ልዑል ቻርልስ ከኦሳማ ቢን ላደን ቤተሰብ 1 ሚሊዮን ፓውንድ መቀበላቸው ተገለጸ

የዌልሱ ልዑል ቻርልስ ከኦሳማ ቢን ላደን ቤተሰብ 1 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀብለው እንደነበር ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ዘገበ።

ልዑል ቻርልስ ኦሳማ ቢን ላደን ከተገደለ ከሁለት ዓመታት በኋላ እአአ 2013 ላይ ከሁለት የቢን ላደን ወንድሞች ገንዘቡን መቀበላቸው ተገልጿል።

ልዑሉ ገንዘቡን የተቀበሉት በበላይነት ለሚመሩት ‘ዘ ፕሪንስ ኦፍ ዌልስስ ቻሪተብል ፈንድ’ ተብሎ ለሚጠራው በጎ አድራጊ ተቋም መሆኑም ተነግሯል።

የልዑሉ ይፋዊ መኖሪያ ቤት ክላረንስ ሐውስ ልዑሉ ገንዘቡን ከመቀበላቸው በፊት የበጎ አድራጎት ተቋሙ ጉዳዩን በጥልቅ መርምሯል ያለ ሲሆን፤ ለጉዳዩ ሌላ ገጽታ መስጠት ትክክል አይደለም ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

ቢን ላደን እአአ ከ1994 በኋላ ከቤተሰቡ ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን፤ ገንዘቡን ለልዑሉ ሰጥተዋል የተባሉት ወንድሞች ከቢን ላደን እንቅስቃሴዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለመሆናቸው ግልጽ አይደለም።

ልዑል ቻርልስ ከንግሥት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ በኋላ ንግሥናውን ይቀበላሉ።

ክላረሰን ሐውስ ጉዳዩን በተመለከተ ታይምስ ይዞት በወጣው ዘገባ ላይ የተካተቱ በርካታ ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች አሉ ብሏል።

በዘገባው መሠረት ልዑል ቻርልሰ ከባከር ቢን ላደን እና ከባከር ወንድም ሻፊቅ ጋር በይፋዊ መኖሪያ ቤታቸው ከተገናኙ በኋላ ገንዘቡን ተቀብለዋል።

ሰንደይ ታይምስ ልዑል ቻርልስ ገንዘቡን እንዳይቀበሉ በክላረንስ ሐውስ እና በረድኤት ድርጅቱ ምክር ቢለገሳቸውም አሻፈረኝ ብለዋል ሲል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ የ‘ዘ ፕሪንስ ኦፍ ዌልስስ ቻሪተብል ፈንድ’ ሰብሳቢ ሰር አየን ቼሻየር እአአ 2013 ላይ ልገሳውን ለመቀበል ከውሳኔ ላይ የተደረሰው አምስት አባላት ያሉት ተቋሙን በበላይነት የሚመሩ ግለሰቦች “በጥንቃቄ” ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የበጎ አድራጊው ተቋም ሊቀ መንበር ሰር አየር ቼሻየር፤ ገንዘቡን የመቀበል ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት መንግሥትን ጨምሮ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ሰንደይ ታይምስ የገንዘቡ ልገሳ በዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ቢሮም ጸድቋል ሲል አስነብቧል።

የልዑሉ ተቋም በዩናይትድ ኪንግደም እና በቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ለተሰማሩ ለትርፍ ላልተቋቋሙ ድርጅቶች ገንዘብ ይለግሳል።

ኦሳማ ቢን ላደን በአሜሪካ በጥብቅ ከሚፈለጉ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ይገኝ ነበር። ቢን ላደን በኒው ዮርክ እና ዋሽንግተን ‘ሴፕቴምበር 11’ ተብሎ የሚጠራውን ጥቃት እንዳቀነባበረ ይታመናል።

በዚህ ጥቃት ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።

የአሜሪካ ኃይሎች ቢን ላደንን እአአ 2011 ፓኪስታን ውስጥ ባደረጉት ዘመቻ መግደላቸው ይታወቃል።