ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ ክልል ፍጻሜ እየተቃረበ ይሆን?
በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የሆኑ እና ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ሆነው ለመደራጀት የተለያዩ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ የነበሩ ዞኖችን እና ልዩ ወረዳዎች በተለያዩ ክልሎች ስር ለመደራጀት የሚያስችላቸውን ውሳኔ በምክር ቤቶቻቸው አማካኝነት እያሳለፉ ነው።
ከ50 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን የያዘው የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከአገሪቱ ትልቅ ከሚባሉት ክልሎች መካከል አንዱ ሆኖ ቆይቷል።
ከ25 ዓመታት በፊት አሁን በሥራ ላይ ያለው ቋንቋን እና ማንነትን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ አወቃቀር ተግባራዊ በተደረገበት ጊዜ በአምስት ክልሎች ተዋቅረው የነበሩ ክልሎችን በማዋሃድ በተፈጠረው የደቡብ ክልል ራስን የማስተዳደር ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር።
የደቡብ ክልል አመሰራረት
ኤርትራን ጨምሮ በ14 ክፍላተ አገራት ተዋቅራ የነበረችው ኢትዮጵያ ኢህአዴግ ሥልጣን ጨብጦ የሽግግር መንግሥት ሲቋቋም፣ ኤርትራ ሳትካተት ቋንቋና ማንነትን መሰረት ባደረገ አዲስ የክልል አወቃቀር ተግበራዊ ሆነ።
በዚህም አከላለል አዲስ አበባን ጨምሮ በመላዋ አገሪቱ 14 ክልሎች የተዋቀሩ ቢሆንም፣ በሂደት አሁን የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተባለው በቦታው አልነበረም።
ከዚያ ይልቅ ግን የክልል መዋቀሩ ተግባራዊ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ አምስት ክልሎች ተዋህደው የደቡብ ክልል እንዲመሰረት ተደረገ።
በወቅቱ ሁሉም ክልሎች ስያሜያቸው በቁጥር የነበረ ሲሆን በዚህም ክልል 7 ጉራጌ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ፣ የም፣ ሐላባና ስልጤን፤ ክልል 8 ሲዳማን፣ ጌዲኦን፣ አማሮን እና ቡርጂን የያዙ ነበሩ።
በተጨማሪም ክልል 9 ወላይታ፣ጋሞ ጎፋ፣ ዳውሮ እና ሌሎችንም የያዘ፤ ክልል 10 ደግሞ ደቡብ ኦሞ ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን እንዲሁም ክልል 11 ደግሞ ከኦሞ ወንዝ ባሻገር ያሉትን ሕዝቦች የያዙ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ነበሩ።
ነገር ግን በወቅቱ ተቃውሞን ባስነሳ ሁኔታ በተሰጠ ውሳኔ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ 56 የሚደርሱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን በማዋሃድ ትልቁ የደቡብ ክልል እንዲመሰረት ተደርጓል።
ክልል የመሆን ጥያቄ
በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ በደቡብ ክልል በተናጠል ክልል ሆኖ የመውጣት ጥያቄ በክልሉ ካሉ ሁሉም ዞኖች የቀረበ ዋነኛ ጉዳይ ነበር።
በተለይም አለመረጋጋት ብሎም ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት የሆኑ ጥያቄዎች በሲዳማ እና በወላይታ ውስጥ ተስተውለው ነበር።
በተለይ የሲዳማ ጥያቄ እየተጠናከረ በመምጣቱ የተነሳ በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ በክልልነት በመደራጀት ከደቡብ ክልል የወጣ የመጀመሪያው ዞን በመሆን 10ኛው የአገሪቱ ክልል ለመሆን ቻለ።
በማስከተልም የደቡብ ክልል ባዘጋጀው መዋቅር አማካይነት የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮ፣ የሸካ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ በአንድ ላይ ተጣምረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ክልል ለመመስረት ባለፈው ዓመት ከተደረገው ምርጫ ጎን ለጎን በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ 11ኛው ክልል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከዚያው ከደቡብ ክልል ወጣ።
ከዚህም በኋላ ቢሆን በቀሩት የክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ውስጥ በጥምረት አልያም በተናጠል ክልል የመሆን ጥያቄዎች የደቡብ ክልል ዋነኛው ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
አዲስ አወቃቀር
የሲዳማንና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን ራሳቸውን ችለው እንዲዋቀሩ ያመቻቸው የደቡብ ክልል መስተዳደር የቀረቡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርጎ ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ነው።
በየአካባቢው የቀረቡ ክልል የመሆን ፍላጎቶችን በተናጠል ለመመለስ ከተሞከረ አሁን አገሪቱ ካሏት ክልሎች የበለጡ ክልሎች ከተቀረው የደቡብ ክልል ሊወጡ ይችላሉ።
በአሁኑ ሰዓትም ተጎራባችና በአኗኗርና በባህል ተቀራራቢ የሆኑ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን በማጣመር ተጨማሪ ክልሎችን ለማደራጀት እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም መሠረት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የካፋ፣ የጌዲኦ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች በተጨማሪም የአማሮ፣ የደራሼ፣ የአሌ፣ የቡርጂ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል ስር ለመሆን በምክር ቤቶቻቸው አማካይነት ውሳኔ አሳልፈዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በአንድ ክልል ስር እንዲወቀሩ ሀሳብ የቀረበላቸው የሃድያ፣ የከንባታ፣ የሀላባ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ ዞኖች እና ዬም ልዩ ወረዳ ሲሆኑ፣ እስካሁን ድረስ ከጉራጌ እና ከስልጤ ዞን ምክር ቤቶች በስተቀር የሌሎቹ ምክር ቤቶች ሀሳቡን መቀበላቸውን አሳውቀዋል።
የደቡብ ክልል መስተዳደር ይህ አዲሱ የክልሉ አወቃቀር “የሕዝቡን የቆየ አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መተሳሰብ ብሎም ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማይጎዳ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን” መረዳቱን ገልጾ፣ አዲሱ የክልል አደረጃጀት ውጤታማ እንዲሆን ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብሏል።
የደቡብ ክልል ፍጻሜ
ይህ ሀሳብ ግን አሁንም የራሳቸውን የተናጠል ክልል ለመመስረት በሚፈልጉ ወገኖች ተቃውሞ እየገጠመው ቢሆንም የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳዎቹ ምክር ቤቶች በአዲስ ክልል ስር የመደረጀቱን ዕቅድ እየደገፉት ነው።
የጉራጌ እና የስልጤ ዞኖች ራሳቸውን ችለው በክልል እንዲዋቀሩ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን አሁንም በዚሁ ውሳኔያቸው የሚገፉ ከሆነ የደቡብ ክልል ያቀደው አደረጃጀት እንቅፋት ይገጥመዋል።
ነገር ግን የተቀረውን የደቡብ ክልል በሁለት ክልሎች የማወቀሩ ዕቅድ በአብዛኞቹ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ተቀባይነትን አግኝቷል።
አዲሱን አደረጃጀት ለማስፈጸም እየሰራ ያለው የደቡብ ክልል መስተዳደር እስካሁን በአዲሶቹ የክልል አወቃቀር ስር ለመታቀፍ የወሰኑት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ውሳኔያቸውን “በሳል” ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
ይህ ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነትን አግኝቶ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በአወቃቀሩ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የተለየ የሆነው እና በአስተዳደር መዋቅር እንዲሁም በማንነት ጥያቄዎች ሲናጥ የቆየው የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፍጻሜው ይሆናል።
የደቡብ ክልልም ሲቀርቡለት የነበሩትን ራስን በራስ የማስተዳደር ፍላጎትን ምላሽ ለመስጠት “የአደረጃጀት ጥያቄዎች በሕዝቦች መካከል ያለውን ብዝሃነት በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ሲሰራ መቆየቱን” ጠቅሷል።
በዚህም ቀድመው የራሳቸውን ክልል ከመሰረቱት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውጪ ያሉት የክልሉ ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ለሁለት ተከፍለው አዲስ ክልል በመመስረት የኢትዮጵያ 12ኛ እና 13ኛ ክልሎች ይሆናሉ።