በአማራ ክልል በዚህ ሳምንት በተፈፀሙ የድሮን ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል፣ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ እና በሰሜን ወሎ ዞን፣ ቡግና ወረዳ በዚህ ሳምንት ውስጥ በተፈፀሙ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች፣ በድሮን ጥቃቶቹ ታጣቂዎች እና በአካባቢዎቹ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።
የቡቢኝ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ፣ ዋበር በተባለው የወረዳው አካባቢ የድሮን ጥቃት ሲፈፀም በወራት ውስጥ ይህ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ሰኞ ኅዳር 17/2016 ዓ.ም. በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“የድሮን ጥቃቱ የተፈፀመው በአካባቢው ባለ ‘ታረቀኝ ምግብ ቤት’ ላይ ነው። በጥቃቱ በምግብ ቤቱ የነበሩ ታጣቂዎች እና ምግብ ቤት ውስጥ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። የተቀበሩትም አንድ ላይ ነው” ብለዋል።
ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪም ሰኞ ዕለት ምሽት 1፡00 ሰዓት አካባቢ ላይ በተፈፀመው የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም. እዚያው አካባቢ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈፅሞ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ያስታወሱት እኚህ እናት፣ ታጣቂዎችን ጨምሮ 16 ሰዎች መገደላቸውን መስማታቸችን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“የጥቃቱ ሰላባዎች የዚያኑ ዕለት በጨለማ በባትሪ እገዛ ነው የተቀበሩት። ምን ያህል ሰላማዊ ሰዎች እና ታጣቂዎች እንደተገደሉ ቁጥራቸው በውል አልታወቀም” ብለዋል ነዋሪዋ።
በአካባቢው የተፈፀመውን ተደጋጋሚ ጥቃት ተከትሎ በርካቶች ከቀያቸው መሸሻቸውንም ነዋሪዋ ጨምረው ተናግረዋል።
“በአካባቢው በመንግሥት ኃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻ እና ግድያ እንደሚፈፀም” የሚናገሩት ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት እንደሆኑ ለቢቢሲ የገለጹት ነዋሪም፣ በስጋት በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት በአካባቢው የትራንስፖርትም ሆነ ሌላ አገልግሎት እና የተረጋጋ መንግሥታዊ አስተዳደር የለም።
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ፣ ዳሪያ እየሱስ ቀበሌ ትናንት ረቡዕ ኅዳር 19/2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በተፈፀሙ ሁለት የድሮን ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጥቃት የተፈፀመባት አካባቢ በቅርቡ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ ከተካሄደባት ላሊበላ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኝ ቀበሌ ናት።
የድሮን ጥቃቱ የተፈፀመበት ዕለት የገበያ ቀን ነበር የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በመጀመሪያ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት በሲኖትራክ ተጭነው ሲጓዙ የነበሩ ታጣቂዎች መመታታቸውን እና ጩኸት ሰምተው አስክሬን ለማንሳት ወደ ሥፍራው የሄዱ ሰላማዊ ሰዎች እዚያው ቦታ ላይ በድጋሚ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ተገድለዋል ብለዋል።
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የድሮን ጥቃቶች ተፈፅመዋል። በዚህም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫም በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት እየተፈፀሙ ያሉት የድሮን ጥቃቶች እና ሌሎች ግጭቶች እንዳሳሰበው መግለጹ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋበር ከተማ በሚገኝ የአውቶብስ መናኽሪያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአውቶብስ ለመሳፈር ሲጠብቁ የነበሩ 13 ሰዎች መገደላቸውንም አመልክቷል።
ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ዋደራ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ከመንግሥት ኃይሎች በኩል ተፈጽሟል በተባለ የድሮን ጥቃትም ሦስት መምህራንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውንም በመግለጫው ጠቅሷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በመግለጫው ላይ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቃቶች በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ “በዘፈቀደ የሰዎችን ሕይወት ከማጥፋት ጋር” የሚስተካከል ነው ሲልም አሳስቦ ነበር።
በሰሜን ወሎ ዞን፣ ቡግና ወረዳ ትናንት ረቡዕ ኅዳር 19/2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ምን ያህል ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ መለየት እንዳልቻሉ የገለጹት አንድ ነዋሪ፣ ሁለት ጊዜ በተፈፀሙት ጥቃቶች ታጣቂዎቹን ጨምሮ ቢያንስ 40 ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው በጥቃቶቹ ታጣቂዎቹን ጨምሮ ከ65 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና የቆሰሉም መኖራቸውን ገልጸዋል።
“የእህቷን ልጅ ከታጣቂዎቹ ጋር መኪናው ላይ መሳፈሩን ሰምታ ከመኪናው ላይ ለማስወረድ የሄደች እናት ከተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች መካከል ትገኝበታለች” ብለዋል ነዋሪው።
ላሊበላ በተለያዩ ጊዜያት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ከባድ ወጊያ ካስተናገዱ የክልሉ አካባቢዎች አንዷ ስትሆን፣ አሁን ላይ የተኩስ ድምጽ ባይሰማም፣ የነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንደተስተጓጎለ ነው።
“ከተማው በብዙ ችግር ውስጥ ነው ያለው፣ በከተማው እርዳታ ከቆመ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል። በዚህም ምክንያት ከተማው ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጦት አለ” ብለዋል ነዋሪው።
እንደ ነዋሪዎቹ ከሆነ በምሥራቅ ጎጃም ውስጥ በምትገኘው ቢቡኝ ወረዳ እና በሰሜን ወሎ ውስጥ በምትገኘው ቡግና ወረዳ ውስጥ ጥቃት የተፈፀመባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ያለበት ነው።
ተፈፅመዋል ስለተባሉት የድሮን ጥቃቶች የክልሉ ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት አስካሁን ያሉት ነገር የለም። ቢቢሲ ከባለሥልጣናቱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደደጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ለወራት እየተካሄደ ባለው ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና ያለ ፍርድ ግድያን ጨምሮ ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ሌሎችም ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል።
መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ውጥረት ተባብሶ ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ወደለየለት ግጭት መግባቱ ይታወሳል።
በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት የክልሉ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያ እንዳለ ይሰማል።
የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ እና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች የሉም።












