረቤቴ ቤተሰቦቹ ገንዘብ ካልላኩ አምስት ልጆቹን መመገብ አልችልም ብሎኛል።
በአሜሪካ ውስጥ ሁለት እህቶች ያሉት ሲሆን፣ በትግራይ ከተጣለው ከበባ በኋላ አራት ጊዜ ገንዘብ ተልኮለታል።
ጦርነቱን ተከትሎ መሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ እና ነዳጅን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ ታግዷል። በርካቶች በእግራቸው፣ ወይም በጋሪ እንዲጓዙም ተገደዋል።
የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። የጤፍ ዋጋ በየሳምንቱ ጭማሪ የሚያሳይ ሲሆን ዋጋውም የማይቀመስ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት የ100 ኪሎ ጤፍ ዋጋ 265 ዶላር (15 ሺህ ብር) አካባቢ ሲሆን ከዓመት በፊት 85 ዶላር (5 ሺህ) ብር ነበር። በተጣለው ከበባ ምክንያት መድኃኒት ስለማይገባ በርካቶች እየረገፉ ነው።
ለረዥም ጊዜ በሕመም የሚሰቃዩ ሰዎችም መድኃኒት ለማግኘት እየተንገላቱ ሲሆን፣ የመድኃኒቶች ዋጋም በአሥር እጥፍ ጨምሯል።
በትግራይ የሚፈጸመው አዳዲስ የአየር ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን መቅጠፉን በመቀጠሉም በርካታ ወጣቶች ትግሉን ለመቀላቀል ምክንያት እየሆነ ነው።
አንዲት የ29 ዓመት የትግራይ ነዋሪ ሦስት የቤተሰቧ አባላት፣ ሁለት ወንድሞቿና እህቷ የትግራይን ጦር እንደተቀላቀሉ ነገረችኝ።
ላለፉት ሁለት ወራትም ጊዜዋን እንዲሁም ያላትን በመጠቀም በጦር ግንባር ላሉ የትግራይ ጦር አባላት ምግብ እያዘጋጀች ትገኛለች።
ሌሎች ነዋሪዎችም ያላቸውን ምግብ ወደ ጦር ግንባር ቤተሰቦቻቸውን ከላኩ ጋር ተካፍለው ይቋደሳሉ።
ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ውይይት ሊጀመር እንደሚችል ዜና ሲሰማ ሕዝቡ ደስተኛ ነበር።
ነገር ግን ውይይቱ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል።
በትግራይ በርካቶች ሰላምን ይሻሉ፤ ሰላም እንዲመጣ ለመማጸንም ወደ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ይሄዳሉ።
በምሽቶች እነዚህ የእምነት ተቋማት ሙሉ ናቸው፤ ሕዝቡም ጦርነቱ እንዲያበቃ እየጸለየ ነው።
*ቢቢሲ የጋዜጠኛውን እና ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸውን ሰዎች ማንነት ለደኅንነታቸው ሲል ይፋ አያደርግም።