ስለ ዓባይ ወንዝ እና የሕዳሴ ግድቡ ጥቂት እውነታዎች

አሥር ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በግንባታ ላይ የቆየው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ መጀመሩ ሱዳንና ግብፅን ቅር አሰኝቷል።

2003 ዓ. ም ላይ ኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ግብፅና ሱዳን ተቃውሞና ስጋታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ እስከ ዛሬ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ላለፉት አሥር ዓመታት በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ዓባይ. . .

ዓባይ ከዓለማችን ረዛዥም ወንዞች በቀዳሚነት ይቀመጣል። 6696 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም መረጃዎች ያሳያሉ።

ወንዙ 2700 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ ይጓዛል። አማዞን ወንዝን እንደ ምሳሌ ብናነሳ ከዓባይ ወንዝ አንጻር 65 እጥፍ ያህል ይፈጥናል።

10 የዓባይ ተፋሰስ አገራት አሉ። እነዚህም ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ግብፅ እና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡

ሁለት አገራት አባይን ተከፋፍለው ይዘዋል። ግብፅ እና ሱዳን።

በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ አደራዳሪነት በተደረገ ስምምነት ወንዙን ለመከፋፈል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ግብፅ 66 በመቶ ድርሻ ሲኖራት 22 በመቶ ደግሞ የሱዳን ነው። 12 በመቶ የሚሆነው ውሃው በመትነን የሚያልቅ ሲሆን ኢትዮጵያ ምንም ድርሻ የላትም።

ግብፅና ሱዳን የዓባይ ወንዝን በተመለከተ የተጋነነ ወይም ከመስመር የወጣ የባለቤትነት ጥያቄ እያነሱ ነው ብለው የሚያምኑና የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት የሚደግፉ ወገኖች ይህንን ስምምነት የቅኝ ግዛት ስምምነት ሲሉ ያጣጥሉታል።

ግብፅ በላይኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር (ቪቶ ፓወር) አላት። በዚህ ስምምነት ላይ ኢትየጵያ ምንም ተሳተፎ አልነበራትም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ ይገኛል።

የግንባታው መሠረተ ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ. ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ነው የተቀመጠው።

የግድቡን ግንባታ ከሚያከናውኑ ሥራ ተቋራጮች መካከል የጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ ይጠቀሳለ።

ግድቡን ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ 80 ቢሊየን ብር (ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ) እንደሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።

የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።

የዋናው ግድብ ውፍረት የግድቡ ግርጌ ላይ 130 ሜትር ሲሆን፤ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል ደግሞ 11 ሜትር ነው።

ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል

የግድቡ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች 16 ናቸው። እያንዳንዱ ዩኒት የሚያመነጨው የኃይል መጠን ከ375 እስከ 400 ሜጋዋት ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 6450 ሜጋዋት ኃይል ማምረት ይችላል።

ከግድቡ የሚገኘውን ኃይል ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ የሚተርፈውን ማለትም 2000 ሜጋዋት ያህሉን ለጎረቤት አገራት በመሸጥ በዓመት እስከ 580 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላል ተብሎ ተገምቷል።

ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሕዝብ ብዛት ያላት ግብፅ፤ ከኢትዮጵያ 15 እጥፍ የሚያህል የኃይል ፍጆታ አላት። የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍጆታ 10.7 ቢሊዮን ኪሎዋት ሲሆን የግብፅ ደግሞ 159 ቢሊዮን ኪሎዋት ነው።

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ዙር የግድቡ ሙሌት ተከናውኗል። በዚህም 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ ዕቅዱ ተሳክቷል። ዘንድሮ ተጨማሪ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለመያዝ ነው የታቀደው።

በቀጣይ ደግሞ ከውሃ ሙሌት ጎን ለጎን የኃይል ማመንጨት ሙከራ እና ሥራው ይከናወናል ተብሏል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃ የሚተኛበት መሬት ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ ግንባታው አሁን ላይ ከ78 በመቶ በላይ ደርሷል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 78 ነጥብ 3 መድረሱን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአምስት ወራት በፊት አስታውቆ ነበር።

በወቅቱ ሚኒስቴሩ በስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራትንና የሕዳሴ ግድቡን የግንባታ ሂደት በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ የግድቡ ግንባታ የሲቪል ሥራዎች አፈጻጸም 91 በመቶ ደርሷል።

በተመሳሳይ ወቅት አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም ደግሞ 78 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል።