ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እና የግብፅ አቤቱታ
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት፣ ይህ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት እንደምታከናውን ካሳወቀች ሰንብታለች።
ግብፅም ልክ እንደ ሁልጊዜው በቅድሚያ የግድቡ ውሃ አሞላልና አጠቃላይ ሥራን በሚመለከት ስምምነት መደረስ አለበት ስትል ቆይታለች።
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስለመጀመሩ በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ ግብፅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አሁንም አቤቱታ አስገብታለች።
ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት በነሐሴ ወር እንደምታካሂድ የገለጸች ቢሆንም እስካሁን ግን በይፋ ስለሙሌቱ ያለችው ነገር የለም።
የሳተላይት ምስሎችን የሚጠቅሱ ወገኖች ሙሌቱ መጀመሩን፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ደግሞ ሥራው መከናወኑ እየተገለጸ ነው።
ቢቢሲ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ‘ሙሌቱ በተያዘው ዕቅድ መሰረት እንደሚካሄድ’ ከመግለጽ ባሻገር ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልቻለም።
ሦስተኛ ውዙር ሙሌት
ኢትዮጵያ ግንባታውን ማከናወን ከጀመረች አስር ዓመታትን ያስቆጠረው ግዙፉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው።
ግብፅ ከ85 በመቶ በላይ ውሃው ከኢትዮጵያ ከሚመነጨው የአባይ ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል ያላትን ስጋት አጥብቃ ስታሰማ ቆይታለች።
የአፍሪካ ኅብረት፣ የአረብ ሊግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለኃያላኑ ምዕራባውያን በተደጋጋሚ ከግድቡ ጋር በተያያዘ እንዲደግፏት እየጠየቀች ትገኛለች።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ሰኔ ግም ብሎ የኢትዮጵያ ከባዱ የክረምት ወቅት ሲጀምር ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን በማንሳት ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ የምትላቸውን አገራትና ተቋማት፣ በውሃ አጠቃቀሙ ዙሪያ ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲደረስ እንዲያሸማግሏት ግፊቷን ታጠናክራለች።
እነሆ አሁንም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ባለፈው አርብ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ በተናጠል ግድቡን በውሃ መሙላት ቀጥላላች በሚል የአገራቸውን ተቃውሞ አስመዝግበዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሱዳንና ግብፅ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ መሙላት አትችልም በሚል ተቃውሞና ማስጠንቀቂያ ቢሰነዝሩም፣ የውሃው ሙሌት የግንባታው ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑንና ጥያቄውም ተቀባይነት የሌለው ነው በሚል ሁለት ዙር ሙሌት በተሳካ ማካሄዷን ኢትዮጵያ አሳውቃለች።
ሦስተኛው ዙርም በዚህ ዓመት ነሐሴ ወር ላይ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳወቀ ሲሆን፣ አንዳንድ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ግን ከሳምንት በፊት ጀምሮ የሳተላይት ምስሎችን ዋቢ በማድረግ የግድቡ ሦስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጀመሩን ሲዘግቡ ቆይተዋል።
ከቀናትበፊት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ ላይም “ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ የመሙላት የተናጠል እርምጃዋን ቀጥላበታለች” ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አሕመድ ሃፌዝ ካይሮ ላይ ባለፈው ሳምንት ባሰራጩት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት እንደምታከናውን ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም. በጻፈችው ደብዳቤ እንዳሳወቀች ‘ኢጂፕሺያን ስትሪትስ’ የተሰኘ ድረ ገጽ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በኩል ግን እስካሁን ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስለመጀመሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
የግብፅ አቤቱታ
አሁንም ሆነ ቀደም ሲል የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት በታላቁሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የውሃ ሙሌት እና ሥራ ዙሪያ በሚያነሱት ቅሬታላይ፣ ኢትዮጵያ ሦስቱ አገራት በአውሮፓውያኑ 2015 የደረሱትን ‘የመርሆች ስምምነት’ ጥሳለች በማለት ይከስሳሉ።
በዚህ ስምምነት ላይም በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በአገራቱ መካከል ትብብር፣ ፍትሐዊ እና አሳማኝ አጠቃቀም ዙሪያ በየትኛውም አገር ላይ “ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ” አስፈላጊ በሆነ መንገድ ሁሉ ጉዳቱን ማስቀረት ይገባል እንደሚል በመጥቀስ ግብፅ ስጋቷን ታነሳለች።
በኢትዮጵያ በኩል ግን ግድቡ ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት የሚውል በመሆኑ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የጎላ ጉዳት ስለማያመጣ በውሃው የመጠቀም መብቷን ጥያቄ ውስጥ የሚያሰገባ ግዴታን እንደማትፈርም አሳውቃለች።
ግብፅ በበኩሏ የአባይ ወንዝ በዋነኛነት የእርሻና የመጠጥ ውሃ ምንጯ በመሆኑ መጠኑ የሚቀንስ ከሆነ በሕዝቧ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚከሰት በመግለጽ ጥቅሟን ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ እደምታደርግ ስትገልጽ፤ በተለይ ከሱዳን ጋር ወታደራዊ ስምምነት በመድረስ የጦር ልምምድ እስከማድረግ ደርሳለች።
ኢትዮጵያ ደግሞ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ውስጥ የለውን ሕዝቧን ብርሃን ለማሳየትና ኢንዱስትሪዋን ለማጠናከር ግድቡ የማትደራደርበት ፕሮጀክት መሆኑን በመጥቀስ በየትኛውም መልኩ ግድቡን ለመከላከል ዝግጁ መሆኗን አሳውቃለች።
አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በተለይ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉላት አንጋፋ ዲፕሎማቶችን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ስትሾም አንደኛው ሥራቸው የነበረው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአገራቱ መካከል ስምምነት እንዲደረስ ማድረግ ሆኖ ቆይቷል።
ግብፅም ባገኘችው አጋጣሚዎች ሁሉ ተሰሚነት ያላቸውና ተጽፅኖ ማሳደር ለሚችሉ መሪዎችንና ተቋማት በውሃ ደኅንነቷ ላይ ተጋርጧል የምትለውን ስጋት በማስረዳት እንዲደግፏት ስትጥር ቆይታለች።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሳዑዲ አረቢያን ከጎበኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር የተገናኙት ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ የግድቡን ጉዳይ አንስተው መወያየታቸውንየሁለቱም መሪዎች ጽህፈት ቤቶች መግለጻቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ አገራቸው የግድቡን የውሃ ሙሌትና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ የግብፅን የውሃ ዋስትናን በሚያስከብር መልኩ “አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረስ” ያላቸውን ፍላጎት ለባይደን የገለጹ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ባይደንም አሜሪካ የግብፅን የውሃ ዋስትና እንደምትደግፍ እንዲሁም ለአካባቢው ሰላምና ብልጽግና አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያስከብር ስምምነት እንዲደረስ እንደሚሹ መናገራቸው ተዘግቧል።
የሕዳሴው ግድብ እውነታዎች
የግንባታውመሠረተ ድንጋይ መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የተጣለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በስተምዕራብ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ ይገኛል።
ግድቡንለመገንባት 80 ቢሊየን ብር (ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ) የሚያስወጣ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ግንባታው በዋናነት በጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ በተባለው ሥራ ተቋራጮ የሚከናወን ነው።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ የሚሆነው የሕዳሴ፣ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሆናል።
ለዚህም በተከታታይ ዓመታት የሚካሄድ የውሃ ሙሌት የሚኖር ሲሆን በ2012 ዓ.ም እና 2013 ዓ.ም ሁለት ክረምቶች ለተከታታይ ጊዜ የውሃ ሙሌት ተካሂዶ በዚህ ዓመትም ሙሌቱ ይካሄዳል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሆነው ይህ ግድብ 13 ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን አንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በተያዘለት ዕቅድ መሠረትም የካቲት 13/2014 ዓ.ም. በአንድ ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ሁሉም ተርባይኖች ሥራ ሲጀምሩ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የማመንጨት አቅሙ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ይደርሳል።